2 ዜና መዋዕል 1 - አዲሱ መደበኛ ትርጒምሰሎሞን ጥበብ እንዲሰጠው ጠየቀ 1፥14-17 ተጓ ምብ – 1ነገ 10፥26-29 ፤ 2ዜና 9፥25-28 1 አምላኩ እግዚአብሔር ከርሱ ጋራ ስለ ነበር፣ እጅግም ስላገነነው፣ የዳዊት ልጅ ሰሎሞን በመንግሥቱ ላይ ተደላድሎ ተቀመጠ። 2 ከዚያም ሰሎሞን ለመላው እስራኤል፣ ለሻለቆች፣ ለመቶ አለቆች፣ ለዳኞች፣ ለእስራኤል መሪዎች ሁሉ እንዲሁም ለየቤተ ሰቡ አለቆች ተናገረ። 3 የእግዚአብሔር ባሪያ ሙሴ በምድረ በዳ የሠራው የአምላክ የመገናኛ ድንኳን በዚያ ስለ ነበር፣ ሰሎሞንና መላው ጉባኤ በገባዖን ወዳለው ኰረብታ ሄዱ። 4 በዚያ ጊዜ ዳዊት የአምላክን ታቦት ከቂርያትይዓይሪም በኢየሩሳሌም ድንኳን ተክሎ ወዳዘጋጀለት ስፍራ አምጥቶት ነበር፤ 5 ይሁን እንጂ የሑር ልጅ፣ የኡሪ ልጅ ባስልኤል የሠራው መሠዊያ በገባዖን በእግዚአብሔር ማደሪያ ድንኳን ፊት ለፊት ይገኝ ነበር፤ ስለዚህ ሰሎሞንና ጉባኤው ይህንኑ ፈለጉ። 6 ሰሎሞንም በእግዚአብሔር ፊት በመገናኛው ድንኳን ውስጥ ወዳለው ወደ ናሱ መሠዊያ ወጥቶ በላዩ ላይ አንድ ሺሕ የሚቃጠል መሥዋዕት አቀረበ። 7 በዚያ ሌሊት እግዚአብሔር ለሰሎሞን ተገልጦ፣ “እንድሰጥህ የምትፈልገውን ሁሉ ጠይቀኝ” አለው። 8 ሰሎሞን እግዚአብሔርን እንዲህ አለው፤ “ለአባቴ ለዳዊት ታላቅ ቸርነትን አሳይተኸዋል፤ እኔንም በእግሩ ተክተህ አንግሠኸኛል። 9 አሁን እግዚአብሔር አምላክ ሆይ፤ ያነገሥኸኝ ብዛቱ እንደ ምድር ትቢያ በሆነ ሕዝብ ላይ ስለ ሆነ፣ ለአባቴ ለዳዊት የሰጠኸው ተስፋ ይጽና። 10 ይህን ሕዝብ ለመምራት እንድችል፣ ጥበብና ዕውቀትን ስጠኝ፤ አለዚያማ፣ ይህን ታላቅ ሕዝብህን ማን ሊያስተዳድር ይችላል?” 11 እግዚአብሔርም ሰሎሞንን እንዲህ አለው፤ “የልብህ መሻት ይህ ስለ ሆነ፣ ብልጽግናና ሀብት ወይም የጠላቶችህን ነፍስ ወይም ረዥም ዕድሜ ስላልጠየቅህ፣ ነገር ግን ባነገሥሁህ ሕዝቤ ላይ የምትገዛበትን ጥበብና ዕውቀት ስለ ጠየቅህ፣ 12 ጥበብና ዕውቀት ይሰጥሃል፤ እንዲሁም ከአንተ በፊት የነበረ ማንኛውም ንጉሥ ያላገኘውን፣ ከአንተ በኋላም የሚነሣው የማያገኘውን ብልጽግና፣ ሀብትና ክብር እሰጥሃለሁ።” 13 ሰሎሞንም የመገናኛው ድንኳን ካለበት ከገባዖን ኰረብታ ወደ ኢየሩሳሌም ተመለሰ፤ በእስራኤልም ላይ ነገሠ። 14 ሰሎሞን ሠረገሎችንና ፈረሶችን ሰበሰበ፤ እርሱም አንድ ሺሕ አራት መቶ ሠረገሎችና ዐሥራ ሁለት ሺሕ ፈረሶች ነበሩት፤ እነርሱንም በሠረገላ ከተሞችና ንጉሡ ባለበት በኢየሩሳሌም ከተማ አኖራቸው። 15 ንጉሡ በኢየሩሳሌም ብሩንና ወርቁን እንደ ማንኛውም ድንጋይ፣ የዝግባውንም ዕንጨት ብዛት በየኰረብታው ግርጌ እንደሚበቅል ሾላ አደረገው። 16 የሰሎሞን ፈረሶች የመጡት ከግብጽና ከቀዌ ሲሆን፣ ከቀዌ የገዟቸውም የንጉሡ ነጋዴዎች ነበሩ። 17 ከግብጽ ያስመጧቸውም አንዱን ሠረገላ በስድስት መቶ ሰቅል ብር፣ አንዱን ፈረስ በአንድ መቶ ዐምሳ ሰቅል ብር ገዝተው ነው። እነዚህንም ደግሞ ለኬጢያውያንና ለሶርያውያን ነገሥታት ሁሉ ይሸጡላቸው ነበር። |
መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™
የቅጂ መብት © 2001, 2024 በBiblica, Inc.
በፈቃድ የሚወሰድ። በዓለም ዐቀፍ ባለቤትነቱ።
The Holy Bible, New Amharic Standard Version™
Copyright © 2001, 2024 by Biblica, Inc.
Used with permission. All rights reserved worldwide.
Biblica, Inc.