Biblia Todo Logo
在线圣经

- 广告 -

2 ዜና መዋዕል 32 - አዲሱ መደበኛ ትርጒም


ሰናክሬም በኢየሩሳሌም ላይ ዛተ
32፥20-21 ተጓ ምብ – 2ነገ 19፥35 ፤ ኢሳ 37፥36-38

1 ሕዝቅያስ እንዲህ ባለ ታማኝነት ነገሮችን ሁሉ ካከናወነ በኋላ፣ የአሦር ንጉሥ ሰናክሬም መጥቶ ይሁዳን ወረረ። ድል አድርጎ የራሱ ሊያደርጋቸው በማሰብም የተመሸጉትን ከተሞች ከበበ።

2 ሕዝቅያስም ሰናክሬም መምጣቱንና ኢየሩሳሌምንም ለመውጋት ማሰቡን ባወቀ ጊዜ፣

3 ከከተማዪቱ ውጭ ያሉት የውሃ ምንጮች እንዲዘጉ ከሹማምቱና ከጦር አለቆቹ ጋራ ተማከረ፤ እነርሱም ረዱት።

4 ብዙ ሰዎችም ተሰብስበው “የአሦር ነገሥታት መጥተው ስለ ምን ብዙ ውሃ ያገኛሉ?” በማለት ምንጮቹን ሁሉና በምድር ውስጥ ለውስጥ ይተላለፍ የነበረውን ውሃ ዘጉ።

5 ከዚህ በኋላም ንጉሡ ጠንክሮ በመሥራት፣ ከቅጥሩ የፈራረሱትን ሁሉ ጠገነ፤ በላዩም ማማ ሠራበት፤ በውጭ በኩልም ሌላ ቅጥር በመገንባት የዳዊትን ከተማ ድጋፍ እርከን አጠናከረ፤ እንደዚሁም ብዙ የጦር መሣሪያዎችንና ጋሻዎችን ሠራ።

6 የጦር መኰንኖችንም በሕዝቡ ላይ ሾሞ በከተማዪቱ በር አደባባይ ላይ በፊቱ ከሰበሰበ በኋላ፣ እንዲህ ሲል አበረታታቸው፤

7 “በርቱ፤ ጠንክሩ፤ ከእኛ ጋራ ያለው ከርሱ ጋራ ካለው ስለሚበልጥ፣ የአሦርን ንጉሥና ዐብሮት ያለውን ብዙ ሰራዊት አትፍሩ፤ አትደንግጡም።

8 ከእነርሱ ጋራ ያለው የሥጋ ክንድ ሲሆን፣ ከእኛ ጋራ ያለው ግን የሚረዳንና ጠላታችንን የሚዋጋልን አምላካችን እግዚአብሔር ነው።” ሕዝቡም የይሁዳ ንጉሥ ሕዝቅያስ በተናገረው ቃል ተበረታታ።

9 ከዚህ በኋላ የአሦር ንጉሥ ሰናክሬም ከሰራዊቱ ሁሉ ጋራ ለኪሶን ከብቦ ሳለ፣ የሚከተለውን መልእክት በጦር መኰንኖቹ አማካይነት፣ ለሕዝቅያስና ከርሱ ጋራ በኢየሩሳሌም ለነበሩት ለይሁዳ ሕዝብ ላከ፤

10 “የአሦር ንጉሥ ሰናክሬም እንዲህ ይላል፤ በተከበበችው በኢየሩሳሌም እስከዚህ የቈያችሁት በማን ተማምናችሁ ነው?

11 ሕዝቅያስ፣ ‘አምላካችን እግዚአብሔር ከአሦር ንጉሥ እጅ ያድነናል’ ማለቱስ በራብና በጥማት እንድትሞቱ ሊያሳስታችሁ አይደለምን?

12 ለይሁዳና ለኢየሩሳሌም፣ ‘በአንድ መሠዊያ ፊት ስገዱ፤ በላዩም መሥዋዕት አቃጥሉ’ በማለት የራሱን አምላክ የኰረብታ ላይ መስገጃ ስፍራዎችንና መሠዊያዎችንስ ያስወገደ ሕዝቅያስ አይደለምን?

13 “እኔና አባቶቼ በሌሎች አገሮች ሕዝቦች ሁሉ ላይ ያደረግነውን አታውቁምን? ታዲያ ከእነዚያ ከአሕዛብ አማልክት ምድራቸውን ከእጄ ለማዳን ችለዋልን?

14 አባቶቼ ሙሉ በሙሉ ከደመሰሷቸው ከእነዚህ መንግሥታት አማልክት ሁሉ፣ ሕዝቡን ከእጄ ሊያድን የቻለ አምላክ የትኛው ነው? ታዲያ አምላካችሁ እንዴት ከእጄ ሊታደጋችሁ ይችላል?

15 አሁንም ሕዝቅያስ አያታልላችሁ፤ አያስታችሁም። የየትኛውም አገር ሕዝብ ወይም መንግሥት አምላክ ሕዝቡን ከእጄ ወይም ከአባቶቼ እጅ መታደግ የቻለ ስለሌለ አትመኑት። የእናንተ አምላክማ ከእጄ ያድናችሁ ዘንድ ምንኛ ያንስ!”

16 የሰናክሬም ሹማምትም በእግዚአብሔር አምላክና በባሪያው በሕዝቅያስ ላይ ከዚህ የከፋ ብዙ ነገር ተናገሩ።

17 ንጉሡም እንደዚሁ የእስራኤልን አምላክ እግዚአብሔርን በመሳደብ፣ “የሌሎቹ አገሮች ሕዝቦች አማልክት፣ ከእጄ እንዳልታደጉ ሁሉ፣ የሕዝቅያስም አምላክ ሕዝቡን ከእጄ ሊታደግ አይችልም” ሲል በርሱ ላይ ደብዳቤ ጻፈ።

18 ከዚያም በማስደንገጥና በማስፈራራት ከተማዪቱን ለመያዝ ሲሉ በቅጥሩ ላይ ወደ ተቀመጠው ወደ ኢየሩሳሌም ሕዝብ ድምፃቸውን ከፍ አድርገው በዕብራይስጥ ጮኹ፤

19 የሰው እጅ በሠራቸው በሌሎች የምድር አሕዛብ አማልክት ላይ እንደ ተናገሩት ሁሉ፣ በኢየሩሳሌም አምላክ ላይም ተናገሩ።

20 ንጉሥ ሕዝቅያስና የአሞጽ ልጅ ነቢዩ ኢሳይያስም ስለዚህ ጕዳይ በጸሎት ወደ ሰማይ ጮኹ።

21 እግዚአብሔርም መልአክ ልኮ በአሦር ንጉሥ ሰፈር ተዋጊዎችን፣ መሪዎችንና የጦር መኰንኖችን እንዲያጠፋቸው አደረገ። ስለዚህ ንጉሡ በውርደት ወደ ገዛ አገሩ ተመለሰ። ወደ አምላኩ ቤተ ጣዖት እንደ ገባም፣ የገዛ ልጆቹ በሰይፍ ገደሉት።

22 እግዚአብሔርም ሕዝቅያስንና የኢየሩሳሌምን ሕዝብ ከአሦር ንጉሥ ከሰናክሬምና ከሌሎችም እጅ ሁሉ አዳናቸው፤ በዙሪያቸው ካሉትም ሁሉ ጠበቃቸው፤

23 ብዙዎችም ለእግዚአብሔር መባ ይዘው ወደ ኢየሩሳሌም መጡ፤ ለይሁዳ ንጉሥ ለሕዝቅያስም ውድ የሆኑ ገጸ በረከቶችን አመጡለት፤ ከዚያ ጊዜ ጀምሮም በአሕዛብ ሁሉ ፊት ከፍ ከፍ አለ።


የሕዝቅያስ ዕብሪት፣ ያከናወናቸው ተግባሮችና ሞቱ
32፥24-33 ተጓ ምብ – 2ነገ 20፥1-21 ፤ ኢሳ 37፥21-38 ፤ 38፥1-8

24 በዚያ ጊዜ ሕዝቅያስ ታምሞ ሊሞት ተቃርቦ ነበር፤ ወደ እግዚአብሔርም ጸለየ፤ እርሱም መለሰለት፤ ምልክትም ሰጠው።

25 የሕዝቅያስ ልብ ግን ታበየ እንጂ ስለ ተደረገለት በጎ ነገር ተገቢ ምላሽ አልሰጠም፤ በዚህ ምክንያት የእግዚአብሔር ቍጣ በርሱ፣ በይሁዳና በኢየሩሳሌም ላይ ወረደ።

26 ይሁን እንጂ ሕዝቅያስና የኢየሩሳሌም ሕዝብ ስለ ልባቸው ትዕቢት ራሳቸውን አዋረዱ፤ ስለዚህ የእግዚአብሔር ቍጣ በዘመነ መንግሥቱ አልመጣባቸውም።

27 ሕዝቅያስ እጅግ ብዙ ሀብትና ክብር ነበረው፤ ከዚህ የተነሣም ለብሩ፣ ለወርቁ፣ ለከበሩት ዕንቍዎቹ፣ ለቅመማ ቅመሞቹ፣ ለጋሻዎቹና ለተለያዩ ውድ ዕቃዎቹ ሁሉ ግምጃ ቤቶችን ሠራ።

28 እንደዚሁም ለእህሉ፣ ለወይን ጠጁና ለዘይቱ ማከማቻ የሚሆኑ ግምጃ ቤቶች ለተለያዩ እንስሳት በረት ለበግና ለፍየል መንጋም በረት ሠራ።

29 እግዚአብሔር ታላቅ ብልጽግና ስለ ሰጠው፤ ብዙ የበግና የፍየል፣ የእንስሳትም መንጋ ሰበሰበ፤ ከተሞችንም ሠራ።

30 የላይኛውን የግዮንን ምንጭ መውጫ ገድቦ፣ ውሃውን በቦይ ቍልቍል ወደ ምዕራቡ የዳዊት ከተማ እንዲወርድ ያደረገም ይኸው ሕዝቅያስ ነበር፤ ሥራውም ሁሉ ተከናወነለት።

31 ነገር ግን በምድሪቱ ላይ ስለ ተፈጸመው ታምራዊ ምልክት እንዲጠይቁት፣ የባቢሎን ገዦች መልእክተኞችን በላኩ ጊዜ፣ እግዚአብሔር ሊፈትነውና በልቡ ያለውን ሁሉ ሊያውቅ ስለ ፈለገ ተወው።

32 በሕዝቅያስ ዘመነ መንግሥት የተከናወኑ ሌሎች ተግባራትና ቸርነቱ በአሞጽ ልጅ በነቢዩ በኢሳይያስ ራእይ፣ በይሁዳና በእስራኤል ነገሥታት መጽሐፍ ተጽፏል።

33 ሕዝቅያስም ከአባቶቹ ጋራ አንቀላፋ፤ የዳዊት ዘሮች መካነ መቃብር በሆነው ኰረብታም ተቀበረ። በሞተም ጊዜ ይሁዳ ሁሉና የኢየሩሳሌም ሕዝብ በሙሉ አከበሩት። ልጁ ምናሴም በእግሩ ተተካ።

መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™

የቅጂ መብት © 2001, 2024 በBiblica, Inc.

በፈቃድ የሚወሰድ። በዓለም ዐቀፍ ባለቤትነቱ።

The Holy Bible, New Amharic Standard Version™

Copyright © 2001, 2024 by Biblica, Inc.

Used with permission. All rights reserved worldwide. 

Biblica, Inc.
跟着我们:



广告