2 ዜና መዋዕል 20 - አዲሱ መደበኛ ትርጒምኢዮሣፍጥ ሞዓብንና አሞንን ድል ማድረጉ 1 ከዚህ በኋላ ሞዓባውያንና አሞናውያን ከጥቂት ምዑናውያን ጋራ ሆነው ኢዮሣፍጥን ለመውጋት መጡ። 2 ሰዎችም መጥተው ኢዮሣፍጥን፣ “ግዙፍ ሰራዊት ሊወጋህ ከሙት ባሕር ወዲያ ካለው ከኤዶም መጥቶብሃል፤ እነሆም፣ ሐሴሶን ታማር በተባለው በዓይንጋዲ ናቸው” አሉት። 3 ኢዮሣፍጥም እጅግ ስለ ፈራ እግዚአብሔርን ለመፈለግ ፊቱን አቀና፤ በይሁዳም ሁሉ ጾም ዐወጀ። 4 የይሁዳ ሕዝብም የእግዚአብሔርን ርዳታ ይሻ ዘንድ በአንድነት ተሰበሰበ፤ ከይሁዳ ከተሞች ሁሉም እግዚአብሔርን ለመፈለግ መጡ። 5 ኢዮሣፍጥም በእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ፣ ከአዲሱ አደባባይ ፊት ለፊት በይሁዳና በኢየሩሳሌም ጉባኤ መካከል ቆመ፤ 6 እንዲህም አለ፤ “የአባቶቻችን አምላክ እግዚአብሔር ሆይ፤ አንተ በሰማይ የምትኖር አምላክ አይደለህምን? የምድር ሕዝቦችን መንግሥታት ሁሉ የምትገዛ አንተ ነህ፤ ኀይልና ሥልጣን በእጅህ ነው፤ ሊቋቋምህም የሚችል ማንም የለም። 7 አምላካችን ሆይ፤ የዚህችን ምድር ነዋሪዎች ከሕዝብህ ከእስራኤል ፊት አሳድደህ ያስወጣህና ለወዳጅህ ለአብርሃም ዘሮች ለዘላለም የሰጠሃቸው አንተ አይደለህምን? 8 እነርሱም ተቀመጡባት፤ ለስምህ መቅደስ ሠሩባት፤ እንዲህም አሉ፤ 9 ‘የፍርድ ሰይፍም ሆነ የቸነፈር ወይም የራብ መከራ ቢደርስብን፣ ስምህ በተጠራበት በዚህ ቤተ መቅደስ ፊት ለፊት፣ በፊትህ ቆመን በጭንቀታችን ወደ አንተ እንጮሃለን፤ አንተም ትሰማናለህ፤ ታድነናለህም።’ 10 “እስራኤል ከግብጽ በወጡ ጊዜ፣ ግዛታቸውን እንዳይወርሩባቸው በማድረግህ ከእነርሱ ተመልሰው ሳያጠፏቸው የቀሩት የአሞን፣ የሞዓብና የሴይር ተራራ ሰዎች እነሆ እዚህ አሉ። 11 እነሆ፣ አንተ ርስት አድርገህ ከሰጠኸን ምድር እኛን በማፈናቀል ወሮታ ሊመልሱልን መጥተዋል። 12 አምላካችን ሆይ፤ አንተ አትፈርድባቸውምን? የመጣብንን ይህን ታላቅ ሰራዊት እንቋቋም ዘንድ ዐቅም የለንምና የምናደርገውን አናውቅም፤ ነገር ግን ዐይኖቻችን ወዳንተ ናቸው።” 13 የይሁዳ ሰዎች ሁሉ ከሚስቶቻቸው፣ ከልጆቻቸውና ከሕፃኖቻቸው ጋራ በእግዚአብሔር ፊት ቆመው ነበር። 14 በዚህ ጊዜ የአሳፍ ዘር በሆነው በሌዋዊው በዘካርያስ ልጅ፣ በየሕዚኤል ላይ የእግዚአብሔር መንፈስ መጣ። ዘካርያስም የበናያስ ልጅ ሲሆን፣ በናያስም የመታንያን ልጅ የሆነው የይዒኤል ልጅ ነው። 15 እርሱም እንዲህ አለ፤ “ንጉሥ ኢዮሣፍጥ፣ እናንተም በይሁዳና በኢየሩሳሌም የምትኖሩ ሁሉ አድምጡ! እግዚአብሔር እንዲህ ይላችኋል፤ ‘ውጊያው የእግዚአብሔር እንጂ የእናንተ አይደለምና፣ ከዚህ ታላቅ ሰራዊት የተነሣ አትፍሩ፤ አትደንግጡ። 16 ነገ በእነርሱ ላይ ውረዱ፤ እነርሱ በጺጽ መተላለፊያ ሽቅብ ይወጣሉ፣ እናንተም በይሩኤል ምድረ በዳ ውስጥ በሸለቆው መጨረሻ ላይ ታገኟቸዋላችሁ። 17 ይህን ጦርነት የምትዋጉት እናንተ አይደላችሁም፤ ይሁዳና ኢየሩሳሌም ሆይ፤ ቦታ ቦታችሁን ያዙ፤ ጸንታችሁ ቁሙ፤ እግዚአብሔር የሚሰጣችሁንም ማዳን እዩ። አትፍሩ፤ አትደንግጡም፤ ነገውኑ ውጡና ግጠሟቸው፤ እግዚአብሔርም ከእናንተ ጋራ ይሆናል።’ ” 18 ኢዮሣፍጥ በግንባሩ ወደ መሬት ተደፋ፤ የይሁዳና የኢየሩሳሌምም ሕዝብ ሁሉ በእግዚአብሔር ፊት ወደቁ፤ ሰገዱም። 19 ከቀዓትና ከቆሬ ወገኖች ጥቂት ሌዋውያንም ቆመው፣ እጅግ ከፍ ባለ ድምፅ የእስራኤልን አምላክ እግዚአብሔርን አመሰገኑ። 20 በማግስቱም ጧት በማለዳ ተነሥተው ወደ ቴቁሔ ምድረ በዳ ሄዱ። መንገድ እንደ ጀመሩም ኢዮሣፍጥ ቆሞ፣ “ይሁዳና የኢየሩሳሌም ሕዝብ ሆይ፣ ስሙኝ! በአምላካችሁ በእግዚአብሔር እመኑ፤ ትጸኑማላችሁ። በነቢያቱም እመኑ፤ ይሳካላችሁማል” አላቸው። 21 ከሕዝቡም ጋራ ከተመካከረ በኋላ ከሰራዊቱ ፊት ቀድመው በመሄድ፣ “እግዚአብሔርን አመስግኑ፣ ፍቅሩ ለዘላለም ጸንቶ ይኖራልና” እያሉ ለእግዚአብሔር የሚዘምሩና ስለ ቅድስናውም ክብር የሚያወድሱ ሰዎችን መደበ። 22 መዘመርና ማወደስ እንደ ጀመሩም፣ እግዚአብሔር ይሁዳን በወረሩት በአሞን፣ በሞዓብና በሴይር ተራራ ሰዎች ላይ ድብቅ ጦር አመጣባቸው፤ ተሸነፉም። 23 የአሞንና የሞዓብ ሰዎችም የሴይርን ተራራ ሰዎች ለማጥፋትና ለመደምሰስ ተነሡባቸው። ከሴይር የመጡትን ሰዎች ካጠፉ በኋላም፣ እርስ በርስ ተጠፋፉ። 24 የይሁዳ ሰዎች ምድረ በዳውን ቍልቍል ወደሚያሳየው ቦታ መጥተው ግዙፉን ሰራዊት ሲመለከቱ፣ መሬቱ ሬሳ በሬሳ ሆኖ አዩ፤ አንድም ሰው አላመለጠም። 25 ኢዮሣፍጥና ሰዎቹም ምርኳቸውን ለማጋዝ ሄዱ፤ በዚያም መካከል እጅግ ብዙ መሣሪያና ልብስ፣ ሊሸከሙ ከሚችሉትም በላይ ውድ ዕቃዎችን አገኙ። ምርኮውም ከመብዛቱ የተነሣ ለመሰብሰብ ሦስት ቀን ፈጀ። 26 በአራተኛውም ቀን እግዚአብሔርን ባመሰገኑበት በበረከት ሸለቆ ተሰበሰቡ፤ ያም ስፍራ እስከ ዛሬ ድረስ የበረከት ሸለቆ ተብሎ የተጠራው ከዚህ የተነሣ ነው። 27 እግዚአብሔር በጠላቶቻቸው ላይ እንዲደሰቱ ስላደረጋቸው፣ የይሁዳና የኢየሩሳሌም ሰዎች ሁሉ በኢዮሣፍጥ እየተመሩ፣ በታላቅ ደስታ ወደ ኢየሩሳሌም ተመለሱ። 28 ወደ ኢየሩሳሌም ከተማ እንደ ገቡም በበገና፣ በመሰንቆና በመለከት ድምፅ ታጅበው ወደ እግዚአብሔር ቤተ መቅደስ አመሩ። 29 እግዚአብሔር የእስራኤልን ጠላቶች እንዴት እንደ ተዋጋቸው በሰሙ መንግሥታት ሁሉ ላይ ከእግዚአብሔር ዘንድ ፍርሀት ወደቀባቸው። 30 አምላኩ በየአቅጣጫው ዕረፍት ስለ ሰጠው፣ የኢዮሣፍጥ መንግሥት ሰላም አግኝቶ ነበር። የኢዮሣፍጥ ዘመነ መንግሥት ፍጻሜ 20፥31–21፥1 ተጓ ምብ – 1ነገ 22፥41-50 31 ኢዮሣፍጥ በይሁዳ ነገሠ። መንገሥ በጀመረ ጊዜም ዕድሜው ሠላሳ ዐምስት ዓመት ሲሆን፣ በኢየሩሳሌም ተቀምጦ ሃያ ዐምስት ዓመት ገዛ። እናቱም የሺልሒ ልጅ ዓዙባ ነበረች። 32 እርሱም በአካሄዱ ሁሉ የአባቱን የአሳን መንገድ ተከተለ፤ ከዚያም ፈቀቅ አላለም፤ በእግዚአብሔርም ፊት መልካም የሆነውን አደረገ፤ 33 ይሁን እንጂ በየኰረብታው ላይ ያሉት የማምለኪያ ስፍራዎች ገና አልተወገዱም፤ ሕዝቡም ገና ልቡን በአባቶቹ አምላክ ላይ አላደረገም ነበር። 34 የቀረውም ኢዮሣፍጥ በዘመነ መንግሥቱ ከመጀመሪያ እስከ መጨረሻው ያከናወናቸው ተግባራት፦ የአናኒ ልጅ ኢዩ በዘገበው የእስራኤል ነገሥታት የታሪክ መጽሐፍ ተመዝግቧል። 35 ከዚህ በኋላ የይሁዳ ንጉሥ ኢዮሣፍጥ ሥራው እጅግ ክፉ ከሆነው ከእስራኤል ንጉሥ ከአካዝያስ ጋራ የስምምነት ውል አደረገ፤ 36 ወደ ተርሴስ የሚሄዱ መርከቦችን ለመሥራትም ተስማሙ፤ መርከቦቹንም በዔጽዮንጋብር አሠሩ። 37 የመሪሳ ሰው የሆነው የዶዳያ ልጅ አልዓዛር በኢዮሣፍጥ ላይ፣ “ከአካዝያስ ጋራ የስምምነት ውል ስለ አደረግህ፣ እግዚአብሔር ሥራህን ያፈርሰዋል” ሲል ትንቢት ተናገረበት፤ መርከቦቹም ተሰበሩ፤ ለንግዱም ሥራ መሄድ አልቻሉም። |
መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™
የቅጂ መብት © 2001, 2024 በBiblica, Inc.
በፈቃድ የሚወሰድ። በዓለም ዐቀፍ ባለቤትነቱ።
The Holy Bible, New Amharic Standard Version™
Copyright © 2001, 2024 by Biblica, Inc.
Used with permission. All rights reserved worldwide.
Biblica, Inc.