Biblia Todo Logo
在线圣经

- 广告 -

1 ነገሥት 22 - አዲሱ መደበኛ ትርጒም


ሚክያስ በአክዓብ ላይ ትንቢት ተናገረ
22፥1-28 ተጓ ምብ – 2ዜና 18፥1-27

1 በሶርያና በእስራኤል መካከል ለሦስት ዓመት ጦርነት አልነበረም።

2 በሦስተኛው ዓመት ግን የይሁዳ ንጉሥ ኢዮሣፍጥ የእስራኤልን ንጉሥ ለመጐብኘት ወረደ።

3 የእስራኤልም ንጉሥ ሹማምቱን፣ “በገለዓድ የምትገኘው ራሞት የእኛ ሆና ሳለች፣ ከሶርያው ንጉሥ እጅ ለመመለስ ምንም እንዳላደረግን አታውቁምን?” አላቸው።

4 ስለዚህ ኢዮሣፍጥን፣ “በገለዓድ የምትገኘው ራሞት ላይ ለመዝመት ዐብረኸኝ ለመሄድ ትፈቅዳለህን?” ሲል ጠየቀው። ኢዮሣፍጥም የእስራኤልን ንጉሥ፣ “እኔ እንደ አንተው ነኝ፤ ሕዝቤም እንደ ሕዝብህ፣ ፈረሶቼም እንደ ፈረሶችህ ናቸው” አለው።

5 ደግሞም ኢዮሣፍጥ የእስራኤልን ንጉሥ፣ “በመጀመሪያ ግን የእግዚአብሔርን ሐሳብ ጠይቅ” አለው።

6 ስለዚህ የእስራኤል ንጉሥ አራት መቶ ነቢያትን በአንድነት ሰብስቦ፣ “በገለዓድ በምትገኘው ራሞት ላይ ልዝመት ወይስ ልቅር?” ሲል ጠየቃቸው። እነርሱም፣ “እግዚአብሔር በንጉሡ እጅ አሳልፎ ይሰጣታልና ዝመትባት” አሉት።

7 ኢዮሣፍጥ ግን፣ “እንጠይቀው ዘንድ ሌላ የእግዚአብሔር ነቢይ እዚህ የለምን?” አለ።

8 የእስራኤልም ንጉሥ ለኢዮሣፍጥ፣ “መኖሩንማ በርሱ አማካይነት የእግዚአብሔርን ፈቃድ የምንጠይቀው አንድ ነቢይ አሁንም አለ፤ ነገር ግን ስለ እኔ ክፉ እንጂ ምን ጊዜም መልካም ትንቢት ተናግሮ ስለማያውቅ እጠላዋለሁ፤ ይህም ሰው የይምላ ልጅ ሚክያስ ነው” አለ። ኢዮሣፍጥም፣ “ንጉሡ እንዲህ ማለት አይገባውም” ሲል መለሰ።

9 ስለዚህ የእስራኤል ንጉሥ ከሹማምቱ አንዱን ጠርቶ፣ “የይምላን ልጅ ሚክያስን በፍጥነት አምጣው” አለው።

10 የእስራኤል ንጉሥና የይሁዳ ንጉሥ ኢዮሣፍጥ አልባሰ መንግሥታቸውን ለብሰው፣ በሰማርያ መግቢያ በር አጠገብ ባለው ዐውድማ ላይ በየዙፋናቸው ተቀምጠው፣ ነቢያቱ ሁሉ በፊታቸው ትንቢት ይናገሩ ነበር።

11 በዚህ ጊዜ፣ የክንዓና ልጅ ሴዴቅያስ የብረት ቀንዶች ሠርቶ፣ “እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ ‘ሶርያውያን እስኪጠፉ ድረስ በእነዚህ ትወጋቸዋለህ’ ” አለ።

12 የቀሩትም ነቢያት ሁሉ፣ “እግዚአብሔር በንጉሡ እጅ አሳልፎ ይሰጣታልና፣ በገለዓድ በምትገኘው ራሞት ላይ ዝመትባት” በማለት ተመሳሳይ ትንቢት ይናገሩ ነበር።

13 ሚክያስን ሊጠራ ሄዶ የነበረውም መልእክተኛ፣ “እነሆ፣ ሌሎቹ ነቢያት በአንድ አፍ ሆነው፣ ለንጉሡ መልካምን ነገር እየተነበዩ ነው፤ እባክህ የአንተም ቃል እንደ ቃላቸው ይሁን፤ ንጉሡን ደስ የሚያሠኘውን ተናገር” አለው።

14 ሚክያስ ግን፣ “ሕያው እግዚአብሔርን! እግዚአብሔር የነገረኝን ብቻ እነግረዋለሁ” አለ።

15 ወደ ንጉሡ በመጣ ጊዜ ንጉሡ፣ “ሚክያስ ሆይ፤ በገለዓድ በምትገኘው ራሞት ላይ እንዝመት ወይስ እንቅር?” ሲል ጠየቀው። እርሱም፣ “ሂዱና ድል አድርጉ እግዚአብሔር በንጉሡ እጅ አሳልፎ ይሰጣታል” ብሎ መለሰለት።

16 ንጉሡም፣ “ከእውነት በቀር ምንም ነገር በእግዚአብሔር ስም እንዳትነግረኝ የማምልህ ስንት ጊዜ ነው?” አለው።

17 ከዚያም ሚክያስ፣ “እስራኤል ሁሉ እረኛ እንደሌላቸው በጎች በተራሮች ላይ ተበታትነው አየሁ፤ እግዚአብሔርም፣ ‘እነዚህ ሰዎች ጌታ የላቸውም፤ እያንዳንዱም በሰላም ወደየቤቱ ይመለስ’ ብሏል” ሲል መለሰ።

18 የእስራኤልም ንጉሥ ኢዮሣፍጥን፣ “ስለ እኔ ክፉ ብቻ እንጂ፣ መልካም ትንቢት አይናገርም አላልሁህምን?” አለው።

19 ከዚያም ሚክያስ እንዲህ አለ፤ “እንግዲህ የእግዚአብሔርን ቃል ስማ፤ እግዚአብሔር በዙፋኑ ላይ ተቀምጦ፣ የሰማይም ሰራዊት ሁሉ በቀኙና በግራው ቆመው አየሁ።

20 እግዚአብሔርም፣ ‘የእስራኤል ንጉሥ አክዓብ በገለዓድ በምትገኘው ራሞት ላይ ዘምቶ እዚያው እንዲሞት ማን ያሳስተው?’ አለ። “አንዱ አንድ ሐሳብ፣ ሌላውም ሌላ ሐሳብ አቀረበ።

21 ከዚያም አንድ መንፈስ መጥቶ፣ በእግዚአብሔር ፊት በመቆም፣ ‘እኔ አሳስተዋለሁ’ አለ።

22 “እግዚአብሔርም፣ ‘እንዴት አድርገህ?’ ሲል ጠየቀው። “እርሱም፣ ‘እኔ እወጣና፤ በገዛ ነቢያቱ ሁሉ አፍ የሐሰት መንፈስ እሆናለሁ’ አለ። “እግዚአብሔርም፣ ‘ታሳስተዋለህ፤ ይሳካልሃልም፤ እንግዲህ ውጣና አድርግ’ አለው።

23 “ስለዚህ እነሆ እግዚአብሔር በእነዚህ ሁሉ ነቢያትህ አፍ የሐሰት መንፈስ አኖረ፤ እግዚአብሔርም ጥፋት እንደሚያመጣብህ ተናግሯል።”

24 ከዚያም የክንዓና ልጅ ሴዴቅያስ ወጥቶ ሚክያስን በጥፊ መታውና፣ “ለመሆኑ የእግዚአብሔር መንፈስ በየት በኩል ዐልፎኝ ነው አንተን ያናገረህ?” አለው።

25 ሚክያስም፣ “ለመሸሸግ ወደ እልፍኝህ በምትሄድበት በዚያ ዕለት ታገኘዋለህ” አለው።

26 ከዚያም የእስራኤል ንጉሥ እንዲህ ሲል አዘዘ፤ “ሚክያስን ይዛችሁ ወደ ከተማዪቱ ገዥ ወደ አሞንና ወደ ንጉሡ ልጅ ወደ ኢዮአስ መልሱት፤

27 ከዚያም፣ ‘ንጉሡ፣ ይህን ሰው እስር ቤት አስገቡት፤ በደኅና እስክመለስም ድረስ፣ ከደረቅ እንጀራና ከውሃ በቀር ሌላ እንዳትሰጡት’ ብሏል በሏቸው” አለ።

28 ሚክያስም፣ “አንተ በደኅና ከተመለስክማ እግዚአብሔር በእኔ አልተናገረም ማለት ነው!” አለ፤ ቀጥሎም፣ “እናንተ ሰዎች ሁላችሁ ስሙኝ” አለ።


አክዓብ በገለዓድ በምትገኘው በሬማት ተገደለ
22፥29-36 ተጓ ምብ – 2ዜና 18፥28-34

29 ስለዚህ የእስራኤል ንጉሥና የይሁዳ ንጉሥ ኢዮሣፍጥ ወደ ራሞት ገለዓድ ወጡ።

30 የእስራኤልም ንጉሥ ኢዮሣፍጥን፣ “እኔ ልብሴን ለውጬ ወደ ጦርነቱ እገባለሁ፤ አንተ ግን ልብሰ መንግሥትህን ልበስ” አለው። ስለዚህ የእስራኤል ንጉሥ ልብሱን ለውጦ ሌላ ሰው መስሎ ወደ ጦርነቱ ገባ።

31 በዚህ ጊዜ የሶርያ ንጉሥ ሠላሳ ሁለቱን የሠረገላ አዛዦች፣ “ከራሱ ከእስራኤል ንጉሥ በቀር ትንሽም ሆነ ትልቅ ከሌላ ከማንም ጋራ እንዳትዋጉ” ብሎ አዝዟቸው ነበር፤

32 የሠረገላው አዛዦችም ኢዮሣፍጥን ባዩ ጊዜ፣ “የእስራኤል ንጉሥ ይህ ነው” ብለው አሰቡ፤ ሊወጉትም ከበቡት፤ ኢዮሣፍጥ ግን ጮኸ፤

33 የሠረገላ አዛዦቹ እርሱ የእስራኤል ንጉሥ አለመሆኑን ዐውቀው መከታተሉን ተዉት።

34 ይሁን እንጂ አንዱ ቀስቱን በነሲብ ቢያስፈነጥረው፣ በጥሩሩ መጋጠሚያዎች መካከል ዐልፎ የእስራኤልን ንጉሥ ወጋው። ንጉሡም ሠረገላ ነጂውን “ተመለስና ከጦርነቱ አውጣኝ፤ ቈስያለሁና” አለው።

35 ጦርነቱም ቀኑን ሙሉ ተፋፍሞ ዋለ፤ በዚህ ጊዜ ንጉሡ በሶርያውያን ፊት ለፊት በሠረገላው ላይ ቀና ብሎ እንደ ተደገፈ ነበር፤ የቍስሉ ደም በሠረገላው ወለል ላይ ይወርድ ነበር፤ በዚያ ዕለት ማታም ንጉሡ ሞተ።

36 ፀሓይ ስትጠልቅም በሰራዊቱ መካከል፣ “እያንዳንዱ ሰው ወደ ቤቱ፣ እያንዳንዱም ወደ አገሩ ይሂድ!” የሚል ጩኸት አስተጋባ።

37 ንጉሡ ስለ ሞተም ወደ ሰማርያ አምጥተውት እዚያው ተቀበረ።

38 ሠረገላውንም አመንዝሮች በታጠቡበት በሰማርያ ኵሬ ዐጠቡት፤ እግዚአብሔርም እንደ ተናገረው ቃል ደሙን ውሾች ላሱት።

39 ሌላው በአክዓብ ዘመነ መንግሥት የተፈጸመውና ያደረገው ሁሉ፣ ቤተ መንግሥቱን መሥራቱና በዝኆን ጥርስ መለበጡ እንዲሁም የሠራቸው የምሽግ ከተሞች በእስራኤል ነገሥታት ታሪክ የተጻፈ አይደለምን?

40 አክዓብም ከአባቶቹ ጋራ አንቀላፋ፤ ልጁ አካዝያስም በእግሩ ተተክቶ ነገሠ።


የይሁዳ ንጉሥ ኢዮሣፍጥ
22፥41-50 ተጓ ምብ – 2ዜና 20፥31–21፥1

41 የእስራኤል ንጉሥ አክዓብ በነገሠ በአራተኛው ዓመት የአሳ ልጅ ኢዮሣፍጥ በይሁዳ ነገሠ።

42 ኢዮሣፍጥ መንገሥ በጀመረ ጊዜ ዕድሜው ሠላሳ ዐምስት ዓመት ነበረ፤ በኢየሩሳሌም ተቀምጦ ሃያ ዐምስት ዓመት ገዛ። እናቱም የሺልሒ ልጅ ዓዙባ ነበረች።

43 እርሱም በአካሄዱ ሁሉ የአባቱን የአሳን መንገድ ተከተለ፤ ከዚያም ፈቀቅ አላለም፤ በእግዚአብሔርም ፊት መልካም የሆነውን አደረገ፤ ይሁን እንጂ በየኰረብታው ላይ ያሉት የማምለኪያ ስፍራዎች ገና አልተወገዱም፤ ሕዝቡም በዚያ መሥዋዕት ማቅረቡንና ዕጣን ማጤሱን እንደ ቀጠለ ነበር።

44 እንዲሁም ኢዮሣፍጥ ከእስራኤል ንጉሥ ጋራ በሰላም ኖረ።

45 የቀረውም ኢዮሣፍጥ በዘመነ መንግሥቱ ከመጀመሪያ እስከ መጨረሻው ያከናወናቸው ተግባራት፦ ጀግንነቱና ያደረጋቸው ጦርነቶች ሁሉ በይሁዳ ነገሥታት የታሪክ መጽሐፍ የተጻፉ አይሉምን?

46 ከአባቱ ከአሳ ዘመን በኋላ እንኳ ተርፈው በጣዖት ማምለኪያ ቦታዎች የነበሩትን የወንደቃ ቅሬታዎች ከምድሪቱ አስወገደ።

47 በዚያ ጊዜ ኤዶም ንጉሥ አልነበራትም፤ የሚገዛት እንደራሴ ነበር።

48 ኢዮሣፍጥ ወርቅ ለማምጣት ወደ ኦፊር የሚሄዱ የተርሴስ መርከቦች አሠርቶ ነበር፤ ይሁን እንጂ በዔጽዮንጋብር ስለ ተሰበሩ ከቶ ወደዚያ መሄድ አልቻሉም ነበር።

49 በዚያ ጊዜም የአክዓብ ልጅ አካዝያስ ኢዮሣፍጥን “ሰዎቼ ከሰዎችህ ጋራ በመርከብ ይሂዱ” ሲል ጠይቆት ነበር፤ ኢዮሣፍጥ ግን ዕሺ አላለውም።

50 ኢዮሣፍጥ ከአባቶቹ ጋራ አንቀላፋ፤ እነርሱ በተቀበሩበት በአባቱ በዳዊት ከተማ ተቀበረ። ልጁ ኢዮራምም በምትኩ ነገሠ።


የእስራኤል ንጉሥ አካዝያስ

51 የይሁዳ ንጉሥ ኢዮሣፍጥ በነገሠ በዐሥራ ሰባተኛው ዓመት የአክዓብ ልጅ አካዝያስ የእስራኤል ንጉሥ ሆኖ በሰማርያ ነገሠ፤ እስራኤልንም ሁለት ዓመት ገዛ።

52 እርሱም የአባቱንና የእናቱን፣ እንዲሁም እስራኤልን ያሳተውን የናባጥን ልጅ የኢዮርብዓምን መንገድ በመከተሉ፣ በእግዚአብሔር ፊት የተጠላ ክፉ ሥራ ሠራ።

53 አባቱ እንዳደረገው ሁሉ፣ እርሱም በኣልን አመለከ፤ ሰገደለትም። በዚህም የእስራኤልን አምላክ እግዚአብሔርን ለቍጣ እንዲነሣሣ አደረገ።

መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™

የቅጂ መብት © 2001, 2024 በBiblica, Inc.

በፈቃድ የሚወሰድ። በዓለም ዐቀፍ ባለቤትነቱ።

The Holy Bible, New Amharic Standard Version™

Copyright © 2001, 2024 by Biblica, Inc.

Used with permission. All rights reserved worldwide. 

Biblica, Inc.
跟着我们:



广告