2 ዜና መዋዕል 33 - አዲሱ መደበኛ ትርጒምየይሁዳ ንጉሥ ምናሴ 33፥18-20 ተጓ ምብ – 2ነገ 21፥17-18 1 ምናሴ በነገሠ ጊዜ፣ ዕድሜው ዐሥራ ሁለት ዓመት ነበር፤ በኢየሩሳሌም ተቀምጦም ዐምሳ ዐምስት ዓመት ገዛ። 2 እግዚአብሔር ከእስራኤላውያን ፊት አሳድዶ ያስወጣቸውን የአሕዛብን አስጸያፊ ልማድ በመከተል በእግዚአብሔር ፊት ክፉ ድርጊት ፈጸመ። 3 አባቱ ሕዝቅያስ ያፈራረሳቸውን የኰረብታ ላይ ማምለኪያ ስፍራዎች መልሶ ሠራ፤ ለበኣሊም መሠዊያዎችን አቆመ፤ የአሼራንም ምስል ዐምዶች ሠራ፤ ለሰማይ ከዋክብት ሰራዊትም ሁሉ ሰገደ፤ አመለካቸውም። 4 እግዚአብሔር፣ “ስሜ ለዘላለም በኢየሩሳሌም ይኖራል” ባለበት በእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ መሠዊያዎችን ሠራ። 5 በሁለቱም የእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ አደባባዮች፣ ለሁሉም የሰማይ ከዋክብት ሰራዊት መሠዊያዎችን ሠራ። 6 እርሱም በሄኖም ልጅ ሸለቆ ወንዶች ልጆቹን በእሳት ሠዋ፤ ሟርት፣ አስማት፣ መተትና ጥንቈላ አደረገ፤ ሙታን ጠሪዎችንና መናፍስት ሳቢዎችን ጠየቀ። ለቍጣ ያነሣሣው ዘንድ በእግዚአብሔር ፊት እጅግ ክፉ ነገር አደረገ። 7 ያበጀውን የተቀረጸ ምስል ወስዶ በእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ውስጥ አስቀመጠ፤ ይህም ቤተ መቅደስ እግዚአብሔር ለዳዊትና ለልጁ ለሰሎሞን፣ “በዚህ ቤተ መቅደስና ከእስራኤል ነገዶች ሁሉ በመረጥኋት በኢየሩሳሌም ስሜን ለዘላለም አኖራለሁ፤ ያለው ስፍራ ነው። 8 በሙሴ አማካይነት ያዘዝኋቸውን ሕጎቼን፣ ደንቦቼንና ሥርዐቶቼን ሁሉ በጥንቃቄ ይፈጽሙ እንጂ፣ ከእንግዲህ የእስራኤላውያን እግር ለአባቶቻችሁ ከሰጠኋቸው ምድር ለቅቆ እንዲወጣ አላደርግም።” 9 ምናሴ ግን እግዚአብሔር በእስራኤላውያን ፊት ካጠፋቸው አሕዛብ የባሰ ክፉ ድርጊት ይፈጽሙ ዘንድ፣ የይሁዳንና የኢየሩሳሌምን ሕዝብ አሳተ። 10 እግዚአብሔር ለምናሴና ለሕዝቡ ተናገረ፤ እነርሱ ግን መስማት አልፈለጉም። 11 ስለዚህ እግዚአብሔር የአሦርን ንጉሥ ሰራዊት አዛዦች አመጣባቸው፤ እነርሱም በምናሴ አፍንጫ መንጠቆ አገቡበት፤ በናስ ሰንሰለት አስረውም ወደ ባቢሎን ወሰዱት። 12 በተጨነቀም ጊዜ የአምላኩን የእግዚአብሔርን በጎነት ፈለገ፤ በአባቶቹም አምላክ ፊት ራሱን እጅግ አዋረደ። 13 ወደ እርሱም በጸለየ ጊዜ፣ በጭንቀት ልመናው ራርቶለት እግዚአብሔር ጸሎቱን ሰማው። ስለዚህ ወደ ኢየሩሳሌም፣ ወደ መንግሥቱም መለሰው፤ ምናሴም እግዚአብሔር አምላክ መሆኑን ዐወቀ። 14 ከዚህ በኋላ በሸለቆው ውስጥ ከሚገኘው ከግዮን ምንጭ ምዕራብ አንሥቶ እስከ ዓሣ በር መግቢያ ድረስ ያለውን የዳዊትን ከተማ የውጭውን ቅጥር፣ የዖፌልን ኰረብታ እንዲከብብ በማድረግ፣ ይበልጥ ከፍ አድርጎ እንደ ገና ሠራው። በተመሸጉትም የይሁዳ ከተሞች ሁሉ የጦር አዛዦችን አኖረ። 15 እንግዶች አማልክትንና ጣዖታቱን ከእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ አስወገደ፤ በቤተ መቅደሱ ኰረብታና በኢየሩሳሌም የሠራቸውንም መሠዊያዎች ሁሉ አራቀ፤ ከከተማዪቱም ውጭ ጣላቸው። 16 ከዚያም የእግዚአብሔርን መሠዊያ ዐደሰ፤ በላዩም የኅብረት መሥዋዕትና የምስጋና መሥዋዕት አቀረበ፤ ይሁዳም የእስራኤልን አምላክ እግዚአብሔርን እንዲያገለግሉ አዘዘ። 17 ሕዝቡ ግን በኰረብታ መስገጃ ስፍራዎች መሠዋቱን ቢቀጥልም፣ የሚሠዋው ግን ለአንዱ አምላክ ለእግዚአብሔር ብቻ ነበር። 18 በምናሴ ዘመነ መንግሥት የተከናወነው ሌላው ተግባር፣ ወደ አምላኩ ያቀረበው ጸሎቱና ባለራእዮች በእስራኤል አምላክ በእግዚአብሔር ስም የነገሩት ቃል በእስራኤል ነገሥታት ታሪክ ተጽፏል። 19 ጸሎቱና እግዚአብሔር ራርቶ ልመናውን እንዴት እንደ ተቀበለው፣ ኀጢአቱ ሁሉና ታማኝነቱን ማጕደሉ፣ እንደዚሁም ራሱን ከማዋረዱ በፊት ያሠራቸው የኰረብታ መስገጃ ስፍራዎች፣ ያቆማቸው የአሼራ ምስል ዐምዶችና ጣዖታት ሁሉ በባለራእዮች መዛግብት ተጽፈዋል። 20 ምናሴም እንደ አባቶቹ ሁሉ አንቀላፋ፤ በቤተ መንግሥቱም ተቀበረ። ልጁም አሞን በርሱ ፈንታ ነገሠ። የይሁዳ ንጉሥ አሞን 33፥21-25 ተጓ ምብ – 2ነገ 21፥19-20 21 አሞን በነገሠ ጊዜ ዕድሜው ሃያ ሁለት ዓመት ነበር፤ በኢየሩሳሌም ተቀምጦም ሁለት ዓመት ገዛ። 22 አባቱ ምናሴ እንዳደረገው ሁሉ እርሱም በእግዚአብሔር ፊት ክፉ ድርጊት ፈጸመ፤ አሞንም ምናሴ ለሠራቸው ጣዖታት ሁሉ ሠዋ፤ አመለካቸውም። 23 አሞን በእግዚአብሔር ፊት ራሱን እንዳዋረደ እንደ አባቱ እንደ ምናሴ ራሱን አላዋረደም፤ ነገር ግን በበደል ላይ በደል እየጨመረ ሄደ። 24 የአሞንም ሹማምት በርሱ ላይ አሢረው በቤተ መንግሥቱ ውስጥ ገደሉት። 25 ከዚያም የአገሩ ሕዝብ በንጉሥ አሞን ላይ ያሤሩትን ሁሉ ገደሉ፤ ልጁን ኢዮስያስንም በምትኩ አነገሡት። |
መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™
የቅጂ መብት © 2001, 2024 በBiblica, Inc.
በፈቃድ የሚወሰድ። በዓለም ዐቀፍ ባለቤትነቱ።
The Holy Bible, New Amharic Standard Version™
Copyright © 2001, 2024 by Biblica, Inc.
Used with permission. All rights reserved worldwide.
Biblica, Inc.