Biblia Todo Logo
在线圣经

- 广告 -

2 ዜና መዋዕል 2 - አዲሱ መደበኛ ትርጒም


ቤተ መቅደሱን ለመሥራት የተደረገ ዝግጅት
2፥1-18 ተጓ ምብ – 1ነገ 5፥1-16

1 ሰሎሞን ለእግዚአብሔር ስም ቤተ መቅደስ፣ ለራሱም ቤተ መንግሥት እንዲሠራ አዘዘ።

2 እርሱም፣ የሚሸከሙ ሰባ ሺሕ፣ ከኰረብታ ላይ ድንጋይ የሚፈልጡ ሰማንያ ሺሕ ሰዎችና ሦስት ሺሕ ስድስት መቶ የሥራ ተቈጣጣሪዎች አሰማራ።

3 ከዚህ በኋላ፣ ሰሎሞን ለጢሮስ ንጉሥ ለኪራም የሚከተለውን ይህን መልእክት ላከ፤ “አባቴ ዳዊት የሚኖርበትን ቤተ መንግሥት ሲሠራ እንደ ላክህለት ሁሉ፣ ለእኔም የዝግባ ዕንጨት ላክልኝ።

4 ሽታው ደስ የሚያሰኝ ዕጣን በፊቱ የሚታጠንበትን፣ የተቀደሰ እንጀራ በየጊዜው የሚቀርብበትን፣ በየጧቱና በየማታው፣ በየሰንበቱና በየመባቻው እንዲሁም በተወሰኑት በአምላካችን በእግዚአብሔር በዓላት የሚቃጠል መሥዋዕት የሚቀርብበትን ቤተ መቅደስ ለአምላኬ ለእግዚአብሔር ስም ሠርቼ እቀድስ ዘንድ አስቤአለሁ። ይህም ለእስራኤል የዘላለም ሥርዐት ነው።

5 “አምላካችን ከሌሎች አማልክት ሁሉ ይበልጥ ታላቅ ስለ ሆነ፣ የምሠራውም ቤተ መቅደስ ታላቅ ይሆናል።

6 ነገር ግን ሰማይና ከሰማያት በላይ ያለው ሰማይ እንኳ እርሱን ይይዘው ዘንድ አይችልምና ቤተ መቅደስ ሊሠራለት የሚችል ማነው? በፊቱ ዕጣን የሚታጠንበትን እንጂ ቤተ መቅደስ እሠራለት ዘንድ እኔ ማን ነኝ?

7 “ስለዚህ አንተ በወርቅና በብር፣ በናስና በብረት፣ በሐምራዊና በደማቅ ቀይ፣ በሰማያዊም ግምጃ ሥራ ዕውቀት ያለውን እንዲሁም አባቴ ዳዊት ካዘጋጃቸው ከእኔ የእጅ ባለሙያዎች ጋራ በይሁዳና በኢየሩሳሌም የቅርጻ ቅርጽ ጥበብ ሥራ የሚሠራ ሰው ላክልኝ።

8 “ሰዎችህ ከሊባኖስ ዕንጨት በመቍረጥ ሥራ ዐዋቂዎች መሆናቸውን ስለማውቅ፣ ከሊባኖስ የዝግባ፣ የጥድና የሰንደል ዕንጨትም ላክልኝ፤ ሰዎቼም ከሰዎችህ ጋራ ዐብረው ይሠራሉ።

9 የምሠራው ቤተ መቅደስ ትልቅና እጅግ ውብ መሆን ስላለበት፣ ብዙ ጠርብ ያዘጋጁልኛልና።

10 ዕንጨቱን ለሚቈርጡ አገልጋዮችህ ሃያ ሺሕ የቆሮስ መስፈሪያ ስንዴ ዱቄት፣ ሃያ ሺሕ የቆሮስ መስፈሪያ ገብስ፣ ሃያ ሺሕ የባዶስ መስፈሪያ ወይን ጠጅና ሃያ ሺሕ የባዶስ መስፈሪያ ዘይት እሰጣለሁ።”

11 የጢሮስ ንጉሥ ኪራምም ለሰሎሞን እንዲህ ሲል በደብዳቤ መለሰለት፤ “እግዚአብሔር ሕዝቡን ስለሚወድድ አንተን በእነርሱ ላይ አነገሠህ።”

12 ኪራምም በመቀጠል እንዲህ አለ፤ “ሰማይንና ምድርን የፈጠረ የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር ይባረክ! ለእግዚአብሔር ቤተ መቅደስን፣ ለራሱም ቤተ መንግሥትን የሚሠራ፣ ብልኅነትንና ማስተዋልን የተሞላ ጥበበኛ ልጅ ለንጉሥ ዳዊት ሰጥቷልና።

13 “እጅግ ብልኀተኛ የሆነውን ኪራም አቢን ልኬልሃለሁ፤

14 እርሱም እናቱ ከዳን ወገን፣ አባቱም የጢሮስ አገር ሰው ነው፤ በወርቅና በብር፣ በናስና በብረት፣ በድንጋይና በዕንጨት፤ እንዲሁም በሐምራዊና በሰማያዊ፣ በቀይ ግምጃና በቀጭን በፍታ ሥራ የሠለጠነ ሲሆን፣ በልዩ ልዩ ቅርጻ ቅርጽ ሥራ ልምድ ያካበተና የተሰጠውን ማንኛውንም ንድፍ በሥራ መተርጐም የሚችል ባለሙያ ነው። እርሱም ከአንተ የእጅ ሥራ ባለሙያዎችና ከጌታዬ ከዳዊት የእጅ ሥራ ባለሙያዎች ጋራ ዐብሮ ይሠራል።

15 “አሁንም ጌታዬ በሰጠው ተስፋ መሠረት ስንዴውንና ገብሱን፣ የወይራ ዘይቱንና የወይን ጠጁን ለአገልጋዮቹ ይላክ፤

16 እኛም የሚያስፈልግህን ግንድ ሁሉ ከሊባኖስ ቈርጠንና አስረን እስከ ኢዮጴ ድረስ ቍልቍል በማንሳፈፍ እንሰድድልሃለን፤ አንተም ወደ ኢየሩሳሌም ታስወስደዋለህ።”

17 ሰሎሞን አባቱ ዳዊት ካደረገው ቈጠራ በኋላ፣ በእስራኤል ምድር የነበሩትን መጻተኞች ሁሉ ቈጠረ፤ ቍጥራቸውም አንድ መቶ ዐምሳ ሦስት ሺሕ ስድስት መቶ ሆነ።

18 ከእነዚህም ሰባ ሺሑን ተሸካሚዎች፣ ሰማንያ ሺሑን በኰረብታው ላይ ድንጋይ ፈላጮች፣ ሦስት ሺሕ ስድስት መቶውን ደግሞ የሥራው ተቈጣጣሪዎች ሆነው ሰዎቹን እንዲያሠሩ መደበ።

መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™

የቅጂ መብት © 2001, 2024 በBiblica, Inc.

በፈቃድ የሚወሰድ። በዓለም ዐቀፍ ባለቤትነቱ።

The Holy Bible, New Amharic Standard Version™

Copyright © 2001, 2024 by Biblica, Inc.

Used with permission. All rights reserved worldwide. 

Biblica, Inc.
跟着我们:



广告