Biblia Todo Logo
在线圣经

- 广告 -

2 ዜና መዋዕል 35 - አዲሱ መደበኛ ትርጒም


ኢዮስያስ ፋሲካን ማክበሩ
35፥1 ፤ 35፥18-19 ተጓ ምብ – 2ነገ 23፥21-23

1 ኢዮስያስ በኢየሩሳሌም ለእግዚአብሔር ፋሲካን አደረገ፤ በመጀመሪያውም ወር በዐሥራ አራተኛው ቀን የፋሲካው በግ ታረደ።

2 ካህናቱን በየአገልግሎታቸው መደበ፤ በእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ አገልግሎትም እንዲተጉ አበረታታቸው።

3 እስራኤልን ሁሉ ያስተምሩ ለነበሩትና ራሳቸውን ለእግዚአብሔር ለቀደሱት ሌዋውያን እንዲህ አላቸው፤ “የእግዚአብሔርን ታቦት የእስራኤል ንጉሥ የዳዊት ልጅ ሰሎሞን ባሠራው ቤተ መቅደስ አኑሩ፤ በእናንተ ትከሻ አትሸከሙት፤ አሁንም አምላካችሁን እግዚአብሔርንና ሕዝቡን እስራኤልን አገልግሉ።

4 በእስራኤል ንጉሥ በዳዊትና በልጁ በሰሎሞን በተጻፈው መመሪያ መሠረት፣ እንደየቤተ ሰባችሁ በክፍል በክፍላችሁ ራሳችሁን አዘጋጁ።

5 “ሌዋውያን ባልሆኑ ወንድሞቻችሁ አንጻር እንደየቤተ ሰቡ ምድብ በተቀደሰው ስፍራ ቁሙ፤ ለእያንዳንዱም የቤተ ሰብ ምድብ ሌዋውያን ይኑሩት።

6 ከዚያም የፋሲካውን በጎች ዕረዱ፤ ራሳችሁን ቀድሱ፤ እግዚአብሔር በሙሴ አማካይነት ባዘዘውም መሠረት ዕርዶቹን ለወንድሞቻችሁ አዘጋጁ።”

7 ኢዮስያስም እዚያ ለነበሩት ሕዝብ ሁሉ ለፋሲካው መሥዋዕት እንዲሆኑ በአጠቃላይ ሠላሳ ሺሕ በግና ፍየል እንዲሁም ሦስት ሺሕ ወይፈን ከንጉሡ ሀብት ሰጠ።

8 ሹማምቱም ለሕዝቡ፣ ለካህናቱና ለሌዋውያኑ በገዛ ፈቃዳቸው አዋጥተው ሰጡ። የእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ አለቆች የሆኑት ኬልቅያስ፣ ዘካርያስና ይሒኤልም ለፋሲካ መሥዋዕት የሚቀርቡ ሁለት ሺሕ ስድስት መቶ በግ እንዲሁም ሦስት መቶ ወይፈን ሰጡ።

9 ደግሞም ኮናንያ፣ ወንድሞቹ ሸማያና ናትናኤል እንደዚሁም የሌዋውያኑ መሪዎች ሐሸቢያ፣ ይዔኤልና ዮዛባት ለፋሲካ መሥዋዕት እንዲሆኑ ዐምስት ሺሕ በግና ፍየል ዐምስት መቶም በሬ ለሌዋውያኑ ሰጧቸው።

10 የአገልግሎቱ ዝግጅት በተጠናቀቀ ጊዜ፣ ንጉሡ ባዘዘው መሠረት ካህናቱ በየክፍላቸው ከተመደቡት ሌዋውያን ጋራ ቦታ ቦታቸውን ይዘው ቆሙ።

11 የፋሲካው በጎች ታረዱ፤ ካህናቱ የተቀበሉትን ደም ረጩ፤ ሌዋውያኑም የበጎቹን ቈዳ ገፈፉ።

12 በሙሴ ሕግ እንደ ተጻፈው ለእግዚአብሔር እንዲያቀርቡም፣ እንደየቤተ ሰቡና እንደየምድቡ ለሕዝቡ ለመስጠት የሚቃጠለውን መሥዋዕት ለዩ፤ ወይፈኖቹንም እንደዚሁ አደረጉ።

13 እነርሱም የፋሲካውን መሥዋዕት በሥርዐቱ መሠረት ጠበሱ፤ የተቀደሰውንም ቍርባን በምንቸት፣ በሰታቴና በድስት ቀቀሉ፤ ወዲያውኑም ለሕዝቡ አደሉ።

14 ከዚህ በኋላ ለራሳቸውና ለካህናቱ ዝግጅት አደረጉ፤ ምክንያቱም ካህናቱ የአሮን ልጆች የሚቃጠለውን መሥዋዕትና ሥቡን እስከ ሌሊት ድረስ ያቀርቡ ስለ ነበር ነው። ስለዚህ ሌዋውያኑ ለራሳቸውና ለካህናቱ ለአሮን ልጆች ዝግጅት አደረጉ።

15 መዘምራኑ የአሳፍ ዘሮች በዳዊት፣ በአሳፍ፣ በኤማንና በንጉሡ ባለራእይ በኤዶታም በተሰጠው መመሪያ መሠረት በቦታቸው ነበሩ። በእያንዳንዱ በር ላይ የነበሩት በር ጠባቂዎችም ሌዋውያን ወገኖቻቸው ስላዘጋጁላቸው፣ ከጥበቃ ቦታቸው መለየት አያስፈልጋቸውም ነበር።

16 በዚህ ዐይነት የፋሲካን በዓል በማክበርና የሚቃጠል መሥዋዕት በእግዚአብሔር መሠዊያ ላይ በማቅረብ የእግዚአብሔር አገልግሎት ሁሉ ንጉሥ ኢዮስያስ ባዘዘው መሠረት በዚያ ቀን ተከናወነ።

17 በዚያ ጊዜ በስፍራው የተገኙ እስራኤላውያን የፋሲካን በዓል አከበሩ፤ የቂጣንም በዓል እንደዚሁ ሰባት ቀን አከበሩ።

18 ከነቢዩ ሳሙኤል ዘመን ጀምሮ እንዲህ ያለ ፋሲካ በእስራኤል ዘንድ ተከብሮ አያውቅም፤ ኢዮስያስ ከካህናቱ፣ ከሌዋውያኑ፣ ከመላው ይሁዳና ከእስራኤል፣ በዚያ ከነበሩትም ከኢየሩሳሌም ሰዎች ጋራ እንዳከበረው አድርጎ ያከበረ አንድም የእስራኤል ንጉሥ የለም።

19 ይህ ፋሲካ የተከበረው በኢዮስያስ ዘመነ መንግሥት በዐሥራ ስምንተኛው ዓመት ነበር።


የኢዮስያስ መሞት
35፥20–36፥1 ተጓ ምብ – 2ነገ 23፥28-30

20 ከዚህ ሁሉ በኋላ ኢዮስያስ ቤተ መቅደሱን አደራጅቶ ባጠናቀቀ ጊዜ፣ የግብጽ ንጉሥ ኒካዑ በኤፍራጥስ ወንዝ አጠገብ፣ በከርከሚሽ ላይ ለመዋጋት ወጣ፤ ኢዮስያስም ጦርነት ሊገጥመው ወጣ።

21 ኒካዑ ግን መልእክተኛውን ልኮ፣ “የይሁዳ ንጉሥ ሆይ፤ አንተንና እኔን የሚያጣላን ምንድን ነው? ጦርነት ከገጠምሁት ቤት ጋራ እንጂ በአሁኑ ጊዜ አንተን የምወጋህ አይደለሁም፤ እግዚአብሔር እንድፈጥን አዝዞኛል፤ ስለዚህ ከእኔ ጋራ ያለውን እግዚአብሔርን መቃወምህን ተው፤ አለዚያ ያጠፋሃል” አለው።

22 ኢዮስያስ ግን ሌላ ሰው መስሎ በጦርነት ሊገጥመው ወጣ እንጂ ወደ ኋላ አልተመለሰም፤ በመጊዶ ሜዳ ላይ ሊዋጋው ሄደ እንጂ፣ ኒካዑ ከእግዚአብሔር ታዝዞ የነገረውን ሊሰማ አልፈለገም።

23 ቀስተኞች ንጉሥ ኢዮስያስን ወጉት፤ እርሱም የጦር መኰንኖቹን፣ “ክፉኛ ቈስያለሁና ከዚህ አውጡኝ” አላቸው።

24 ስለዚህ ከሠረገላው አውርደው በራሱ ሠረገላ ላይ አስቀምጠውት ወደ ኢየሩሳሌም ወሰዱት፤ እዚያም ሞተ፤ በአባቶቹ መካነ መቃብር ተቀበረ፤ የይሁዳና የኢየሩሳሌም ሕዝብ ሁሉ ለኢዮስያስ አለቀሱለት።

25 ኤርምያስ ለኢዮስያስ የሐዘን እንጕርጕሮ ግጥም ጻፈለት፤ ወንዶችና ሴቶች ሙሾ አውራጆች ሁሉ እስከ ዛሬ ድረስ በዚህ ግጥም ኢዮስያስን ያስታውሱታል፤ ይህም በእስራኤል የተለመደ ሆኖ በልቅሶ ግጥም መጽሐፍ ተጽፏል።

26 በኢዮስያስ ዘመነ መንግሥት የተከናወነው ሌላው ድርጊትና በእግዚአብሔር የሕግ መጽሐፍ በተጻፈው መሠረት ያከናወነው መንፈሳዊ ተግባር፣

27 ከመጀመሪያው እስከ መጨረሻው ያደረገው ሁሉ በይሁዳና በእስራኤል ነገሥታት መጽሐፍ ተጽፏል።

መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™

የቅጂ መብት © 2001, 2024 በBiblica, Inc.

በፈቃድ የሚወሰድ። በዓለም ዐቀፍ ባለቤትነቱ።

The Holy Bible, New Amharic Standard Version™

Copyright © 2001, 2024 by Biblica, Inc.

Used with permission. All rights reserved worldwide. 

Biblica, Inc.
跟着我们:



广告