Biblia Todo Logo
在线圣经

- 广告 -

2 ዜና መዋዕል 25 - አዲሱ መደበኛ ትርጒም


የይሁዳ ንጉሥ አሜስያስ
25፥17-28 ተጓ ምብ – 2ነገ 14፥8-20

1 አሜስያስ በነገሠ ጊዜ፣ ዕድሜው ሃያ ዐምስት ዓመት ነበር፤ በኢየሩሳሌም ተቀምጦም ሃያ ዘጠኝ ዓመት ገዛ። እናቱም ዮዓዳን የተባለች የኢየሩሳሌም ሴት ነበረች።

2 እርሱም በእግዚአብሔር ፊት መልካም ነገር አደረገ፤ ነገር ግን በፍጹም ልቡ አልነበረም።

3 መንግሥቱም ከጸናለት በኋላ፣ ንጉሡን አባቱን የገደሉትን ሹማምት ገደላቸው።

4 እግዚአብሔር በሙሴ መጽሐፍ በተጻፈው ሕግ “ሰው ሁሉ በገዛ ኀጢአቱ ይሙት እንጂ ወላጆች በልጆቻቸው አይገደሉ፤ ልጆችም በወላጆቻቸው ኀጢአት አይገደሉ” ብሎ ባዘዘው መሠረት አደረገ እንጂ ልጆቻቸውን አልገደለም።

5 አሜስያስ የይሁዳን ሕዝብ በአንድነት ሰብስቦ፣ እንደየቤተ ሰቡ በሻለቆችና በመቶ አለቆች በመደልደል በመላው ይሁዳና በብንያም መደባቸው። ከዚያም ዕድሜያቸው ሃያና ከሃያ በላይ የሆናቸውን ሰብስቦ፣ ለውትድርና አገልግሎት ብቁ ሆነው ጋሻና ጦር መያዝ የሚችሉ ሦስት መቶ ሺሕ ሰዎች አገኘ።

6 እንዲሁም በመቶ መክሊት ጥሬ ብር አንድ መቶ ሺሕ ተዋጊዎች ከእስራኤል ቀጠረ።

7 ነገር ግን አንድ የእግዚአብሔር ሰው ወደ እርሱ መጥቶ እንዲህ አለው፤ “ንጉሥ ሆይ፤ እግዚአብሔር ከእስራኤልም ሆነ ከማናቸውም የኤፍሬም ሕዝብ ጋራ አይደለምና፣ እነዚህ የእስራኤል ወታደሮች ከአንተ ጋራ አይዝመቱ።

8 ሄደህ፣ ጦርነቱን በቈራጥነት ብትዋጋም እንኳ፣ የመርዳትና የመጣል ኀይል ከእግዚአብሔር ዘንድ ስለ ሆነ፣ እግዚአብሔር በጠላቶችህ ፊት ይጥልሃል።”

9 አሜስያስም የእግዚአብሔርን ሰው፣ “ታዲያ ለእነዚህ ለእስራኤል ወታደሮች የከፈልሁት መቶ መክሊት እንዴት ይሁን?” ሲል ጠየቀው። የእግዚአብሔርም ሰው፣ “እግዚአብሔር ከዚህ አብልጦ ሊሰጥህ ይችላል” ሲል መለሰለት።

10 ስለዚህ አሜስያስ ከኤፍሬም ወደ እርሱ የመጡትን ወታደሮች ወደየመኖሪያ ስፍራቸው አሰናበታቸው። እነርሱም በይሁዳ ላይ ክፉኛ ተበሳጭተው ነበርና በታላቅ ቍጣ ወደ መኖሪያ ስፍራቸው ተመለሱ።

11 አሜስያስም ኀይሉን በሚገባ አደራጅቶ ሰራዊቱን ወደ ጨው ሸለቆ መራ፤ በዚያም ዐሥር ሺሕ የሴይር ወታደሮችን ገደለ።

12 የይሁዳ ሰራዊት ሌሎች ዐሥር ሺሕ ሰዎች ማረኩ፤ ወደ አንድ ዐለት ዐናት ላይም አውጥተው ቍልቍል ለቀቋቸው፤ ሁሉም ተፈጠፈጡ።

13 በዚያ ጊዜ አሜስያስ ያሰናበታቸውና በጦርነቱ እንዳይካፈሉ የከለከላቸው ወታደሮች፤ ከሰማርያ እስከ ቤትሖሮን ያሉትን የይሁዳ ከተሞች ወረሩ፤ ሦስት ሺሕ ሰው ገደሉ፤ እጅግ ብዙ ምርኮም ወሰዱ።

14 አሜስያስም ኤዶማያውያንን ደምስሶ በተመለሰ ጊዜ፣ የሴይርን ሕዝብ አማልክት ይዞ መጣ፤ ለራሱም አማልክት አድርጎ በማቆም ሰገደላቸው፤ መሥዋዕትም አቀረበላቸው።

15 የእግዚአብሔርም ቍጣ በአሜስያስ ላይ ነደደ፤ ነቢይንም ላከበት፤ ነቢዩም፣ “የገዛ ሕዝባቸውን ከእጅህ ማዳን ያልቻሉትን የአሕዛብን አማልክት ርዳታ የጠየቅኸው ለምንድን ነው?” አለው።

16 እርሱም በመናገር ላይ ሳለ፣ ንጉሡ፣ “ለመሆኑ አንተን የንጉሥ አማካሪ አድርገን ሾመንሃልን? ዝም አትልም እንዴ! መሞት ትፈልጋለህ?” አለው። ነቢዩም ዝም አለ፤ ሆኖም፣ “ይህን አድርገሃልና ምክሬንም አልሰማህምና፤ አምላክ ሊያጠፋህ እንደ ወሰነ ዐውቃለሁ” አለ።

17 የይሁዳ ንጉሥ አሜስያስ አማካሪዎቹን ካማከረ በኋላ፣ የእስራኤል ንጉሥ የኢዩ የልጅ ልጅ፣ የኢዮአካዝ ልጅ ወደ ሆነው ወደ ኢዮአስ፣ “ናና ፊት ለፊት እንጋጠም” ሲል ላከበት።

18 የእስራኤል ንጉሥ ዮአስ ግን ለይሁዳ ንጉሥ ለአሜስያስ እንዲህ ሲል ላከበት፤ “አንድ የሊባኖስ ኵርንችት፣ ለአንድ የሊባኖስ ዝግባ፣ ‘ሴት ልጅህን ለልጄ ሚስት እንድትሆነው ስጠው’ አለው፤ ከዚያም አንድ የሊባኖስ ዱር አውሬ መጥቶ ኵርንችቱን በእግሩ ረገጠው።

19 እነሆ፤ ኤዶምን አሸንፌአለሁ ብለህ ልብህ በትዕቢት ተወጥሯል፤ አሁን ክብርህን ጠብቀህ ዐርፈህ በቤትህ ተቀመጥ! ጠብ በመጫር በራስህና በይሁዳ ላይ ውድቀት ለማምጣት ችግር የምትፈጥረው ለምንድን ነው?”

20 የኤዶምን አማልክት ማምለክ በመፈለጋቸው፣ እግዚአብሔር በጠላቶቻቸው እጅ አሳልፎ ሊሰጣቸው ወስኗልና፣ አሜስያስ አልሰማም።

21 ስለዚህ የእስራኤል ንጉሥ ኢዮአስ አደጋ ጣለ። እርሱና የይሁዳ ንጉሥ አሜስያስ በይሁዳ ምድር በቤትሳሚስ ፊት ለፊት ተጋጠሙ።

22 ይሁዳ በእስራኤል ድል ሆነ፤ እያንዳንዱም ወደ ድንኳኑ ሸሸ።

23 የእስራኤል ንጉሥ ዮአስም የአካዝያስን የልጅ ልጅ የኢዮአስን ልጅ የይሁዳ ንጉሥ አሜስያስን ቤትሳሚስ ላይ ማርኮ ወደ ኢየሩሳሌም አመጣው፤ ከኤፍሬም በር እስከ ማእዘኑ በር ድረስ አራት መቶ ክንድ ያህል ርዝመት ያለውን የኢየሩሳሌምን ቅጥር አፈረሰ።

24 እርሱም በአቢዳራ ጥበቃ ሥር የነበረውንና በአምላክ ቤተ መቅደስ የተገኘውን ወርቅ፣ ጥሬ ብርና ዕቃ በሙሉ፣ ከቤተ መንግሥቱም ንብረትና በመያዣ ከያዛቸው ሰዎች ጭምር ወስዶ ወደ ሰማርያ ተመለሰ።

25 የይሁዳ ንጉሥ የኢዮአስ ልጅ አሜስያስም፣ የእስራኤል ንጉሥ የኢዮአካዝ ልጅ ኢዮአስ ከሞተ በኋላ ዐሥራ ዐምስት ዓመት ኖረ።

26 በአሜስያስ ዘመነ መንግሥት ከመጀመሪያው እስከ መጨረሻው የተከናወነው ሌላው ተግባር ሁሉ በይሁዳና በእስራኤል ነገሥታት መጽሐፍ የተጻፈ አይደለምን?

27 አሜስያስ እግዚአብሔርን መከተል ከተወ በኋላ፣ አሜስያስ በኢየሩሳሌም ሤራ ስለ ጠነሰሱበት ሸሽቶ ወደ ለኪሶ ሄደ፤ እነርሱ ግን የሚከታተሉትን ሰዎች ወደ ለኪሶ ላኩ፤ እነርሱም ገደሉት።

28 አስከሬኑን በፈረስ ጭነው አመጡ። እንደ አባቶቹም በይሁዳ ከተማ ተቀበረ።

መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™

የቅጂ መብት © 2001, 2024 በBiblica, Inc.

በፈቃድ የሚወሰድ። በዓለም ዐቀፍ ባለቤትነቱ።

The Holy Bible, New Amharic Standard Version™

Copyright © 2001, 2024 by Biblica, Inc.

Used with permission. All rights reserved worldwide. 

Biblica, Inc.
跟着我们:



广告