2 ዜና መዋዕል 3 - አዲሱ መደበኛ ትርጒምሰሎሞን ቤተ መቅደስ ሠራ 3፥1-14 ተጓ ምብ – 1ነገ 6፥1-29 1 ሰሎሞንም በኢየሩሳሌም እግዚአብሔር ለአባቱ ለዳዊት በተገለጠበት በሞሪያ ተራራ ላይ በኢያቡሳዊው በኦርና ዐውድማ ዳዊት ባዘጋጀው ቦታ የእግዚአብሔርን ቤተ መቅደስ መሥራት ጀመረ። 2 በነገሠም በአራተኛው ዓመት፣ በሁለተኛው ወር፣ በሁለተኛው ቀን ቤተ መቅደሱን መሥራት ጀመረ። 3 ሰሎሞን ለአምላክ ቤተ መቅደስ ሕንጻ የጣለው መሠረት በቀድሞው ስፍር ልክ ርዝመቱ ስድሳ ክንድ፣ ወርዱም ሃያ ክንድ ነበር። 4 በቤተ መቅደሱ አዳራሽ ፊት ለፊት ያለው በረንዳ ርዝመቱ በቤተ መቅደሱ ወርድ ልክ ሃያ ክንድ ሲሆን፣ ከፍታውም ሃያ ክንድ ነበር። ውስጡንም በንጹሕ ወርቅ ለበጠው። 5 የቤተ መቅደሱን ዋና ክፍል በጥድ ዕንጨት አልብሶ በተጣራ ወርቅ ለበጠው፤ የዘንባባና የሰንሰለት አምሳልም ቀረጸበት። 6 ቤተ መቅደሱን በከበረ ድንጋይ አስጌጠው፤ የተጠቀመበትም ወርቅ የፈርዋይም ወርቅ ነበር። 7 የጣራውን ተሸካሚዎች፣ መቃኖችን፣ የቤተ መቅደሱን ግድግዳና መዝጊያዎች በወርቅ ለበጠ፤ በግድግዳዎቹም ላይ የኪሩቤልን ምስል ቀረጸ። 8 እንደዚሁም ቅድስተ ቅዱሳኑን ሠራ፤ ርዝመቱ ከቤተ መቅደሱ ወርድ ጋራ እኩል ሲሆን፣ ርዝመቱ ሃያ ክንድ፣ ስፋቱም ሃያ ክንድ ነበር፤ ውስጡንም በስድስት መቶ መክሊት የተጣራ ወርቅ ለበጠው። 9 የወርቅ ምስማሮቹም ዐምሳ ሰቅል ይመዝኑ ነበር፤ የላይኛውንም ክፍሎች እንደዚሁ በወርቅ ለበጠ። 10 በቅድስተ ቅዱሳኑ ውስጥ የሁለት ኪሩቤል ምስል አስቀርጾ በወርቅ ለበጣቸው። 11 ከዳር እስከ ዳር ገጥሞ የተዘረጋው የኪሩቤል ክንፍ በጠቅላላው ሃያ ክንድ ነበር፤ የመጀመሪያው ኪሩብ አንዱ ክንፍ ዐምስት ክንድ ሆኖ የቤተ መቅደሱን ግድግዳ ሲነካ፣ ሌላው ዐምስት ክንድ የሆነው ክንፉ ደግሞ የሁለተኛውን ኪሩብ ክንፍ ይነካ ነበር። 12 እንደዚሁም የሁለተኛው ኪሩብ አንዱ ክንፍ ዐምስት ክንድ ሆኖ በአንጻሩ ያለውን የቤተ መቅደስ ግድግዳ ሲነካ፣ ዐምስት ክንድ የሆነው ሌላው ክንፉ ደግሞ የመጀመሪያውን ኪሩብ ክንፍ ይነካ ነበር። 13 የተዘረጋው የእነዚህ ኪሩቤል ክንፍ ሃያ ክንድ ሲሆን፣ ፊታቸውን ወደ ቤተ መቅደሱ ዋና ክፍል አዙረው በእግራቸው ቆመዋል። 14 ደግሞም ከሰማያዊ፣ ከሐምራዊ፣ ከደማቅ ቀይ ፈትልና ከቀጭን በፍታ መጋረጃ ሠርቶ፣ የኪሩቤልን ምስል በጥልፍ ጠለፈበት። 15 በቤተ መቅደሱም ፊት ለፊት በአንድነት ቁመቱ ሠላሳ ዐምስት ክንድ የሆነ፣ በእያንዳንዱም ላይ ዐምስት ክንድ ጕልላት ያለው ሁለት ዐምድ ሠራ። 16 እርስ በርሳቸው የተጠላለፉ ሰንሰለቶች ሠርቶ ከዐምዶቹ ጫፍ ጋራ አገናኛቸው፤ ከዚያም መቶ የሮማን ፍሬዎች ሠርቶ ከሰንሰለቶቹ ጋራ አያያዛቸው። 17 ዐምዶቹንም አንዱን በደቡብ፣ ሌላውን በሰሜን አድርጎ በቤተ መቅደሱ ፊት ለፊት አቆማቸው፤ በስተ ደቡብ ያቆመውን ዐምድ፣ “ያኪን”፣ በስተሰሜን ያለውንም፣ “ቦዔዝ” ብሎ ጠራቸው። |
መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™
የቅጂ መብት © 2001, 2024 በBiblica, Inc.
በፈቃድ የሚወሰድ። በዓለም ዐቀፍ ባለቤትነቱ።
The Holy Bible, New Amharic Standard Version™
Copyright © 2001, 2024 by Biblica, Inc.
Used with permission. All rights reserved worldwide.
Biblica, Inc.