Biblia Todo Logo
在线圣经

- 广告 -

2 ዜና መዋዕል 4 - አዲሱ መደበኛ ትርጒም


የቤተ መቅደሱ ዕቃዎች መሟላት
4፥2-6 ፤ 4፥10–5፥1 ተጓ ምብ – 1ነገ 7፥23-26 ፤ 7፥38-51

1 ርዝመቱ ሃያ ክንድ፣ ወርዱ ሃያ ክንድ፣ ቁመቱ ዐሥር ክንድ የሆነ የናስ መሠዊያ ሠራ።

2 እንዲሁም ስፋቱ ከጠርዝ እስከ ጠርዝ ዐሥር ክንድ፣ ቁመቱ ዐምስት ክንድ የሆነ ክብ ገንዳ ከቀለጠ ብረት ሠራ፤ ዙሪያውም ሲለካ ሠላሳ ክንድ ሆነ።

3 ከገንዳው ከንፈር በታችም በእያንዳንዱ ክንድ ርቀት ላይ ዙሪያውን ዐሥር የኰርማ ቅርጾች ነበሩበት፤ ኰርማዎቹም ከገንዳው ጋራ አንድ ወጥ ሆነው በሁለት ረድፍ ቀልጠው ተሠርተው ነበር።

4 ገንዳውም፣ ሦስቱ ፊታቸውን ወደ ሰሜን፣ ሦስቱ ወደ ደቡብ፣ ሦስቱ ወደ ምዕራብ፣ ሦስቱ ወደ ምሥራቅ ባዞሩ የዐሥራ ሁለት በሬዎች ምስሎች ላይ የተቀመጠ ሲሆን፣ ገንዳው በላያቸው ሆኖ የሁሉም የኋላ አካል በመካከል ላይ የገጠመ ነበር።

5 የገንዳው ውፍረት አንድ ስንዝር ሲሆን፣ የከንፈሩ ጠርዝ ደግሞ የአበባ ቅርጽ ያለው የጽዋ ከንፈር የመሰለ ነው፤ ይህም ሦስት ሺሕ የባዶስ መስፈሪያ ያህል ውሃ የሚይዝ ነው።

6 እንዲሁም ዐሥር የመታጠቢያ ገንዳዎች አሠርቶ ዐምስቱን በደቡብ፣ ዐምስቱን ደግሞ በሰሜን በኩል አስቀመጠ፤ ገንዳዎቹ ለሚቃጠል መሥዋዕት የሚቀርቡት ነገሮች የሚታጠቡባቸው ሲሆኑ፣ ገንዳው ግን ለካህናት መታጠቢያ የሚያገለግል ነበር።

7 በተሰጠው የአሠራር መመሪያ መሠረት፣ ዐሥር የወርቅ መቅረዞች ሠርቶ ወደ ቤተ መቅደሱ በማስገባት፣ ዐምስቱን በስተ ደቡብ፣ ዐምስቱን በስተሰሜን አኖራቸው።

8 ዐሥር ጠረጴዛ ሠርቶም ወደ ቤተ መቅደሱ በማስገባት ዐምስቱን በስተ ደቡብ፣ ዐምስቱን ደግሞ በስተሰሜን በኩል አኖራቸው፤ ደግሞም አንድ መቶ ጐድጓዳ የወርቅ ሳሕኖች ሠራ።

9 የካህናቱንም አደባባይ ሠራ፤ እንዲሁም ታላቁን አደባባይና በሮቹን ከሠራ በኋላ በናስ ለበጣቸው።

10 ገንዳውንም ከቤተ መቅደሱ በስተ ደቡብ ምሥራቅ ባለው ማእዘን በቀኝ በኩል አኖረው።

11 ኪራምም ምንቸቶችን፣ መጫሪያዎችንና ጐድጓዳ ሳሕኖችን ሠራ። ኪራምም ለአምላክ ቤተ መቅደስ አገልግሎት ለንጉሥ ሰሎሞን የሠራውን ሥራ ፈጸመ እነዚህም፦

12 ሁለቱን አዕማድ፣ በአዕማዱ ጫፎች ላይ ያሉትን ሁለት ባለሳሕን ጕልላቶችን፤ በአዕማዱ ላይ ያሉትን ባለሳሕን ቅርጽ ሁለት ጕልላቶችን ያስጌጡትን ሁለት መረቦች፤

13 በአዕማዱ ጫፎች ላይ ያሉትን ባለሳሕን ቅርጽ ጕልላቶች የሚሸፍኑና በሁለት ረድፍ የተቀረጹትን መረቦች የሚያስጌጡትን አራት መቶ ሮማኖች፤

14 መቆሚያዎች ከነመታጠቢያ ገንዳዎቻቸው፤

15 ገንዳውና ከሥሩ ያሉትን ዐሥራ ሁለት ኰርማዎች፤

16 ምንቸቶችን፣ መጫሪያዎችን፣ ሜንጦዎችንና ከእነዚሁም ጋራ የተያያዙ ዕቃዎች። ኪራምአቢ ለእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ መገልገያ እንዲሆኑ ለንጉሥ ሰሎሞን የሠራለት ከሚብረቀረቅ ናስ ነበር።

17 ንጉሡም እነዚህ ዕቃዎች በዮርዳኖስ ሸለቆ፣ በሱኮትና በጸሬዳ መካከል ባለው በሸክላ ዐፈር ቦታ ቀልጠው በሸክላ ቅርጽ ተሠርተው እንዲወጡ አደረገ።

18 እነዚህ ሰሎሞን ያሠራቸው ነገሮች ሁሉ እጅግ ብዙዎች ስለ ሆኑ የናሱ ክብደት ምን ያህል እንደ ነበር አልታወቀም።

19 እንደዚሁም ሰሎሞን ለቤተ መቅደስ መገልገያ የሚሆኑትን ዕቃዎች ሠራ፤ እነዚህም፦ የወርቅ መሠዊያ፣ የገጸ ኅብስቱ ጠረጴዛ፣

20 በተሰጠው መመሪያ መሠረት፣ በቅድስተ ቅዱሳኑ ፊት ለፊት እንዲነድዱ፣ ከንጹሕ ወርቅ የተሠሩ መቅረዞች ከነቀንዲሎቻቸው፣

21 ከወርቅ የተቀረጹ አበባዎችን እና ከንጹሕ ወርቅ የተሠሩ መኰስተሪያዎችን፤

22 ከንጹሕ ወርቅ የተሠሩ የመብራት መኰስተሪያዎች፣ ለመርጨት የሚያገለግሉ ጐድጓዳ ሳሕኖች፣ ጭልፋዎችና ጥናዎች፣ እንደዚሁም የቤተ መቅደሱ የወርቅ መዝጊያዎች፣ ይኸውም የቅድስተ ቅዱሳኑ የውስጠኛው መዝጊያዎችና የቤተ መቅደሱ አዳራሽ መዝጊያዎች ከንጹሕ ወርቅ የተሠሩ ነበሩ።

መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™

የቅጂ መብት © 2001, 2024 በBiblica, Inc.

በፈቃድ የሚወሰድ። በዓለም ዐቀፍ ባለቤትነቱ።

The Holy Bible, New Amharic Standard Version™

Copyright © 2001, 2024 by Biblica, Inc.

Used with permission. All rights reserved worldwide. 

Biblica, Inc.
跟着我们:



广告