Biblia Todo Logo
在线圣经

- 广告 -

2 ዜና መዋዕል 36 - አዲሱ መደበኛ ትርጒም

1 የአገሩም ሰዎች የኢዮስያስን ልጅ ኢዮአካዝን ወስደው በአባቱ ምትክ በኢየሩሳሌም አነገሡት።


የይሁዳ ንጉሥ ኢዮአካዝ
36፥2-4 ተጓ ምብ – 2ነገ 23፥31-34

2 ኢዮአካዝ በነገሠ ጊዜ፣ ዕድሜው ሃያ ሦስት ዓመት ነበር፤ በኢየሩሳሌም ተቀምጦም ሦስት ወር ገዛ።

3 ከዚያም የግብጽ ንጉሥ በኢየሩሳሌም ካለው ዙፋኑ አወረደው፣ በአገሩም ላይ አንድ መቶ መክሊት ብርና አንድ መክሊት ወርቅ ግብር ጣለበት።

4 የግብጽም ንጉሥ የኢዮአካዝን ወንድም ኤልያቄምን በይሁዳና በኢየሩሳሌም ላይ አነገሠው፤ ስሙንም ለውጦ ኢዮአቄም አለው። ኒካዑም የኤልያቄምን ወንድም ኢዮአካዝን ይዞ ወደ ግብጽ ወሰደው።


የይሁዳ ንጉሥ ኢዮአቄም
36፥5-8 ተጓ ምብ – 2ነገ 23፥36–24፥6

5 ኢዮአቄም በነገሠ ጊዜ፣ ዕድሜው ሃያ ዐምስት ዓመት ነበር፤ በኢየሩሳሌም ተቀምጦም ዐሥራ አንድ ዓመት ገዛ። በአምላኩም በእግዚአብሔር ፊት ክፉ ነገር አደረገ።

6 የባቢሎን ንጉሥ ናቡከደነፆር በርሱ ላይ ዘመተ፤ ወደ ባቢሎንም ይወስደው ዘንድ በናስ ሰንሰለት አሰረው።

7 እንደዚሁም ናቡከደነፆር የእግዚአብሔርን ቤተ መቅደስ ዕቃ ወስዶ፣ ባቢሎን ባለው በራሱ ቤተ ጣዖት አኖረው።

8 በኢዮአቄም ዘመነ መንግሥት የተከናወነው ሌላው ተግባሩ የፈጸመው አስጸያፊ ድርጊትና በርሱ ላይ የተገኘበት ነገር ሁሉ በእስራኤልና በይሁዳ ነገሥታት መጽሐፍ ተጽፏል። ልጁ ዮአኪንም በምትኩ ነገሠ።


የይሁዳ ንጉሥ ዮአኪን
36፥9-10 ተጓ ምብ – 2ነገ 24፥8-17

9 ዮአኪን በነገሠ ጊዜ፣ ዕድሜው ዐሥራ ስምንት ዓመት ነበር፤ በኢየሩሳሌም ተቀምጦም ሦስት ወር ከዐሥር ቀን ገዛ፤ እርሱም በእግዚአብሔር ፊት ክፉ ድርጊት ፈጸመ።

10 በጸደይም ወራት ንጉሡ ናቡከደነፆር ልኮ በእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ውስጥ ከፍተኛ ዋጋ ካላቸው ዕቃዎች ጋራ ወደ ባቢሎን ወሰደው። የዮአኪንን አጎት ሴዴቅያስን በይሁዳና በኢየሩሳሌም ላይ አነገሠው።


የይሁዳ ንጉሥ ሴዴቅያስ
36፥11-16 ተጓ ምብ – 2ነገ 24፥18 ፤ ኤር 52፥1-3

11 ሴዴቅያስ ሲነግሥ ዕድሜው ሃያ አንድ ዓመት ነበር፤ በኢየሩሳሌም ተቀምጦም ዐሥራ አንድ ዓመት ገዛ።

12 እርሱም በአምላኩ በእግዚአብሔር ፊት ክፉ ነገር አደረገ፤ የእግዚአብሔርን ቃል በተናገረው በነቢዩ በኤርምያስ ፊትም ራሱን ዝቅ አላደረገም።

13 እንደዚሁም በእግዚአብሔር ስም አምሎት በነበረው በንጉሥ ናቡከደነፆር ላይ ዐመፀ፤ ዐንገቱን አደነደነ፤ ልቡንም አጠነከረ እንጂ ወደ እስራኤል አምላክ ወደ እግዚአብሔር አልተመለሰም።

14 ከዚህም ላይ የካህናቱና የሕዝቡ መሪዎች ሁሉ፣ አስጸያፊ የሆኑትን የአሕዛብን ልማዶች በመከተልና በኢየሩሳሌም የተቀደሰውን የእግዚአብሔርን ቤተ መቅደስ በማርከስ፣ ባለመታመናቸው ከጊዜ ወደ ጊዜ እየባሱ ሄዱ።


የኢየሩሳሌም መውደቅ
36፥22-23 ተጓ ምብ – ዕዝ 1፥1-3

15 የአባቶቻቸው አምላክ እግዚአብሔር ለሕዝቡና ለማደሪያው ስለ ዐዘነ፣ መልእክተኞቹን ይልክ ነበር፤

16 እነርሱ ግን የእግዚአብሔር ቍጣ በሕዝቡ ላይ እስኪነሣሣና ፈውስም እስከማይገኝላቸው ድረስ በእግዚአብሔር መልእክተኞች ላይ ተሣለቁ፤ ቃሉን ናቁ፤ ነቢያቱንም አቃለሉ።

17 ስለዚህ የባቢሎናውያንን ንጉሥ አመጣባቸው፤ እርሱም ወጣቶቻቸውን በቤተ መቅደሱ ውስጥ በሰይፍ ፈጀ፤ ወጣቱንም ሆነ ወጣቲቱን፣ ሽማግሌውንም ሆነ በዕድሜ የገፋውን አላስቀረም፤ እግዚአብሔር ሁሉንም ለናቡከደነፆር አሳልፎ ሰጠው።

18 እርሱም ትልልቁንም ሆነ ትንንሹን የእግዚአብሔርን ቤተ መቅደስ ዕቃ በሙሉ፣ እንዲሁም የእግዚአብሔርን ቤተ መቅደስ ሀብት፣ የንጉሡንና የሹማምቱን ሀብት ሁሉ ወደ ባቢሎን አጋዘ።

19 የእግዚአብሔርን ቤተ መቅደስ በእሳት አቃጠሉ፤ የኢየሩሳሌምንም ቅጥሮች አፈረሱ፤ ቤተ መንግሥቶቹን በሙሉ አቃጠሉ፤ በዚያ የነበረውንም የከበረ ዕቃ በሙሉ አጠፉ።

20 ከሰይፍ የተረፉትን ቅሬታዎች በምርኮ ወደ ባቢሎን ወሰዳቸው፤ እስከ ፋርስ መንግሥት መነሣትም ድረስ የእርሱና የልጆቹ አገልጋዮች ሆኑ።

21 ምድሪቱም የሰንበት ዕረፍት አገኘች፤ በኤርምያስ የተነገረው የእግዚአብሔር ቃል ይፈጸም ዘንድ፣ ሰባው ዓመት እስኪያበቃ ድረስ፣ ባድማ በነበረችበት ዘመን ሁሉ ዐረፈች።

22 በፋርስ ንጉሥ በቂሮስ ዘመነ መንግሥት በመጀመሪያ ዓመት፣ በኤርምያስ የተነገረው የእግዚአብሔር ቃል ይፈጸም ዘንድ በግዛቱ ሁሉ ዐዋጅ እንዲያስነግርና ይህም እንዲጻፍ እግዚአብሔር የፋርስን ንጉሥ የቂሮስን መንፈስ አነሣሣ፤ እርሱም እንዲህ አለ፤

23 “የፋርስ ንጉሥ ቂሮስ እንዲህ ይላል፤ “ ‘የሰማይ አምላክ እግዚአብሔር የምድርን መንግሥታት ሁሉ ሰጥቶኛል፤ በይሁዳ በምትገኘው በኢየሩሳሌም ቤተ መቅደስ እንድሠራለት አዝዞኛል፤ ከሕዝቡ መካከል በእናንተ ዘንድ የሚገኝ ማንኛውም ሰው፣ እግዚአብሔር አምላኩ ከርሱ ጋራ ይሁን፤ እርሱም ወደዚያው ይውጣ።’ ”

መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™

የቅጂ መብት © 2001, 2024 በBiblica, Inc.

በፈቃድ የሚወሰድ። በዓለም ዐቀፍ ባለቤትነቱ።

The Holy Bible, New Amharic Standard Version™

Copyright © 2001, 2024 by Biblica, Inc.

Used with permission. All rights reserved worldwide. 

Biblica, Inc.
跟着我们:



广告