Biblia Todo Logo
在线圣经

- 广告 -

2 ዜና መዋዕል 18 - አዲሱ መደበኛ ትርጒም


ሚካያ በአክዓብ ላይ ትንቢት ተናገረ
18፥1-27 ተጓ ምብ – 1ነገ 22፥1-28

1 ኢዮሣፍጥ ታላቅ ሀብትና ክብር ባገኘ ጊዜ፣ ከአክዓብ ጋራ በጋብቻ ተሳሰረ።

2 ከጥቂት ዓመታት በኋላም አክዓብን ሊጐበኝ ወደ ሰማርያ ወረደ። አክዓብም ለርሱና ዐብሮት ለነበረው ሕዝብ ብዙ በግና በሬ ዐረደ፤ ከዚያም በራሞት ገለዓድ ላይ አደጋ እንዲጥል አግባባው።

3 የእስራኤል ንጉሥ አክዓብም የይሁዳን ንጉሥ ኢዮሣፍጥን፣ “ራሞት ገለዓድን ለመውጋት ዐብረኸኝ ትሄዳለህን?” ሲል ጠየቀው። ኢዮሣፍጥም፣ “እኔ እንደ አንተው ነኝ፤ ሕዝቤም እንደ ሕዝብህ ነው፤ በጦርነቱ ዐብረናችሁ እንሰለፋለን” አለው።

4 ደግሞም ኢዮሣፍጥ የእስራኤልን ንጉሥ፣ “በመጀመሪያ ግን የእግዚአብሔርን ሐሳብ ጠይቅ” አለው።

5 ስለዚህ የእስራኤል ንጉሥ አራት መቶ ነቢያትን በአንድነት ሰብስቦ፣ “በገለዓድ በምትገኘው ራሞት ላይ እንዝመት ወይስ እንቅር?” ሲል ጠየቃቸው። እነርሱም፣ “እግዚአብሔር በንጉሡ እጅ አሳልፎ ይሰጣታልና ዝመትባት” አሉት።

6 ኢዮሣፍጥ ግን፣ “እንጠይቀው ዘንድ ሌላ የእግዚአብሔር ነቢይ እዚህ የለምን?” አለ።

7 የእስራኤልም ንጉሥ ለኢዮሣፍጥ፣ “መኖሩንማ በርሱ አማካይነት የእግዚአብሔርን ፈቃድ የምንጠይቀው አንድ ነቢይ አሁንም አለ፤ ነገር ግን ምን ጊዜም ስለ እኔ ክፉ እንጂ መልካም ትንቢት ተናግሮ ስለማያውቅ እጠላዋለሁ፤ እርሱም የይምላ ልጅ ሚክያስ ነው” አለ። ኢዮሣፍጥም፣ “ንጉሡ እንዲህ ማለት አይገባውም” አለው።

8 ስለዚህ የእስራኤል ንጉሥ ከሹማምቱ አንዱን ጠርቶ “የይምላን ልጅ ሚክያስን በፍጥነት አምጣው” አለው።

9 የእስራኤል ንጉሥና የይሁዳ ንጉሥ ኢዮሣፍጥ አልባሰ መንግሥታቸውን ለብሰው፣ በሰማርያ ቅጥር በር መግቢያ አጠገብ ባለው ዐውድማ ላይ በየዙፋናቸው ተቀምጠው፣ ነቢያቱ ሁሉ በፊታቸው ትንቢት ይናገሩ ነበር።

10 በዚህ ጊዜ፣ የክንዓና ልጅ ሴዴቅያስ የብረት ቀንዶች ሠርቶ፣ “እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ ‘ሶርያውያን እስኪጠፉ ድረስ በእነዚህ ትወጋቸዋለህ’ ” አለ።

11 የቀሩትም ነቢያት ሁሉ፣ “እግዚአብሔር በንጉሡ እጅ አሳልፎ ይሰጣታልና፣ በገለዓድ በምትገኘው ራሞት ላይ ዝመትባት” በማለት ተመሳሳይ ትንቢት ይናገሩ ነበር።

12 ሚክያስን ሊጠራ ሄዶ የነበረውም መልእክተኛ፣ “እነሆ፣ ሌሎቹ ነቢያት በአንድ አፍ ሆነው፣ ለንጉሡ መልካምን ነገር እየተነበዩ ነው፤ እባክህ የአንተም ቃል እንደ ቃላቸው ይሁን፤ ንጉሡን ደስ የሚያሠኘውን ተናገር” አለው።

13 ሚክያስ ግን፣ “ሕያው እግዚአብሔርን! አምላኬ የሚለውን ብቻ እነግረዋለሁ” አለ።

14 ወደ ንጉሡ በመጣ ጊዜ ንጉሡ፣ “ሚክያስ ሆይ፤ በገለዓድ በምትገኘው ራሞት ላይ እንዝመት ወይስ እንቅር?” ሲል ጠየቀው። እርሱም መልሶ፣ “ሂዱና ድል አድርጉ፤ በእጃችሁ ዐልፈው ይሰጣሉና” አለው።

15 ንጉሡም፣ “ከእውነት በቀር ምንም ነገር በእግዚአብሔር ስም እንዳትነግረኝ የማምልህ ስንት ጊዜ ነው?” አለው።

16 ከዚያም ሚክያስ፣ “እስራኤል ሁሉ እረኛ እንደሌላቸው በጎች በተራሮች ላይ ተበታትነው አየሁ፤ እግዚአብሔርም፣ ‘እነዚህ ሰዎች ጌታ የላቸውም፤ እያንዳንዱም በሰላም ወደየቤቱ ይመለስ’ ብሏል” ሲል መለሰ።

17 የእስራኤልም ንጉሥ ኢዮሣፍጥን፣ “ስለ እኔ ክፉ ብቻ እንጂ፣ መልካም ትንቢት አይናገርም አላልሁህምን?” አለው።

18 ከዚያም ሚክያስ እንዲህ አለ፤ “እንግዲህ የእግዚአብሔርን ቃል ስማ፤ እግዚአብሔር በዙፋኑ ላይ ተቀምጦ፣ የሰማይም ሰራዊት ሁሉ በቀኙና በግራው ቆመው አየሁ።

19 እግዚአብሔርም፣ ‘የእስራኤል ንጉሥ አክዓብ በገለዓድ በምትገኘው ራሞት ላይ ዘምቶ እዚያው እንዲሞት ማን ያሳስተው?’ አለ። “አንዱ አንድ ሐሳብ፣ ሌላውም ሌላ ሐሳብ አቀረበ።

20 ከዚያም አንድ መንፈስ መጥቶ፣ በእግዚአብሔር ፊት በመቆም፣ ‘እኔ አሳስተዋለሁ’ አለ። “እግዚአብሔርም፣ ‘እንዴት አድርገህ?’ ሲል ጠየቀው።

21 “እርሱም፣ ‘እኔ እወጣና በገዛ ነቢያቱ ሁሉ አፍ የሐሰት መንፈስ እሆናለሁ’ አለ። “እግዚአብሔርም፣ ‘ታሳስተዋለህ፤ ይሳካልሃልም፤ እንግዲህ ውጣና አድርግ፤’ አለው።

22 “ስለዚህ እነሆ፣ እግዚአብሔር በእነዚህ ነቢያትህ አፍ የሐሰት መንፈስ አኖረ፤ እግዚአብሔርም ጥፋት እንደሚያመጣብህ ተናግሯል”።

23 ከዚያም የክንዓና ልጅ ሴዴቅያስ ወጥቶ ሚክያስን በጥፊ መታውና፣ “ለመሆኑ የእግዚአብሔር መንፈስ በየት በኩል ዐልፎኝ ነው አንተን ያናገረህ?” አለው።

24 ሚክያስም፣ “ለመሸሸግ ወደ እልፍኝህ በምትሄድበት በዚያ ዕለት ታገኘዋለህ” አለው።

25 ከዚያም የእስራኤል ንጉሥ እንዲህ ሲል አዘዘ፤ “ሚክያስን ይዛችሁ ወደ ከተማዪቱ ገዥ ወደ አሞንና ወደ ንጉሡ ልጅ ወደ ኢዮአስ መልሱት፤

26 ከዚያም፣ ‘ንጉሡ፣ ይህን ሰው እስር ቤት አስገቡት፤ በደኅና እስክመለስም ድረስ፣ ከደረቅ እንጀራና ከውሃ በቀር ሌላ እንዳትሰጡት’ ብሏል በሏቸው” አለ።

27 ሚክያስም፣ “አንተ በደኅና ከተመለስክማ እግዚአብሔር በእኔ አልተናገረም ማለት ነው!” አለ፤ ቀጥሎም፣ “እናንተ ሰዎች ሁላችሁ ስሙኝ” አለ።


አክዓብ በሬማት ገለዓድ ተገደለ
18፥28-34 ተጓ ምብ – 1ነገ 22፥29-36

28 ስለዚህ የእስራኤል ንጉሥና የይሁዳ ንጉሥ ኢዮሣፍጥ ወደ ራሞት ገለዓድ ወጡ።

29 የእስራኤልም ንጉሥ ኢዮሣፍጥን፣ “እኔ ልብሴን ለውጬ ወደ ጦርነቱ እገባለሁ፤ አንተ ግን ልብሰ መንግሥትህን ልበስ” አለው። ስለዚህ የእስራኤል ንጉሥ ልብሱን ለውጦ ሌላ ሰው መስሎ ወደ ጦርነቱ ገቡ።

30 በዚህ ጊዜ የሶርያ ንጉሥ የሠረገላ አዛዦቹን፣ “ከእስራኤል ንጉሥ በቀር፣ ትንሽም ሆነ ትልቅ ከሌላ ከማንም ጋራ እንዳትዋጉ” ብሎ አዝዟቸው ነበር።

31 የሠረገላው አዛዦችም ኢዮሣፍጥን ባዩ ጊዜ፣ “የእስራኤል ንጉሥ ይህ ነው” ብለው አሰቡ፤ ሊወጉትም ከበቡት፤ ኢዮሣፍጥ ግን ጮኸ፤ እግዚአብሔርም ረዳው፤ አምላክም ከርሱ መለሳቸው፤

32 የሠረገላ አዛዦቹም የእስራኤል ንጉሥ አለመሆኑን በተረዱ ጊዜ እርሱን ከማሳደድ ተመለሱ።

33 ይሁን እንጂ አንዱ ቀስቱን በነሲብ ቢያስፈነጥረው፣ በጥሩሩ መጋጠሚያዎች መካከል ዐልፎ የእስራኤልን ንጉሥ ወጋው። ንጉሡም ሠረገላ ነጂውን “ተመለስና ከጦርነቱ አውጣኝ፤ ቈስያለሁና” አለው።

34 ጦርነቱም ቀኑን ሙሉ ተፋፍሞ ዋለ፤ በዚህ ጊዜ የእስራኤል ንጉሥ በሶርያውያን ፊት ለፊት በሠረገላው ላይ እስከ ምሽት ድረስ ተደግፎ ነበር፤ ፀሓይ ስትጠልቅም ሞተ።

መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™

የቅጂ መብት © 2001, 2024 በBiblica, Inc.

በፈቃድ የሚወሰድ። በዓለም ዐቀፍ ባለቤትነቱ።

The Holy Bible, New Amharic Standard Version™

Copyright © 2001, 2024 by Biblica, Inc.

Used with permission. All rights reserved worldwide. 

Biblica, Inc.
跟着我们:



广告