Biblia Todo Logo
在线圣经

- 广告 -

2 ዜና መዋዕል 26 - አዲሱ መደበኛ ትርጒም


የይሁዳ ንጉሥ ዖዝያን
26፥21-23 ተጓ ምብ – 2ነገ 15፥5-7

1 ከዚህ በኋላ የይሁዳ ሕዝብ በሙሉ ዕድሜው ዐሥራ ስድስት ዓመት የነበረውን ዖዝያንን ወስደው በአባቱ በአሜስያስ ፈንታ አነገሡት።

2 ንጉሥ አሜስያስ እንደ አባቶቹ ሁሉ ካንቀላፋ በኋላ፣ ኤላትን እንደ ገና የሠራት፣ ወደ ይሁዳም የመለሳት ዖዝያን ነበር።

3 ዖዝያን በነገሠ ጊዜ፣ ዕድሜው ዐሥራ ስድስት ዓመት ነበር፤ በኢየሩሳሌም ተቀምጦ ዐምሳ ሁለት ዓመት ገዛ። እናቱ ይኮልያ የተባለች የኢየሩሳሌም ሴት ነበረች።

4 እርሱም አባቱ አሜስያስ እንዳደረገው ሁሉ በእግዚአብሔር ፊት ቅን ነገር አደረገ።

5 እግዚአብሔርን መፍራት ባስተማረው በዘካርያስ ዘመን እግዚአብሔርን ፈለገ፤ እግዚአብሔርን በፈለገ መጠንም አምላክ ነገሮችን አከናወነለት።

6 በፍልስጥኤማውያን ላይ ዘምቶ የጋትን፣ የየብናንና የአዛጦንን ቅጥሮች አፈረሰ። ከዚያም በአዛጦን አጠገብና በቀሩትም የፍልስጥኤም ግዛቶች ውስጥ ከተሞችን እንደ ገና ሠራ።

7 እግዚአብሔርም በፍልስጥኤማውያን፣ በጉርበኣል በሚኖሩ ዐረቦችና በምዑናውያን ላይ ድልን አቀዳጀው።

8 አሞናውያን ለዖዝያን ግብር ገበሩለት፤ ኀይሉ ስለ ገነነም ዝናው እስከ ግብጽ ዳርቻ ወጣ።

9 ዖዝያንም በኢየሩሳሌም በማእዘኑ በር፣ በሸለቆው በርና በቅጥሩ ማእዘን ማማዎች ሠርቶ መሸጋቸው።

10 እንዲሁም በየኰረብታው ግርጌና በየሜዳው ላይ ብዙ የቀንድ ከብት ስለ ነበረው፣ በምድረ በዳ የግንብ ማማዎች ሠራ፤ ብዙ የውሃ ጕድጓዶችም ቈፈረ። ግብርና ይወድድ ስለ ነበረም በኰረብታዎችና ለም በሆኑ መሬቶች ላይ ዕርሻ የሚያርሱና ወይን የሚተክሉ ሠራተኞች ነበሩት።

11 ዖዝያን ከንጉሡ ሹማምት አንዱ በሆነው በሐናንያ መሪነት፣ በጸሓፊው በይዒኤልና በአለቃው በመዕሤያ አማካይነት ተሰብስቦ በተቈጠረው መሠረት በየምድቡ ለጦርነት ዝግጁ ሆኖ የሚወጣ፣ በሚገባ የሠለጠነ ሰራዊት ነበረው።

12 በተዋጊዎቹ ላይ የተሾሙት የየቤተ ሰቡ መሪዎች ጠቅላላ ቍጥር ሁለት ሺሕ ስድስት መቶ ነበር።

13 በእነዚህም የሚመራ ሦስት መቶ ሰባት ሺሕ ዐምስት መቶ ሰው ያለው ሰራዊት አለ፤ ይህም ንጉሡ በጠላቶቹ ላይ በሚያደርገው ዘመቻ ለመሰለፍ የሚበቃ ጠንካራ ኀይል ነበር።

14 ዖዝያን ለሰራዊቱ ሁሉ ጋሻ፣ ጦር፣ የራስ ቍር፣ ጥሩር፣ የቀስት ማስፈንጠሪያ ደጋንና የሚወነጨፍ ድንጋይ አደለ።

15 በኢየሩሳሌምም፣ ንድፎቻቸው በባለሙያዎች የተዘጋጁ፣ በመጠበቂያ የግንብ ማማዎችና በየማእዘኑ መከላከያዎች ላይ ፍላጻ የሚስፈነጠርባቸውንና ትልልቅ ድንጋዮች የሚወረወርባቸውን መሣሪያዎች አሠራ። እስኪበረታም ድረስ በሚያስደንቅ ሁኔታ ስለ ታገዘ፣ ዝናው በርቀትና በስፋት ተሰማ።

16 ዖዝያን ከበረታ በኋላ ግን ዕብሪቱ ለውድቀት ዳረገው። በዕጣን መሠዊያው ላይ ዕጣን ለማጠን ወደ እግዚአብሔር ቤተ መቅደስ በመግባቱ አምላኩን እግዚአብሔርን በደለ፤

17 ካህኑም ዓዛርያስ ቈራጥ ከሆኑ ከሌሎች ሰማንያ የእግዚአብሔር ካህናት ጋራ ተከትሎት ገባ።

18 እነርሱም ፊት ለፊት በመጋፈጥ፣ “ዖዝያን ሆይ፤ ለእግዚአብሔር ማጠን ለተለዩትና የአሮን ዘሮች ለሆኑት ለካህናቱ እንጂ ለአንተ የተገባ አይደለም፤ እግዚአብሔርን አልታመንህምና ከመቅደሱ ውጣ፤ ከእግዚአብሔር አምላክ ዘንድም ክብር አይሆንልህምና” አሉት።

19 ጥና በእጁ ይዞ ዕጣን ለማጠን ዝግጁ የነበረው ዖዝያን ተቈጣ፤ በእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ውስጥ በዕጣን መሠዊያው ፊት ሆኖ ካህናቱ ላይ እየተቈጣ ሳለ፣ በግንባሩ ላይ የቈዳ በሽታ ወጣበት።

20 ሊቀ ካህናቱ ዓዛርያስና ሌሎቹ ካህናት ሁሉ በተመለከቱት ጊዜ፣ በግንባሩ ላይ ለምጽ እንደ ወጣበት አዩ። ስለዚህ አጣድፈው አስወጡት፤ በርግጥ እርሱም ራሱ ለመውጣት ቸኵሎ ነበር፤ እግዚአብሔር አስጨንቆታልና።

21 ንጉሥ ዖዝያን እስከሚሞትበትም ቀን ድረስ ለምጽ ነበረበት። ለምጻም በመሆኑም ከእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ተወግዶ ነበርና በተለየ ቤት ተቀመጠ። በዚያ ጊዜ ቤተ መንግሥቱን በኀላፊነት የሚመራውና የአገሩንም ሕዝብ የሚያስተዳድረው የንጉሡ ልጅ ኢዮአታም ነበር።

22 በዖዝያን ዘመነ መንግሥት ከመጀመሪያው እስከ መጨረሻው የተከናወነውን ሌላውን ተግባር ሁሉ የአሞጽ ልጅ ነቢዩ ኢሳይያስ ጽፎታል።

23 ዖዝያንም ከአባቶቹ ጋራ አንቀላፋ። ሕዝቡም “ለምጽ አለበት” ብለው የነገሥታቱ በሆነው መቃብር አጠገብ ባለው ቦታ ቀበሩት፤ ልጁም ኢዮአታም በምትኩ ነገሠ።

መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™

የቅጂ መብት © 2001, 2024 በBiblica, Inc.

በፈቃድ የሚወሰድ። በዓለም ዐቀፍ ባለቤትነቱ።

The Holy Bible, New Amharic Standard Version™

Copyright © 2001, 2024 by Biblica, Inc.

Used with permission. All rights reserved worldwide. 

Biblica, Inc.
跟着我们:



广告