Biblia Todo Logo
在线圣经

- 广告 -

2 ዜና መዋዕል 10 - አዲሱ መደበኛ ትርጒም


እስራኤል በሮብዓም ላይ ዐመፀ
10፥1–11፥4 ተጓ ምብ – 1ነገ 12፥1-24

1 እስራኤላውያን ሁሉ ሊያነግሡት ወደ ሴኬም መጥተው ስለ ነበር፣ ሮብዓም ወደ ሴኬም ሄደ።

2 ከንጉሥ ሰሎሞን ሸሽቶ በግብጽ ይኖር የነበረው የናባጥ ልጅ ኢዮርብዓም ይህን ሲሰማ፣ ከግብጽ ተመልሶ መጣ።

3 ኢዮርብዓምንም ልከው አስጠሩት፤ ከዚያም እርሱና እስራኤል ሁሉ ወደ ሮብዓም ሄደው እንዲህ አሉት፤

4 “አባትህ ቀንበራችንን አከበደብን፤ አንተ ግን አስጨናቂውን ሥራና በላያችን የጫነብንን ከባድ ቀንበር አቅልልልን፤ እኛም እንገዛልሃለን።”

5 ሮብዓምም፣ “ከሦስት ቀን በኋላ ተመልሳችሁ ወደ እኔ ኑ” አላቸው፤ ስለዚህ ሰዎቹ ወጥተው ሄዱ።

6 ከዚያም ንጉሡ ሮብዓም አባቱ ሰሎሞን በሕይወቱ ሳለ ካገለገሉት ሽማግሌዎች ጋራ ተማከረ፤ “ለዚህ ሕዝብ ምን መልስ እንድሰጥ ትመክሩኛላችሁ?” አላቸው።

7 እነርሱም፣ “ለዚህ ሕዝብ ደግ ከሆንህለት፣ ደስ ካሠኘኸውና የሚስማማውን መልስ ከሰጠኸው ምን ጊዜም አገልጋይህ ይሆናል” ብለው መለሱለት።

8 ሮብዓም ግን ሽማግሌዎች የሰጡትን ምክር ንቆ፣ ዐብሮ አደጎቹና አገልጋዮቹ ከሆኑት ወጣቶች ምክር ጠየቀ፤

9 እንዲህም አላቸው፤ “ ‘አባትህ የጫነብንን ቀንበር አቅልልልን’ ለሚሉኝ ለእነዚህ ሰዎች የምትሰጡኝ ምክር ምንድን ነው? ምንስ ብለን እንመልስላቸው?”

10 ዐብሮ አደጎቹም ወጣቶች እንዲህ አሉት፤ “ ‘አባትህ በላያችን ከባድ ቀንበር ጫነብን፤ አንተ ግን ቀንበራችንን አቅልልልን’ ለሚሉህ እንዲህ በላቸው፤ ‘ትንሿ ጣቴ ከአባቴ ወገብ ይልቅ ትወፍራለች፤

11 አባቴ ከባድ ቀንበር ጫነባችሁ፤ እኔ ግን የባሰ አከብደዋለሁ፤ አባቴ በዐለንጋ ገረፋችሁ፤ እኔ ግን በጊንጥ እገርፋችኋለሁ።’ ”

12 ንጉሡ፣ “በሦስተኛው ቀን ተመልሳችሁ ኑ” ባላቸው መሠረት፣ ኢዮርብዓምና ሕዝቡ ሁሉ በሦስተኛው ቀን ወደ ሮብዓም ተመልሰው መጡ።

13 ንጉሡ ሮብዓምም በሽማግሌዎቹ የተሰጠውን ምክር ንቆ ሕዝቡን የሚያስከፋ መልስ ሰጣቸው፤

14 እርሱም ወጣቶቹ በሰጡት ምክር መሠረት፣ “አባቴ ቀንበራችሁን አከበደባችሁ፤ እኔ ደግሞ የባሰ አከብደዋለሁ፤ አባቴ በዐለንጋ ገረፋችሁ፤ እኔ ደግሞ በጊንጥ እገርፋችኋለሁ” አላቸው።

15 እግዚአብሔር በሴሎናዊው በአኪያ አማካይነት ለናባጥ ልጅ ለኢዮርብዓም የተናገረው ቃል ይፈጸም ዘንድ፣ ስለ ወሰነ፣ ንጉሡ ሕዝቡን አላዳመጠም።

16 መላው እስራኤልም ንጉሡ ሊሰማቸው አለመፈለጉን በተረዱ ጊዜ፣ እንዲህ ሲሉ መለሱለት፤ “ከዳዊት ምን ድርሻ አለን? ከእሴይስ ልጅ ምን ክፍል አለን? እስራኤል፣ ሆይ፤ ወደ ድንኳንህ ተመለስ፤ ዳዊት ሆይ፤ አንተም የገዛ ቤትህን ጠብቅ።” ስለዚህ እስራኤላውያን ሁሉ ወደ የቤታቸው ተመለሱ።

17 ይሁን እንጂ ሮብዓምም በይሁዳ ከተሞች በሚኖሩት እስራኤላውያን ላይ ነገሠ።

18 ንጉሥ ሮብዓም የጕልበት ሠራተኞች አለቃ የነበረውን አዶኒራምን ላከው፤ ነገር ግን እስራኤላውያን በድንጋይ ወግረው ገደሉት። ንጉሡ ሮብዓም ግን እንደ ምንም ብሎ ሠረገላው ላይ በመውጣት ወደ ኢየሩሳሌም ሸሸ።

19 ስለዚህ እስራኤል እስከ ዛሬ ድረስ በዳዊት ቤት ላይ እንዳመፀ ነው።

መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™

የቅጂ መብት © 2001, 2024 በBiblica, Inc.

በፈቃድ የሚወሰድ። በዓለም ዐቀፍ ባለቤትነቱ።

The Holy Bible, New Amharic Standard Version™

Copyright © 2001, 2024 by Biblica, Inc.

Used with permission. All rights reserved worldwide. 

Biblica, Inc.
跟着我们:



广告