2 ዜና መዋዕል 11 - አዲሱ መደበኛ ትርጒም1 ሮብዓም ኢየሩሳሌም በደረሰ ጊዜ፣ የእስራኤልን ቤት ወግተው መንግሥቱን ወደ ሮብዓም እንዲመልሱ ከይሁዳና ከብንያም ቤት አንድ መቶ ሰማንያ ሺሕ ወታደሮች ሰበሰበ። 2 ነገር ግን የእግዚአብሔር ቃል ወደ እግዚአብሔር ሰው ወደ ሸማያ እንዲህ ሲል መጣ፤ 3 “ለይሁዳ ንጉሥ ለሰሎሞን ልጅ ለሮብዓም፤ ለመላው እስራኤል፣ ለይሁዳና ለብንያም ለቀረውም ሕዝብ ሁሉ እንዲህ በል፤ 4 ‘እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ ይህ ነገር ከእኔ የሆነ ነውና፣ ወንድሞቻችሁን ለመውጋት ወደዚያ አትውጡ፤ እያንዳንዳችሁም ወደየቤታችሁ ተመለሱ’ ” አላቸው። ስለዚህ ለእግዚአብሔር ቃል በመታዘዝ በኢዮርብዓም ላይ መዝመቱን ትተው ተመለሱ። ሮብዓም የይሁዳን ከተሞች መሸገ 5 ሮብዓም መኖሪያውን በኢየሩሳሌም በማድረግ ለመከላከያ የሚሆኑ ከተሞችን በይሁዳ ሠራ፤ እነዚህም 6 ቤተ ልሔም፣ ኤጣም፣ ቴቁሔ፣ 7 ቤትጹር፣ ሦኮን፣ ዓዶላም፣ 8 ጋት፣ መሪሳ፣ ዚፍ፣ 9 አዶራይም፣ ለኪሶ፣ ዓዜቃ፣ 10 ጾርዓ፣ ኤሎን፣ ኬብሮን ናቸው። በይሁዳና በብንያም ውስጥ የተመሸጉት ከተሞች እነዚህ ነበሩ። 11 እነዚህንም ምሽጎቻቸውን አጠንክሮ፣ አዛዦችን ሾመባቸው፤ ምግብ፣ ዘይትና የወይን ጠጅ አከማቸባቸው። 12 በየከተሞቹም ሁሉ ጋሻና ጦር አከማችቶ ይበልጥ አጠናከራቸው። በዚህ ዐይነት ይሁዳንና ብንያምን የራሱ አደረገ። 13 በመላው እስራኤል ያሉት ካህናትና ሌዋውያን ከየክልላቸው ሁሉ ወደ እርሱ ተሰበሰቡ። 14 ኢዮርብዓምና ልጆቹ ሌዋውያኑን ከእግዚአብሔር የክህነት አገልግሎት ስላባረሯቸው ሌዋውያኑ ማሰማሪያ ቦታቸውንና ንብረታቸውን ሁሉ ትተው ወደ ይሁዳና ወደ ኢየሩሳሌም መጡ፤ 15 እርሱም ለየኰረብታው መስገጃ እንዲሁም ለሠራቸው የፍየልና የጥጃ ምስሎች የራሱን ካህናት ሾመ። 16 ከእያንዳንዱም የእስራኤል ነገድ ከልባቸው የእስራኤልን አምላክ እግዚአብሔርን የሚፈልጉ ሁሉ፣ ለአባቶቻቸው አምላክ ለእግዚአብሔር መሥዋዕት ያቀርቡ ዘንድ፣ ሌዋውያኑን ተከትለው ወደ ኢየሩሳሌም ሄዱ። 17 በዚሁ ሁኔታ የዳዊትንና የሰሎሞንን መንገድ በመከተል፣ ለሦስት ዓመት የይሁዳን መንግሥት አበረቱ፤ የሰሎሞንን ልጅ ሮብዓምንም ረዱ። የሮብዓም ቤተ ሰብ 18 ሮብዓም መሐላትን አገባ፤ አባቷ የዳዊት ልጅ ኢያሪሙት ሲሆን፣ እናቷም አቢካኢል የተባለች፣ የእሴይ የልጅ ልጅ የኤልያብ ልጅ ነበረች። 19 እርሷም የዑስ፣ ሰማርያና ዛሃም የተባሉ ወንዶች ልጆች ወለደችለት። 20 ከዚያም የአቤሴሎምን ልጅ መዓካን አገባ፤ እርሷም አብያ፣ ዓታይ፣ ዚዛ፣ ሰሎሚት የተባሉትን ወለደችለት። 21 ሮብዓም መዓካን የአቤሴሎምን ሴት ልጅ ከሌሎቹ ሚስቶቹና ቁባቶቹ ይልቅ አብልጦ ወደዳት። በአጠቃላይ ዐሥራ ስምንት ሚስትና ስድሳ ቁባት፣ ሃያ ስምንት ወንድና ስድሳ ሴት ልጆች ነበሩት። 22 ሮብዓም የመዓካን ልጅ አብያን ሊያነግሠው ስለ ፈለገ ከልዑላን ወንድሞቹ አልቆ ዋና አደረገው። 23 ከወንዶች ልጆቹም ጥቂቱን በይሁዳና በብንያም አውራጃዎች እንዲሁም በተመሸጉት ከተሞች ስለ ሾማቸው፣ ዘዴኛነቱን አሳይቷል። የሚያስፈልጋቸውን በብዛት ሰጣቸው፤ ብዙ ሚስቶችም አጋባቸው። |
መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™
የቅጂ መብት © 2001, 2024 በBiblica, Inc.
በፈቃድ የሚወሰድ። በዓለም ዐቀፍ ባለቤትነቱ።
The Holy Bible, New Amharic Standard Version™
Copyright © 2001, 2024 by Biblica, Inc.
Used with permission. All rights reserved worldwide.
Biblica, Inc.