Biblia Todo Logo
在线圣经

- 广告 -

2 ዜና መዋዕል 23 - አዲሱ መደበኛ ትርጒም

1 በሰባተኛውም ዓመት ዮዳሄ በረታ፤ የመቶ አለቆች ከሆኑት ከይሮሐም ልጅ ከዓዛርያስ፣ ከይሆሐናን ልጅ ከይስማኤል፣ ከዖቤድ ልጅ ከዓዛርያስ፣ ከዓዳያ ልጅ ከማዕሤያ፣ ከዝክሪ ልጅ ከኤሊሳፋጥ ጋራ ቃል ኪዳን አደረገ።

2 እነርሱም ወደ መላው ይሁዳ ሄደው፣ ሌዋውያንንና የእስራኤል ቤት አለቆችን ከየከተማው ሁሉ ሰበሰቡ። ወደ ኢየሩሳሌም በመጡ ጊዜም፣

3 ጉባኤው ሁሉ በእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ውስጥ ከንጉሡ ጋራ ቃል ኪዳን አደረጉ። ዮዳሄም እንዲህ አላቸው፤ “እግዚአብሔር ለዳዊት ዘር በሰጠው ተስፋ መሠረት እነሆ፤ የንጉሡ ልጅ ይነግሣል።

4 እንግዲህ እናንተ የምታደርጉት ይህ ነው፤ በሰንበት ዕለት ተረኛ ከሆናችሁት ከእናንተ ከካህናቱና ከሌዋውያኑ አንድ ሦስተኛው በሮቹን ጠብቁ፤

5 አንድ ሦስተኛው ቤተ መንግሥቱን፣ አንድ ሦስተኛው ‘የመሠረት ቅጽር በር’ የተባለውን ጠብቁ፤ የቀሩት ሰዎች በሙሉ በእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ አደባባይ ይሁኑ።

6 ተረኛ ከሆኑት ካህናትና ሌዋውያን በቀር ማንም ሰው ወደ እግዚአብሔር ቤተ መቅደስ አይግባ፤ እነርሱ የተቀደሱ ስለ ሆኑ ይግቡ፤ የቀሩት ሰዎች በሙሉ ግን፣ እግዚአብሔር ያዘዘውን ይጠብቁ።

7 ሌዋውያኑም እያንዳንዱ የጦር መሣሪያውን በእጁ ይዞ በንጉሡ ዙሪያ ሁኑ፤ ወደ ቤተ መቅደሱ የሚገባ ማንም ሰው ይገደል፤ ንጉሡ በሚሄድበትም ቦታ ሁሉ ዐብራችሁት ሁኑ።”

8 ሌዋውያኑና ይሁዳ ሁሉ ልክ ካህኑ ዮዳሄ እንዳዘዘው አደረጉ፤ ካህኑ ዮዳሄ ከጥበቃ ክፍሎች የትኛውንም አላሰናበተም ነበርና፣ እያንዳንዱ በሰንበት ቀን በሥራ ላይ የሚሰማሩትንና ከሥራ የሚወጡትን የራሱን ሰዎች ወሰደ፤

9 ካህኑ ዮዳሄ በአምላክ ቤተ መቅደስ የነበሩትን የንጉሥ ዳዊትን ጦሮች፣ ትላልቅና ትናንሽ ጋሻዎች ለመቶ አለቆቹ ሰጣቸው።

10 ሰዎቹንም ሁሉ እያንዳንዱ መሣሪያውን በእጁ ይዞ ከቤተ መቅደሱ ደቡብ አንሥቶ እስከ ሰሜን ድረስ በመሠዊያውና በቤተ መቅደሱ አጠገብ በንጉሡ ዙሪያ እንዲቆሙ አደረገ።

11 ዮዳሄና ወንዶች ልጆቹ የንጉሡን ልጅ አምጥተው ዘውድ ጫኑለት፤ ኪዳኑንም ሰጥተው አነገሡት፤ ቀብተውም፣ “ንጉሡ ለዘላለም ይኑር!” እያሉ ጮኹ።

12 ጎቶልያም የሚሯሯጠውንና ደስታውን ለንጉሡ የሚገልጠውን የሕዝቡን ጩኸት ስትሰማ፣ ሕዝቡ ወዳለበት ወደ እግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ሄደች።

13 እነሆ፤ ንጉሡ በመግቢያው ላይ ባለው በዐምዱ አጠገብ ቆሞ አየች፣ የጦር መኰንኖችና መለከት ነፊዎችም በንጉሡ አጠገቡ ነበሩ፤ የምድሪቱ ሕዝብ ሁሉ ይፈነጥዝ፣ መለከትም ይነፋ ነበር፤ መዘምራንም በዜማ ዕቃ ታጅበው የበዓሉን ዝማሬ ይመሩ ነበር፤ ጎቶልያም ልብሷን ቀድዳ፣ “ይህ ክሕደት ነው! ይህ ክሕደት ነው!” ብላ ጮኸች።

14 ካህኑ ዮዳሄም የወታደሮች አዛዥ ወደሆኑት ወደ መቶ አለቆቹ፣ “በሰልፉ መካከል አውጥታችሁ አምጧት፤ የሚከተላት ካለም በሰይፍ ግደሉት” ሲል ላከባቸው። ካህኑም፣ “በእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ አትግደሏት” ብሎ ነበርና።

15 እርሷም በቤተ መንግሥቱ ግቢ የፈረስ መግቢያ በር ወደተባለው ቦታ እንደ ደረሰች ያዟት፤ በዚያም ገደሏት።

16 ዮዳሄም ራሱ፣ ሕዝቡና ንጉሡ የእግዚአብሔር ሕዝብ ይሆኑ ዘንድ ቃል ኪዳን እንዲገቡ አደረገ።

17 ከዚያም ሕዝቡ ሁሉ ሄደው የበኣልን ቤተ ጣዖት አፈራረሱት፤ መሠዊያዎቹንና ምስሎቹን ሰባበሩ፤ የበኣልን ካህን ማታንንም በመሠዊያዎቹ ፊት ለፊት ገደሉት።

18 ዮዳሄም በሙሴ ሕግ እንደ ተጻፈውና ዳዊትም እንዳዘዘው፣ በደስታና በመዝሙር የሚቃጠለውን የእግዚአብሔርን መሥዋዕት እንዲያቀርቡ ዳዊት ለመደባቸው ካህናትና ሌዋውያን የእግዚአብሔርን ቤተ መቅደስ ኀላፊነት ሰጣቸው።

19 እንዲሁም በማንኛውም ነገር የረከሰ ሰው እንዳይገባ፣ በእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ቅጥር በሮች ላይ ጠባቆች አቆመ።

20 የመቶ አለቆቹን፣ መኳንንቱን፣ የሕዝቡን ገዦችና የአገሩን ሕዝብ ሁሉ ይዞ ንጉሡን ከላይ ከእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ወደ ታች አመጣው። በላይኛውም መግቢያ በኩል ወደ ቤተ መንግሥቱ ገብተው ንጉሡን በመንግሥቱ ዙፋን ላይ አስቀመጡት።

21 መላውም የአገሩ ሕዝብ ተደሰተ፤ ጎቶልያ በሰይፍ ስለ ተገደለች ከተማዪቱ ጸጥ አለች።

መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™

የቅጂ መብት © 2001, 2024 በBiblica, Inc.

በፈቃድ የሚወሰድ። በዓለም ዐቀፍ ባለቤትነቱ።

The Holy Bible, New Amharic Standard Version™

Copyright © 2001, 2024 by Biblica, Inc.

Used with permission. All rights reserved worldwide. 

Biblica, Inc.
跟着我们:



广告