1 ጢሞቴዎስ 4 - አዲሱ መደበኛ ትርጒም1 በኋለኞች ዘመናት አንዳንዶች እምነትን ክደው አታላይ መናፍስትንና የአጋንንትን ትምህርት እንደሚከተሉ መንፈስ በግልጽ ይናገራል። 2 እንዲህ ያለው ትምህርት የሚመጣው ኅሊናቸው በጋለ ብረት የተጠበሰ ያህል ከደነዘዘባቸው ግብዝ ውሸተኞች ነው። 3 እነርሱ፣ ሰዎች እንዳያገቡ ይከለክላሉ፤ የሚያምኑና እውነትን የሚያውቁ ሰዎች እግዚአብሔር የፈጠረውን፣ በምስጋናም የሚቀበሉትን እንዳይበሉ ያዝዛሉ። 4 እግዚአብሔር የፈጠረው ማንኛውም ነገር መልካም ነውና፤ በምስጋና ከተቀበሉትም የሚጣል ምንም ነገር የለም፣ 5 በእግዚአብሔር ቃልና በጸሎት የተቀደሰ ነውና። 6 ይህን ትእዛዝ ለወንድሞች ብታሳስብ፣ በእምነት ቃልና በተቀበልኸው መልካም ትምህርት ታንጸህ የክርስቶስ ኢየሱስ በጎ አገልጋይ ትሆናለህ። 7 እግዚአብሔርን ከማያከብር ርባና ቢስ አፈ ታሪክና ከአሮጊቶች ተረታ ተረት ራቅ፤ ይልቁንም ለእውነተኛ መንፈሳዊ ሕይወት ራስህን አሠልጥን። 8 የአካል ብቃት ልምምድ ለጥቂት ነገር ይጠቅማልና፤ ለእውነተኛ መንፈሳዊ ሕይወት ራስን ማሠልጠን ግን ለአሁኑም ሆነ ለሚመጣው ሕይወት ተስፋ ስላለው ለሁለቱም ይጠቅማል። 9 ይህ ቃል የታመነና ሙሉ ለሙሉ ሊቀበሉት የሚገባ ነው። 10 ለዚህ ብለን እንጥራለን፤ እንደክማለንም፤ ይኸውም ለሰዎች ሁሉ፣ በተለይም ለሚያምኑት አዳኝ በሆነው በሕያው እግዚአብሔር ተስፋ ስለምናደርግ ነው። 11 እነዚህን ነገሮች እዘዝ፤ አስተምርም። 12 ወጣትነትህን ማንም አይናቅ፤ ነገር ግን ለሚያምኑት በንግግርና በኑሮ፣ በፍቅር፣ በእምነትና በንጽሕና አርኣያ ሁንላቸው። 13 እኔ እስክመጣ ድረስ ቅዱሳት መጻሕፍትን ለሕዝብ ለማንበብ፣ ለመምከርና ለማስተማር ትጋ። 14 ሽማግሌዎች እጃቸውን በአንተ ላይ ሲጭኑ በትንቢት የተሰጠህን የጸጋ ስጦታ ቸል አትበል። 15 ሰው ሁሉ ማደግህን ያይ ዘንድ በእነዚህ ነገሮች ላይ አትኵር፤ በትጋትም ፈጽማቸው። 16 ለሕይወትህና ለትምህርትህ ተጠንቀቅ፤ በእነዚህም ጽና፤ ይህን ብታደርግ፣ ራስህንና የሚሰሙህንም ታድናለህና። |
መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™
የቅጂ መብት © 2001, 2024 በBiblica, Inc.
በፈቃድ የሚወሰድ። በዓለም ዐቀፍ ባለቤትነቱ።
The Holy Bible, New Amharic Standard Version™
Copyright © 2001, 2024 by Biblica, Inc.
Used with permission. All rights reserved worldwide.
Biblica, Inc.