Biblia Todo Logo
在线圣经

- 广告 -

1 ነገሥት 4 - አዲሱ መደበኛ ትርጒም


የሰሎሞን ሹማምት

1 ንጉሥ ሰሎሞን በእስራኤል ሁሉ ላይ ነገሠ።

2 ዋና ዋናዎቹ ሹማምቱም እነዚህ ነበሩ፤ የሳዶቅ ልጅ ዓዛርያስ፣ ካህን፤

3 የሺሻ ልጆች ኤሊሖሬፍና አኪያ፣ ጸሓፊዎች፤ የአሒሉድ ልጅ ኢዮሣፍጥ፣ ታሪክ ጸሓፊ፤

4 የዮዳሄ ልጅ በናያስ፣ የሰራዊቱ ዋና አዛዥ፤ ሳዶቅና አብያታር፣ ካህናት፤

5 የናታን ልጅ ዓዛርያስ፣ የአውራጃ ገዦች የበላይ ኀላፊ፤ የናታን ልጅ ዛቡድ፣ ካህንና የንጉሡ የቅርብ አማካሪ፤

6 አሒሳር፣ የቤተ መንግሥቱ አዛዥ፤ የዓብዳ ልጅ አዶኒራም የግዳጅ ሥራ ተቈጣጣሪ።

7 እንዲሁም ሰሎሞን ለንጉሡና ለንጉሡ ቤት የሚሆነውን ቀለብ ከመላው እስራኤል የሚሰበስቡ ዐሥራ ሁለት የአውራጃ ገዦች ነበሩት፤ እነዚህም እያንዳንዳቸው በዓመት ውስጥ የወር ቀለብ የሚያቀርቡ ነበሩ።

8 ስማቸውም እንደሚከተለው ነው፤ ቤንሑር፣ በኰረብታማው በኤፍሬም ምድር፤

9 ቤንጼቄር፣ በማቃጽ፣ በሻዓልቢም፣ በቤትሳሚስ፣ በኤሎንቤትሐናን፤

10 ቤንሔሴድ፣ በአሩቦት ውስጥ የሚገኙት ሦኮንና የኦፌር አገር በሙሉ የርሱ ነበር፤

11 ቤን አሚናዳብ፤ በናፎት ዶር፣ እርሱም የሰሎሞንን ልጅ ጣፈትን አግብቶ የነበረ ነው፤

12 የአሒሉድ ልጅ በዓና፣ በታዕናክና በመጊዶ እንዲሁም ከጻርታን ቀጥሎ ቍልቍል እስከ ኢይዝራኤል ባለው በቤትሳን ሁሉ፣ ከዚያም ዮቅምዓምን ተሻግሮ እስከ አቤልምሖላና ድረስ፣

13 ቤንጌበር፣ በገለዓድ ራሞት ከተማ እዚያው ገለዓድ ውስጥ የምናሴ ልጅ የኢያዕር መንደሮች፣ በባሳንም የአርጎብ አውራጃ እንዲሁም በሮቻቸው የናስ መወርወሪያ በሆኑ ስድሳ ባለ ቅጥር ታላላቅ ከተሞች፤

14 የዒዶ ልጅ አሒናዳብ፤ በመሃናይም፣

15 አኪማአስ በንፍታሌም፣ እርሱም የሰሎሞንን ልጅ ባስማትን አግብቶ የነበረ ነው፤

16 የኩሲ ልጅ በዓና፤ በአሴርና በበዓሎት፣

17 የፋሩዋ ልጅ ኢዮሣፍጥ በይሳኮር፣

18 የኤላ ልጅ ሳሚ በብንያም፣

19 የኡሪ ልጅ ጌበር፣ በገለዓድ፤ በአሞራውያን ንጉሥ በሴዎን ምድር፣ በባሳን ንጉሥ በዐግ አገር፣ እርሱም የአውራጃው ብቸኛ ገዥ ነበር።


ለሰሎሞን በየቀኑ የሚገባለት ቀለብ

20 የይሁዳና የእስራኤል ሕዝቦች ብዛታቸው እንደ ባሕር ዳር አሸዋ ሆነ፤ ይበሉ፣ ይጠጡና ይደሰቱም ነበር።

21 ሰሎሞንም ከወንዙ አንሥቶ እስከ ፍልስጥኤማውያን ምድር፣ ከዚያም እስከ ግብጽ ዳርቻ ያሉትን መንግሥታት ሁሉ ገዛ፤ እነዚህም አገሮች ግብር አመጡለት፤ በሕይወት ዘመኑም ሁሉ ተገዙለት።

22 ለሰሎሞን በየቀኑ የሚገባለትም ቀለብ ይህ ነበር፤ ሠላሳ ኮር ማለፊያ ዱቄት፣ ስድሳ ኮር መናኛ ዱቄት፣

23 ዐሥር ቅልብ ሰንጋዎች፣ ሃያ ግጦሽ መሬት ላይ የሚውሉ በሬዎች፣ መቶ በግና ፍየል እንዲሁም ዋሊያ፣ ሚዳቋ፣ የበረሓ ፍየልና ምርጥ አዕዋፍ።

24 ከወንዙ በስተ ምዕራብ፣ ከቲፍሳ እስከ ጋዛ ያሉትን መንግሥታት ስለ ገዛ፣ በሁሉም አቅጣጫ ሰላም ሆኖለት ነበር።

25 በሰሎሞን ዘመን ሁሉ ከዳን አንሥቶ እስከ ቤርሳቤህ ያለው ይሁዳና እስራኤል፣ እያንዳንዱ ሰው ከወይኑና ከበለሱ ጥላ ሥር ያለ ሥጋት ለመኖር በቃ።

26 ሰሎሞን ሠረገላ የሚጐትቱ ፈረሶች የሚያድሩበት አራት ሺሕ ጋጣና ዐሥራ ሁለት ሺሕ ፈረሶች ነበሩት።

27 የየአውራጃው ሹማምትም በየወር ተራቸው ንጉሡን ሰሎሞንንና ወደ ንጉሡ ማእድ የሚቀርቡትን ሁሉ ምንም ሳያጓድሉ ይቀልቡ ነበር፤

28 እንዲሁም ለሠረገላ ፈረሶችና ለፈጣን ፈረሶች የተመደበውን ገብስና ጭድ ከተፈለገው ቦታ ድረስ ያመጡ ነበር።


የሰሎሞን ጥበብ

29 አምላክ ለሰሎሞን ጥበብንና እጅግ ታላቅ ማስተዋልን እንዲሁም በባሕር ዳር እንዳለ አሸዋ የልብ ስፋትን ሰጠው።

30 የሰሎሞን ጥበብ ከምሥራቅ ሰዎች ሁሉ ጥበብ በጣም የላቀ ከግብጽም ጥበብ ሁሉ የበለጠ ነበር፤

31 እርሱም ከማንም ሰው ይልቅ ጥበበኛ ነበር፣ ከኢይዝራኤላዊው ከኤታን፣ ከማሖል ልጆች ከሄማንና ከከልቀድ ደግሞም ከደራል ይልቅ ጥበበኛ ነበር፤ ዝናውም በዙሪያው ባሉት አሕዛብ ሁሉ ተሰማ።

32 እርሱም ሦስት ሺሕ ምሳሌዎችን ተናገረ፤ የመሓልዩም ቍጥር ሺሕ ዐምስት ነበር።

33 ከሊባኖስ ዝግባ አንሥቶ በቅጥር ግንብ ላይ እስከሚበቅለው ሂሶጵ ስለ ዕፀዋት ተናግሯል፤ እንዲሁም ስለ እንስሳት፣ ስለ ወፎች፣ በምድር ላይ ስለሚሳቡ ፍጥረታትና ስለ ዓሦችም ተናግሯል፤

34 ጥበቡን ከሰሙት ከዓለም ነገሥታት ሁሉ የተላኩ፣ የየአገሩ ሰዎች ሁሉ የሰሎሞንን ጥበብ ለማድመጥ መጡ።

መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™

የቅጂ መብት © 2001, 2024 በBiblica, Inc.

በፈቃድ የሚወሰድ። በዓለም ዐቀፍ ባለቤትነቱ።

The Holy Bible, New Amharic Standard Version™

Copyright © 2001, 2024 by Biblica, Inc.

Used with permission. All rights reserved worldwide. 

Biblica, Inc.
跟着我们:



广告