Biblia Todo Logo
在线圣经

- 广告 -

1 ነገሥት 5 - አዲሱ መደበኛ ትርጒም


ቤተ መቅደሱን ለመሥራት የተደረገ ዝግጅት
5፥1-16 ተጓ ምብ – 2ዜና 2፥1-18

1 የጢሮስ ንጉሥ ኪራም በዘመኑ ሁሉ ለዳዊት ወዳጅ ስለ ነበር፣ ሰሎሞን በአባቱ እግር ለመተካት መቀባቱን በሰማ ጊዜ፣ መልእክተኞቹን ወደ ሰሎሞን ላከ።

2 ሰሎሞንም እንዲህ የሚል መልእክት ወደ ኪራም መልሶ ላከ፤

3 “አባቴ ዳዊት በዙሪያው ሁሉ ከገጠመው ጦርነት የተነሣ፣ እግዚአብሔር ጠላቶቹን ከእግሩ በታች እስኪጥልለት ድረስ ለአምላኩ ለእግዚአብሔር ስም ቤተ መቅደስ መሥራት እንዳልቻለ ታውቃለህ።

4 አሁን ግን አምላኬ እግዚአብሔር በዙሪያዬ ሁሉ ሰላም ሰጥቶኛል፤ ጠላትም የለብኝም።

5 እነሆ፣ እግዚአብሔር ለአባቴ ለዳዊት፣ ‘ለስሜ ቤተ መቅደስ የሚሠራልኝ ከአንተ ቀጥሎ በዙፋንህ የማስቀምጠው ልጅህ ነው’ ብሎ እንደ ነገረው፣ ለአምላኬ ለእግዚአብሔር ስም ቤተ መቅደስ ለመሥራት ዐስቤአለሁ።

6 “ስለዚህ የሊባኖስ ዝግባ እንዲቈረጥልኝ ትእዛዝ ስጥ፤ ሰዎቼ ከሰዎችህ ጋራ ዐብረው ይሠራሉ፤ የሰዎችህንም ደመወዝ አንተ በወሰንኸው እከፍልሃለሁ፤ ከሰዎቼ መካከል እንደ ሲዶናውያን ዕንጨት በመቍረጥ እስከዚህ የሠለጠነ ሰው አለመኖሩን ራስህም ታውቃለህና።”

7 ኪራም የሰሎሞን መልእክት በደረሰው ጊዜ እጅግ ደስ ስላለው፣ “ይህን ታላቅ ሕዝብ እንዲመራ ለዳዊት ጥበበኛ ልጅ ሰጥቶታልና ዛሬ ምስጋና ለእግዚአብሔር ይግባው” አለ።

8 ስለዚህ ኪራም፣ ለሰሎሞን እንዲህ ሲል ላከበት፤ “የላክኸው መልእክት ደርሶኛል፤ የዝግባውንና የጥዱን ግንድ በማቅረብ ረገድ የምትፈልገውን ሁሉ ለማድረግ ዝግጁ ነኝ፤

9 ሰዎቼ ግንዱን ከሊባኖስ እስከ ባሕሩ ድረስ ጐትተው ያወርዳሉ፤ እኔም ግንዱ ሁሉ ታስሮ አንተ እስከ ወሰንኸው ስፍራ በባሕር ተንሳፍፎ እንዲደርስ አደርጋለሁ፤ እዚያም እኔ እፈታዋለሁ፤ አንተም ትወስደዋለህ፤ አንተም ለቤተ ሰቤ ቀለብ በመስጠት ፍላጎቴን ታሟላለህ።”

10 በዚህ ሁኔታ ኪራም ለሰሎሞን የሚያስፈልገውን የዝግባና የጥድ ግንድ በሙሉ ያቀርብለት ጀመር፤

11 ሰሎሞን ደግሞ ለኪራም ቤተ ሰብ ቀለብ እንዲሆን ሃያ ሺሕ የቆሮስ መስፈሪያ ስንዴ፣ ሃያ ሺሕ ኮር ንጹሕ የወይራ ዘይት ሰጠው፤ ይህን ባለማቋረጥ በየዓመቱ ለኪራም ይሰጥ ነበር።

12 እግዚአብሔርም በገባለት ተስፋ መሠረት ለሰሎሞን ጥበብን ሰጠው፤ በኪራምና በሰሎሞን መካከልም መልካም ግንኙነት ነበር፤ ሁለቱም ቃል ኪዳን አደረጉ።

13 ንጉሥ ሰሎሞን ከመላው እስራኤል የጕልበት ሠራተኞችን መለመለ፤ ቍጥራቸውም ሠላሳ ሺሕ ነበር።

14 እነዚህንም አንድ ወር በሊባኖስ እንዲሠሩ፣ ሁለት ወር በቤታቸው እንዲያርፉ በማድረግ፣ ዐሥር ዐሥር ሺሑን ወር ተራ አግብቶ ላካቸው። የጕልበት ሠራተኞቹም አለቃ አዶኒራም ነበር።

15 ሰሎሞንም በኰረብታማው አገር ሰባ ሺሕ ተሸካሚዎችና ሰማንያ ሺሕ ድንጋይ ጠራቢዎች ነበሩት፤

16 እንዲሁም ሰሎሞን ሥራውን የሚቈጣጠሩ ሦስት ሺሕ ሦስት መቶ ኀላፊዎች ነበሩ።

17 እነርሱም በንጉሡ ትእዛዝ ለቤተ መቅደሱ መሠረት የሚሆን ታላላቅና ምርጥ ድንጋይ ፈልፍለው በማውጣት የተጠረበ ድንጋይ አዘጋጁ።

18 የሰሎሞንና የኪራም የእጅ ባለሙያዎች እንዲሁም የጌባል ሰዎች ለቤተ መቅደሱ የሚያስፈልገውን ዕንጨትና ድንጋይ ፈልጠው አዘጋጁ።

መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™

የቅጂ መብት © 2001, 2024 በBiblica, Inc.

በፈቃድ የሚወሰድ። በዓለም ዐቀፍ ባለቤትነቱ።

The Holy Bible, New Amharic Standard Version™

Copyright © 2001, 2024 by Biblica, Inc.

Used with permission. All rights reserved worldwide. 

Biblica, Inc.
跟着我们:



广告