Biblia Todo Logo
在线圣经

- 广告 -

2 ዜና መዋዕል 17 - አዲሱ መደበኛ ትርጒም


የይሁዳ ንጉሥ ኢዮሣፍጥ

1 ልጁ ኢዮሣፍጥ በርሱ ፈንታ ነገሠ፤ በእስራኤል ላይ በረታ።

2 እርሱም በተመሸጉት የይሁዳ ከተሞች ሁሉ ውስጥ ወታደር አኖረ፤ እንዲሁም በይሁዳ ምድርና አባቱ አሳ በያዛቸው በኤፍሬም መንደሮች ዘበኞች አስቀመጠ።

3 በለጋነት ዕድሜው አባቱ ዳዊት በሄደበት መንገድ ስለ ሄደ፣ እግዚአብሔር ከኢዮሣፍጥ ጋራ ነበር፤ የበኣልንም አማልክት አልጠየቀም፤

4 ነገር ግን ከእስራኤል ድርጊት ይልቅ፣ የአባቱን ፈለገ፤ ትእዛዞቹንም ተከተለ።

5 እግዚአብሔርም መንግሥቱን በእጁ አጸናለት፤ መላው ይሁዳም ስጦታ ለኢዮሣፍጥ አመጣለት፤ ከዚህ የተነሣም ታላቅ ብልጽግናና ክብር አገኘ።

6 ልቡም በእግዚአብሔር መንገድ የጸና ነበር፤ እንደዚሁም ማምለኪያ ኰረብቶችንና የአሼራ ዐምዶችን ከይሁዳ አስወገደ።

7 በነገሠ በሦስተኛው ዓመት፣ በይሁዳ ከተሞች ያስተምሩ ዘንድ ሹማምቱን፣ ማለትም ቤን ኀይልን፣ አብድያስን፣ ዘካርያስን፣ ናትናኤልንና ሚክያስን ላካቸው።

8 ከእነዚህም ጋራ ጥቂት ሌዋውያን ነበሩ፤ ስማቸውም፦ ሸማያ፣ ነታንያ፣ ዝባድያ፣ አሣሄል፣ ሰሚራሞት፣ ዮናታን፣ አዶንያስ፣ ጦብያና ጦባዶንያ ነበር። ካህናቱ ደግሞ ኤሊሳማና ኢዮራም ነበሩ።

9 እነርሱም የእግዚአብሔርን የሕጉን መጽሐፍ ይዘው በመሄድ በይሁዳ ሁሉ ላለው ሕዝብ አስተማሩ፤ በይሁዳ ከተሞች ሁሉ በመዘዋወርም ሕዝቡን አስተማሩ።

10 በይሁዳ ዙሪያ ባሉ ነገሥታት ሁሉ ላይ ከእግዚአብሔር ዘንድ ፍርሀት ስለ ወደቀባቸው ኢዮሣፍጥን አልተዋጉትም።

11 ከፍልስጥኤማውያንም አንዳንዶቹ ለኢዮሣፍጥ እጅ መንሻ አመጡለት፤ ጥሬ ብርም ገበሩለት፤ ዐረቦችም ሰባት ሺሕ ሰባት መቶ አውራ በግና ሰባት ሺሕ ሰባት መቶ አውራ ፍየል መንጋ አመጡለት።

12 ኢዮሣፍጥም እያየለ ሄደ፤ በይሁዳም ምሽጎችና የዕቃ ማከማቻ ከተሞች ሠራ።

13 በይሁዳም ከተሞች እጅግ ብዙ ስንቅና ትጥቅ ነበረው። ደግሞም በቂ ልምድ ያላቸውን ተዋጊዎች በኢየሩሳሌም አስቀመጠ።

14 እነርሱም በየቤተ ሰቦቻቸው ሲመዘገቡ እንደሚከተለው ነው፤ ከይሁዳ የየሻለቃው አዛዦች፣ አዛዡ ዓድና ከሦስት መቶ ሺሕ ተዋጊዎች ጋራ፤

15 ከርሱ ቀጥሎም አዛዡ ይሆሐናን ከሁለት መቶ ሰማንያ ሺሕ ጋራ፤

16 ከዚያ ቀጥሎም ለእግዚአብሔር አገልግሎት በፈቃደኛነት ራሱን የሰጠው የዝክሪ ልጅ ዓማስያ ከሁለት መቶ ሺሕ ተዋጊዎች ጋራ፤

17 ከብንያምም ጀግናው ወታደር ኤሊዳሄ ቀስትና ጋሻ ከያዙ ከሁለት መቶ ሺሕ ሰዎች ጋራ፤

18 ቀጥሎም ዮዛባት ለጦርነት ዝግጁ ከሆኑ ከአንድ መቶ ሰማንያ ሺሕ ሰዎች ጋራ።

19 እነዚህ እንግዲህ በመላው ይሁዳ በተመሸጉት ከተሞች ካስቀመጣቸው ሌላ፣ ንጉሡን ያገለግሉ የነበሩ ሰዎች ናቸው።

መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™

የቅጂ መብት © 2001, 2024 በBiblica, Inc.

በፈቃድ የሚወሰድ። በዓለም ዐቀፍ ባለቤትነቱ።

The Holy Bible, New Amharic Standard Version™

Copyright © 2001, 2024 by Biblica, Inc.

Used with permission. All rights reserved worldwide. 

Biblica, Inc.
跟着我们:



广告