2 ዜና መዋዕል 21 - አዲሱ መደበኛ ትርጒም1 ኢዮሣፍጥ ከአባቶቹ ጋራ አንቀላፋ፤ እነርሱ በተቀበሩበትም በዳዊት ከተማ ተቀበረ። ልጁ ኢዮራምም በምትኩ ነገሠ። 2 የኢዮሆራም ወንድሞች የሆኑት የኢዮሣፍጥ ልጆችም ዓዛርያስ፣ ይሒኤል፣ ዘካርያስ፣ ዔዛርያስ፣ ሚካኤልና ሰፋጥያስ ይባላሉ። እነዚህ ሁሉ የእስራኤል ንጉሥ የኢዮሣፍጥ ልጆች ነበሩ። 3 አባታቸውም ብዙ የብርና የወርቅ፣ የውድ ዕቃዎችም ስጦታ እንዲሁም በይሁዳ ያሉትን የተመሸጉ ከተሞች ሰጣቸው፤ ነገር ግን መንግሥቱን ለኢዮራም ሰጠ፤ የበኵር ልጁ ነበርና። የይሁዳ ንጉሥ ይሆራም 21፥5-10 ፤ 20 ተጓ ምብ – 2ነገ 8፥16-24 4 ኢዮራም በአባቱ መንግሥት ላይ ተደላድሎ ከተቀመጠ በኋላ፣ ወንድሞቹን በሙሉ ከጥቂት የእስራኤል አለቆች ጋራ በሰይፍ ገደለ። 5 ኢዮራም በነገሠ ጊዜ፣ ዕድሜው ሠላሳ ሁለት ዓመት ነበር፤ በኢየሩሳሌም ተቀምጦም ስምንት ዓመት ገዛ። 6 እርሱም የአክዓብን ልጅ አግብቶ ስለ ነበር፣ የአክዓብ ቤት እንዳደረገው ሁሉ፣ እርሱም የእስራኤል ነገሥታት የሄዱበትን መንገድ ተከተለ፤ በእግዚአብሔርም ፊት ክፉ ድርጊት ፈጸመ። 7 ይሁን እንጂ እግዚአብሔር ከዳዊት ጋራ ካደረገው ኪዳን የተነሣ፣ የዳዊትን ቤት ማጥፋት አልፈለገም፤ ለዳዊትና ለዘሩ ለዘላለም መብራት እንደሚሰጥ ተስፋ ሰጥቶ ነበርና። 8 በይሆራም ዘመነ መንግሥት ኤዶም በይሁዳ ላይ ዐምፆ፣ የራሱን ንጉሥ አነገሠ። 9 ስለዚህ ኢዮራም የጦር ሹማምቱና ሠረገላዎቹን ሁሉ አሰልፎ ተሻገረ። በሌሊትም ተነሥቶ እርሱንና የሠረገላ አዛዦቹን ሁሉ የከበቧቸውን ኤዶማውያንን መታ። 10 ኤዶም እስከ ዛሬ ድረስ በይሁዳ ላይ እንዳመፀ ነው፤ ልብናም በዚሁ ጊዜ ዐመፀ። ይሆራም የአባቶቹን አምላክ እግዚአብሔርን ትቶ ነበርና። 11 ከዚህም በላይ በይሁዳ ኰረብቶች ላይ መስገጃ ስፍራዎች ሠርቶ የኢየሩሳሌም ሕዝብ በዚያ እንዲያመነዝር አደረገ፤ ይሁዳንም አሳተ። 12 ከነቢዩ ከኤልያስ እንዲህ የሚል ደብዳቤ ለኢዮራም መጣ፤ “የአባትህ የዳዊት አምላክ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ ‘አንተ በአባትህ በኢዮሣፍጥ ወይም በይሁዳ ንጉሥ በአሳ መንገድ አልሄድህም፤ 13 ነገር ግን በእስራኤል ነገሥታት መንገድ ሄደሃል፤ የአክዓብ ቤት የእስራኤልን ሕዝብ እንዲያመነዝር እንዳደረገ ሁሉ፣ አንተም ይሁዳና የኢየሩሳሌም ሕዝብ እንዲያመነዝሩ አሳሳትሃቸው፤ እንዲሁም ካንተ የሚሻሉትን፣ የገዛ ወንድሞችህንና የአባትህን ቤተ ሰብ አባላት ገደልሃቸው፤ 14 ስለዚህ እነሆ፤ እግዚአብሔር ሕዝብህን፣ ልጆችህን፣ ሚስቶችህንና ያለህን ሁሉ በታላቅ መቅሠፍት ይመታል። 15 አንተም ራስህ በየዕለቱ እየባሰ በሚሄድ የአንጀት በሽታ ክፉኛ ትታመማለህ፤ በመጨረሻም ሕመሙ አንጀትህን ወደ ውጭ ያወጣዋል።’ ” 16 እግዚአብሔርም ፍልስጥኤማውያንንና በኢትዮጵያውያን አጠገብ የሚኖሩ ዐረቦችን በኢዮራም ላይ በጠላትነት እንዲነሡ አደረገ። 17 እነርሱም በይሁዳ ላይ ወጡ፤ ወረሯትም። በንጉሡ ቤተ መንግሥት የሚገኘውን ዕቃ ሁሉ፣ ከወንዶች ልጆቹና ከሚስቶቹ ጋራ ወሰዱ፤ ከመጨረሻ ልጁ ከአካዝያስ በቀር አንድም ልጅ አልቀረለትም። 18 ከዚህ ሁሉ በኋላ እግዚአብሔር ሊድን በማይችል የአንጀት በሽታ ይሆራምን ቀሠፈው። 19 ሕመሙም ሲያሠቃየው ከቈየ በኋላ፣ በሁለተኛው ዓመት መጨረሻ ላይ በዚሁ ሳቢያ አንጀቱ ወጥቶ በከባድ ሥቃይ ሞተ። ሕዝቡም ለአባቶቹ ክብር እሳት ያነድዱ ነበር፤ ለርሱ ግን አላነደዱለትም። 20 ኢዮራም ሲነግሥ ዕድሜው ሠላሳ ሁለት ዓመት ነበር፤ በኢየሩሳሌም ተቀምጦም ስምንት ዓመት ገዛ። በሞተ ጊዜም ማንም አላዘነለትም፤ በዳዊት ከተማ እንጂ በነገሥታቱ መቃብር አልቀበሩትም። |
መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™
የቅጂ መብት © 2001, 2024 በBiblica, Inc.
በፈቃድ የሚወሰድ። በዓለም ዐቀፍ ባለቤትነቱ።
The Holy Bible, New Amharic Standard Version™
Copyright © 2001, 2024 by Biblica, Inc.
Used with permission. All rights reserved worldwide.
Biblica, Inc.