2 ዜና መዋዕል 19 - አዲሱ መደበኛ ትርጒም1 የይሁዳ ንጉሥ ኢዮሣፍጥ ኢየሩሳሌም ወዳለው ቤተ መንግሥቱ በደኅና በተመለሰ ጊዜ፣ 2 ባለራእዩ የአናኒ ልጅ ኢዩ ሊገናኘው ወጣ፤ ንጉሥ ኢዮሣፍጥንም እንዲህ አለው፣ “አንተ ክፉውን መርዳትህና እግዚአብሔርን የሚጠሉትን ማፍቀርህ ተገቢ ነውን? ስለዚህ የእግዚአብሔር ቍጣ ባንተ ላይ ነው፤ 3 ይሁን እንጂ የአሼራን ዐምዶች ከምድሪቱ ስላስወገድህና እግዚአብሔርን ለመፈለግ ልብህን ስላዘጋጀህ፣ መልካም ነገር ተገኝቶብሃል”። ኢዮሣፍጥ ዳኞችን ሾመ 4 ኢዮሣፍጥ በኢየሩሳሌም ተቀመጠ፤ ከቤርሳቤህ እስከ ኰረብታማው አገር እስከ ኤፍሬም ድረስ እንደ ገና በመውጣት ወደ ሕዝቡ መካከል ገብቶ ወደ አባቶቻቸው አምላክ ወደ እግዚአብሔር መለሳቸው። 5 በምድሪቱም ላይ በተመሸጉት የይሁዳ ከተሞች ሁሉ ዳኞችን ሾመ፤ 6 እንዲህም አላቸው፤ “እናንተ የምትፈርዱት ለሰው ሳይሆን፣ ፍርድ በምትሰጡበት ጊዜ ሁሉ ከእናንተ ጋራ ለሆነው ለእግዚአብሔር ስለ ሆነ፣ በምትሰጡት ውሳኔ ሁሉ ብርቱ ጥንቃቄ አድርጉ፤ 7 አሁንም እግዚአብሔርን መፍራት በእናንተ ላይ ይሁን፤ በአምላካችን በእግዚአብሔር ዘንድ ፍርድ ማጣመም፣ አድልዎ ማድረግና መማለጃ መቀበል ስለሌለ ተጠንቅቃችሁ ፍረዱ።” 8 ኢዮሣፍጥም በኢየሩሳሌም የእግዚአብሔርን ሕግ እንዲያስፈጽሙና ለሚነሡ ክርክሮችም እልባት እንዲሰጡ ከሌዋውያን፣ ከካህናትና ከእስራኤል ቤት አለቆች ጥቂት ሰዎች ሾመ፤ እነርሱም መኖሪያቸው በኢየሩሳሌም ሆነ። 9 እነርሱንም እንዲህ ብሎ አዘዛቸው፤ “እግዚአብሔርን በመፍራት፣ በታማኝነትና በፍጹም ልብ አገልግሉ። 10 በየከተማው ከሚኖሩት ወገኖቻችሁ ስለ ደም መፋሰስ ወይም ሕግን፣ ትእዛዞችን፣ ደንብንና ሥርዐትን ስለ መተላለፍ በሚቀርብላችሁ በማናቸውም ጕዳይ እግዚአብሔርን እንዳይበድሉ አስጠንቅቋቸው፤ አለዚያ ግን ቍጣው በእናንተና በወንድሞቻችሁ ላይ ይመጣል፤ ይህን ብታደርጉ በደለኞች አትሆኑም። 11 “የእግዚአብሔር በሆነው ነገር ሁሉ ላይ የካህናቱ አለቃ አማርያ፣ የንጉሡ በሆነው ነገር ሁሉ ላይ የይሁዳ ነገድ መሪ የሆነው የእስማኤል ልጅ ዝባድያ በላያችሁ ተሾመዋል፤ ሌዋውያኑ ደግሞ በፊታችሁ አለቆች ሆነው ያገለግላሉ፤ በርትታችሁ ሥሩ፤ እግዚአብሔርም መልካም ከሚያደርጉ ጋራ ይሁን።” |
መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™
የቅጂ መብት © 2001, 2024 በBiblica, Inc.
በፈቃድ የሚወሰድ። በዓለም ዐቀፍ ባለቤትነቱ።
The Holy Bible, New Amharic Standard Version™
Copyright © 2001, 2024 by Biblica, Inc.
Used with permission. All rights reserved worldwide.
Biblica, Inc.