1 ጴጥሮስ 4 - አዲሱ መደበኛ ትርጒምለእግዚአብሔር መኖር 1 እንግዲህ ክርስቶስ በሥጋው መከራን ስለ ተቀበለ እናንተም በዚሁ ዐላማ ታጥቃችሁ ተነሡ፤ ምክንያቱም በሥጋው መከራን የሚቀበል ሰው ኀጢአትን ትቷል። 2 ከዚህም የተነሣ ከእንግዲህ በሚቀረው ምድራዊ ሕይወት እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ እንጂ እንደ ሥጋ ምኞት አይኖርም። 3 አሕዛብ ፈቅደው እንደሚያደርጉት በመዳራት፣ በሥጋዊ ምኞት፣ በስካር፣ በጭፈራ፣ ያለ ልክ በመጠጣት፣ በአስጸያፊ የጣዖት አምልኮ የተመላለሳችሁበት ያለፈው ዘመን ይበቃል። 4 ይህን በመሰለ ብኩን ሕይወት ከእነርሱ ጋራ ስለማትሮጡ እንግዳ ሆኖባቸው በመደነቅ ይሰድቧችኋል። 5 ነገር ግን በሕያዋንና በሙታን ላይ ሊፈርድ ለተዘጋጀው መልስ ይሰጣሉ። 6 ወንጌል ለሙታን እንኳ ሳይቀር የተሰበከው በዚህ ምክንያት ነው፤ ስለዚህ እንደ ማንኛውም ሰው በሥጋ ይፈረድባቸዋል፤ በመንፈስ ግን እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ ይኖራሉ። 7 የሁሉ ነገር መጨረሻ ተቃርቧል፤ ስለዚህ መጸለይ እንድትችሉ ንቁ አእምሮ ይኑራችሁ፤ ራሳችሁንም የምትገዙ ሁኑ። 8 ፍቅር ብዙ ኀጢአትን ይሸፍናልና፣ ከሁሉ በላይ እርስ በርሳችሁ ከልብ ተዋደዱ፤ 9 እርስ በርሳችሁ ያለ ማጕረምረም እንግድነት ተቀባበሉ። 10 እንደ ታማኝ የእግዚአብሔር ልዩ ልዩ ጸጋ መጋቢ እያንዳንዱ ሰው በተቀበለው የጸጋ ስጦታ ሌላውን ያገልግል። 11 ከእናንተ ማንም የሚናገር ቢኖር እንደ እግዚአብሔር ቃል ይናገር፤ የሚያገለግልም ቢኖር እግዚአብሔር በሚሰጠው ብርታት ያገልግል፤ ይኸውም እግዚአብሔር በኢየሱስ ክርስቶስ አማካይነት እንዲከብር ነው። ክብርና ኀይል ለርሱ ከዘላለም እስከ ዘላለም ይሁን። አሜን። ክርስቲያን በመሆን የሚደርስ መከራ 12 ወዳጆች ሆይ፤ እንደ እሳት የሚፈትን ብርቱ መከራ በመቀበላችሁ እንግዳ ነገር እንደ ደረሰባችሁ በመቍጠር አትደነቁ፤ 13 ነገር ግን ክብሩ በሚገለጥበት ጊዜ ደስታችሁ ታላቅ እንዲሆን የክርስቶስ መከራ ተካፋዮች በመሆናችሁ ደስ ይበላችሁ። 14 ስለ ክርስቶስ ስም ብትሰደቡ፣ የክብር መንፈስ የሆነው የእግዚአብሔር መንፈስ በእናንተ ላይ ስለሚያርፍ ብፁዓን ናችሁ። 15 ከእናንተ ማንም መከራን የሚቀበል ቢኖር፣ ነፍሰ ገዳይ ወይም ሌባ ወይም ወንጀለኛ ወይም በሰው ነገር ጣልቃ ገቢ ሆኖ መከራን አይቀበል፤ 16 ክርስቲያን በመሆኑ መከራ ቢደርስበት ግን፣ ስለዚህ ስም እግዚአብሔርን ያመስግን እንጂ አይፈር። 17 ፍርድ ከእግዚአብሔር ቤት የሚጀምርበት ጊዜ ደርሷልና፤ እንግዲህ ፍርድ የሚጀምረው በእኛ ከሆነ ለእግዚአብሔር ወንጌል የማይታዘዙ ሰዎች መጨረሻቸው ምን ይሆን? 18 እንግዲህ፣ “ጻድቅ የሚድነው በጭንቅ ከሆነ፣ ዐመፀኛውና ኀጢአተኛው እንዴት ሊሆን ይሆን?” 19 ስለዚህ እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ መከራ የሚቀበሉ ሁሉ ነፍሳቸውን ለታመነ ፈጣሪ ዐደራ ሰጥተው መልካም ማድረጋቸውን ይቀጥሉ። |
መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™
የቅጂ መብት © 2001, 2024 በBiblica, Inc.
በፈቃድ የሚወሰድ። በዓለም ዐቀፍ ባለቤትነቱ።
The Holy Bible, New Amharic Standard Version™
Copyright © 2001, 2024 by Biblica, Inc.
Used with permission. All rights reserved worldwide.
Biblica, Inc.