1 ነገሥት 9 - አዲሱ መደበኛ ትርጒምእግዚአብሔር ለሰሎሞን ዳግመኛ ተገለጠ 9፥1-9 ተጓ ምብ – 2ዜና 7፥11-22 1 ሰሎሞን የእግዚአብሔርን ቤተ መቅደስና ቤተ መንግሥቱን ሠርቶ ከጨረሰና ለመሥራት የፈለገውንም ሁሉ ካከናወነ በኋላ፣ 2 እግዚአብሔር ለሰሎሞን በገባዖን ተገልጦለት እንደ ነበረ ሁሉ ዳግም ተገለጠለት። 3 እግዚአብሔርም እንዲህ አለው፤ “በፊቴ ያቀረብኸውን ጸሎትና ልመና ሰምቻለሁ፤ ይህን የሠራኸውንም ቤተ መቅደስ፣ ስሜ ለዘላለም በዚያ ይኖር ዘንድ ቀድሼዋለሁ፤ ዐይኖቼና ልቤም ዘወትር በዚያ ይሆናሉ። 4 “አንተም አባትህ ዳዊት እንዳደረገው ሁሉ፣ በልበ ቅንነትና በትክክለኛነት በፊቴ ብትሄድ፣ ያዘዝሁህን ሁሉ ብትፈጽም፣ ሥርዐቶቼንና ሕጎቼን ብትጠብቅ፣ 5 ለአባትህ ለዳዊት፣ ‘በእስራኤል ዙፋን ላይ የሚቀመጥ ሰው ከዘርህ አታጣም’ በማለት በሰጠሁት ተስፋ መሠረት ዙፋንህን በእስራኤል ላይ ለዘላለም አጸናለሁ። 6 “ነገር ግን አንተም ሆንህ ልጆችህ እኔን ከመከተል ወደ ኋላ ብትመለሱ፣ የሰጠኋችሁን ትእዛዞችና ሥርዐቶች ሳትጠብቁ ብትቀሩ፣ ሄዳችሁም ሌሎችን አማልክት ብታገለግሉና ብታመልኳቸው፣ 7 እኔም እስራኤልን ከሰጠኋቸው ምድር እነቅላቸዋለሁ፤ ስለ ስሜ የቀደስሁትን ይህን ቤተ መቅደስም እተወዋለሁ፤ ከዚያም እስራኤል በሕዝቦች ሁሉ ዘንድ መተረቻና መዘባበቻ ይሆናሉ፤ 8 ይህ ቤተ መቅደስ አሁን እጅግ የሚያስደንቅ ቢሆንም እንኳ፣ የፍርስራሽ ክምር ይሆናል፤ በዚያ የሚያልፍ ሁሉ ይገረማል፤ እያፌዘም፣ ‘እግዚአብሔር በዚህች ምድርና በዚህ ቤተ መቅደስ ላይ እንዲህ ያለውን ነገር ያደረገው ስለ ምን ይሆን?’ ይላል፤ 9 ሰዎቹም መልሰው፣ ‘አዎን እግዚአብሔር ይህን ሁሉ ጥፋት ያመጣባቸው አባቶቻቸውን ከግብጽ ምድር ያወጣውን አምላካቸውን እግዚአብሔርን ትተው ሌሎች አማልክትን በመከተል ስላመለኳቸውና ስላገለገሏቸው ነው’ ይላሉ።” ሰሎሞን ያከናወናቸው ሌሎች ሥራዎች 9፥10-28 ተጓ ምብ – 2ዜና 8፥1-18 10 ሰሎሞን ሁለቱን ሕንጻዎች፣ የእግዚአብሔርን ቤተ መቅደስና የንጉሡን ቤተ መንግሥት ሠርቶ በፈጸመበት በሃያኛው ዓመት መጨረሻ፣ 11 ንጉሥ ሰሎሞን በገሊላ የሚገኙትን ሃያ ከተሞች ለጢሮስ ንጉሥ ለኪራም ሰጠው፤ ንጉሡ ይህን ያደረገውም፣ የሚያስፈልገውን ሁሉ ዝግባ፣ ጥድና ወርቅ ኪራም ሰጥቶት ስለ ነበር ነው፤ 12 ይሁን እንጂ ኪራም ከጢሮስ ተነሥቶ ሰሎሞን የሰጠውን ከተሞች ለማየት በሄደ ጊዜ አልተደሰተባቸውም፤ 13 እርሱም፣ “ወንድሜ ሆይ፤ እነዚህ የሰጠኸኝ ከተሞች ምንድን ናቸው?” አለ፤ እነዚህንም “ከቡል ምድር” አላቸው፤ እስከ ዛሬም በዚሁ ስም ይጠራሉ። 14 በዚያ ጊዜ ኪራም ለንጉሡ መቶ ሃያ መክሊት ወርቅ ልኮለት ነበር። 15 ንጉሥ ሰሎሞን የእግዚአብሔርን ቤተ መቅደስ፣ የራሱን ቤተ መንግሥት፣ ሚሎን፣ የኢየሩሳሌምን ቅጥር፣ አሦርን፣ መጊዶንና ጌዝርን ለመሥራት የጕልበት ሠራተኞች መልምሎ ነበር። 16 የግብጽ ንጉሥ ፈርዖን ወጥቶ በጌዝር ላይ አደጋ ጥሎ ያዛት፤ አቃጠላትም፤ ነዋሪዎቿን ከነዓናውያንን ገድሎ ለልጁ ለሰሎሞን ሚስት መዳሪያ አድርጎ ሰጥቷት ነበር፤ 17 ሰሎሞንም ጌዝርን መልሶ ሠራት፤ እንዲሁም የታችኛውን ቤትሖሮንን፣ 18 ባዕላትን፣ በይሁዳ ምድር በምድረ በዳው የምትገኘውን ተድሞርን ሠራ፤ 19 በአጠቃላይ ሰሎሞን በኢየሩሳሌም፣ በሊባኖስና በግዛቶቹ ሁሉ ለመሥራት የፈለጋቸውን ነገሮች፣ ዕቃ የሚከማችባቸውን ከተሞች፣ እንዲሁም ሠረገለኞችና ፈረሰኞች የሚቀመጡባቸውን ከተሞች ሁሉ ሠራ። 20 እስራኤላውያን ያልሆኑትን ከአሞራውያን፣ ከኬጢያውያን፣ ከፌርዛውያን፣ ከኤዊያውያንና ከኢያቡሳውያን የተረፉትን ሕዝቦች ሁሉ፣ 21 እስራኤላውያን ዘሮቻቸውን ሙሉ ለሙሉ ለማጥፋት ያልቻሉትንና በምድሪቱ የቀሩትን የእነዚህን ሕዝቦች ዘሮች እስከ ዛሬ ድረስ እንደሚደረገው የጕልበት ሥራ ይሠሩ ዘንድ ሰሎሞን መለመላቸው። 22 ሰሎሞን ከእስራኤላውያን ማንንም ባሪያ አላደረገም፤ ይልቁንም እነርሱ ወታደሮቹ፣ ሹማምቱ፣ የጦር አዛዦቹ፣ ሻምበሎቹ፣ የፈረሰኞችና የሠረገለኞች አዛዦቹ ነበሩ። 23 እነዚህም ሰሎሞን የሚያሠራውን ሥራ የሚያከናውኑትን ሠራተኞች የሚቈጣጠሩ አለቆች ናቸው፤ ቍጥራቸውም ዐምስት መቶ ዐምሳ ነበር። 24 የፈርዖን ልጅ ከዳዊት ከተማ ሰሎሞን ወዳሠራላት ቤተ መንግሥት ከመጣች በኋላ ሰሎሞን ሚሎንን ሠራ። 25 ሰሎሞንም ለእግዚአብሔር ባሠራው መሠዊያ ላይ በዓመት ሦስት ጊዜ የሚቃጠል መሥዋዕትና የኅብረት መሥዋዕት በማቅረብ፣ ከዚሁ ጋራ በእግዚአብሔር ፊት ዕጣን ያሳርግ ነበር፤ በዚህ ሁኔታም የቤተ መቅደሱን ግዳጅ ተወጣ። 26 እንዲሁም ንጉሡ ሰሎሞን በኤዶም ምድር የባሕር ጠረፍ፣ በኤላት አጠገብ፣ በቀይ ባሕር ዳርቻ ላይ ባለችው በዔጽዮንጋብር መርከቦችን ሠራ። 27 በመርከቦቹም ላይ ከሰሎሞን ሰዎች ጋራ ዐብረው እንዲሠሩ፣ ኪራም ባሕሩን የሚያውቁ የራሱን መርከበኞች ላከ። 28 እነዚያም ወደ ኦፊር ሄደው አራት መቶ ሃያ መክሊት ወርቅ ይዘው ተመለሱ፤ ይህንም ወደ ንጉሥ ሰሎሞን አመጡ። |
መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™
የቅጂ መብት © 2001, 2024 በBiblica, Inc.
በፈቃድ የሚወሰድ። በዓለም ዐቀፍ ባለቤትነቱ።
The Holy Bible, New Amharic Standard Version™
Copyright © 2001, 2024 by Biblica, Inc.
Used with permission. All rights reserved worldwide.
Biblica, Inc.