2 ዜና መዋዕል 27 - አዲሱ መደበኛ ትርጒምየይሁዳ ንጉሥ ኢዮአታም 27፥1-4 ፤ 27፥7-9 ተጓ ምብ – 2ነገ 15፥33-38 1 ኢዮአታም በነገሠ ጊዜ፣ ዕድሜው ሃያ ዐምስት ዓመት ነበር፤ ኢየሩሳሌም ተቀምጦም ዐሥራ ስድስት ዓመት ገዛ፤ እናቱም የሳዶቅ ልጅ ስትሆን፣ ኢየሩሳ ትባል ነበር። 2 አባቱ ዖዝያን እንዳደረገው ሁሉ እርሱም በእግዚአብሔር ፊት ቅን ነገር አደረገ፤ ነገር ግን እንደ አባቱ ወደ እግዚአብሔር ቤተ መቅደስ አልገባም። ሕዝቡም በበደሉ እንደ ገፋበት ነበር። 3 ኢዮአታም የእግዚአብሔርን ቤተ መቅደስ የላይኛውን በር ሠራ፤ በዖፌልም በኩል ባለው ቅጥር ላይ፣ አያሌ የማሻሻል ተግባር አከናወነ። 4 በይሁዳ ኰረብቶች ላይ ከተሞችን፣ ደን በለበሱ ስፍራዎችም ምሽጎችንና ማማዎችን ሠራ። 5 ኢዮአታም የአሞናውያንን ንጉሥ ወግቶ ድል አደረጋቸው። በዚያ ዓመትም አሞናውያን አንድ መቶ መክሊት ጥሬ ብር፣ ዐሥር ሺሕ ቆሮስ ስንዴና ዐሥር ሺሕ ቆሮስ ገብስ ገበሩለት። አሞናውያን በሁለተኛውና በሦስተኛው ዓመት ይህንኑ ግብር አመጡለት። 6 ኢዮአታም በአምላኩ በእግዚአብሔር ፊት በታማኝነት ስለ ተመላለሰ፣ እየበረታ ሄደ። 7 በኢዮአታም ዘመነ መንግሥት የተከናወነው ሌላው ተግባር፣ ያደረጋቸው ጦርነቶችና አካሄዱ ሁሉ በእስራኤልና በይሁዳ ነገሥታት መጽሐፍ ተጽፏል። 8 በነገሠ ጊዜ፣ ዕድሜው ሃያ ዐምስት ዓመት ነበር፤ ኢየሩሳሌም ተቀምጦም ዐሥራ ስድስት ዓመት ገዛ። 9 ኢዮአታምም ከአባቶቹ ጋራ አንቀላፋ፤ በዳዊት ከተማ ቀበሩት፤ ልጁ አካዝም በምትኩ ነገሠ። |
መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™
የቅጂ መብት © 2001, 2024 በBiblica, Inc.
በፈቃድ የሚወሰድ። በዓለም ዐቀፍ ባለቤትነቱ።
The Holy Bible, New Amharic Standard Version™
Copyright © 2001, 2024 by Biblica, Inc.
Used with permission. All rights reserved worldwide.
Biblica, Inc.