1 ነገሥት 20 - አዲሱ መደበኛ ትርጒምቤን ሃዳድ ሰማርያን ወጋ 1 በዚህ ጊዜ የሶርያ ንጉሥ ቤን ሃዳድ መላ ሰራዊቱን በአንድነት አሰባሰበ፤ ከርሱም ጋራ ሠላሳ ሁለት ነገሥታት ከነፈረሶቻቸውና ከነሠረገሎቻቸው ዐብረውት ነበሩ፤ ወጥቶም ሰማርያን ከብቦ ወጋት። 2 ወደ ከተማዪቱም መልእክተኞች በመላክ የእስራኤልን ንጉሥ አክዓብን እንዲህ አለው፤ “ቤን ሃዳድ እንዲህ ይላል፤ 3 ‘ብርና ወርቅህ የእኔ ነው፤ የሚያማምሩት ሚስቶችህና ልጆችህም የእኔ ናቸው።’ ” 4 የእስራኤልም ንጉሥ፣ “ንጉሥ ጌታዬ ሆይ፤ ልክ እንዳልኸው ነው፤ እኔም ሆንሁ የእኔ የሆነው ሁሉ የአንተ ነው” ሲል መለሰለት። 5 መልእክተኞቹም እንደ ገና መጥተው እንዲህ አሉት፤ “ቤን ሃዳድ የሚለው ይህ ነው፤ ‘ብርህንና ወርቅህን፣ ሚስቶችህንና ልጆችህን እንድትሰጠኝ ልኬብህ ነበር፤ 6 ሆኖም ነገ በዚሁ ጊዜ ቤተ መንግሥትህንና የሹማምትህን ቤቶች እንዲበረብሩ፣ ሹማምቴን እልካቸዋለሁ። እነርሱም ማንኛውንም ለአንተ ዋጋ ያለውን ሁሉ በእጃቸው በማስገባት ይወስዱታል።’ ” 7 የእስራኤልም ንጉሥ የአገሩን ሽማግሌዎች ሁሉ ጠርቶ፣ “ይህ ሰው እንዴት ጠብ እንደሚፈልግ ታያላችሁ፤ ሚስቶቼንና ልጆቼን፣ ብሬንና ወርቄን እንዳስረክበው በጠየቀኝ ጊዜ አልከለከልሁትም” አላቸው። 8 ሽማግሌዎቹና ሕዝቡም ሁሉ፣ “የሚልህን አትቀበለው፤ የጠየቀህንም ዕሺ አትበለው” አሉት። 9 ስለዚህ ለቤን ሃዳድ መልእክተኞች፣ “ለጌታዬ ለንጉሡ፣ ‘እኔ ባሪያህ በመጀመሪያ ያልኸኝን ሁሉ አደርጋለሁ፤ ያሁኑን ጥያቄህን ግን ልፈጽመው አልችልም’ ብላችሁ ንገሩት” አላቸው። መልእክተኞቹም ይህንኑ ይዘው ተመለሱ። 10 ከዚያም ቤን ሃዳድ፣ “ለሚከተለኝ ሰው ሁሉ የሰማርያ ዐፈር አንዳንድ ዕፍኝ የሚዳረስ ሳይሆን ቢቀር፣ አማልክት ይህን ያድርጉብኝ፤ ከዚህ የባሰም ያምጡብኝ” ሲል ሌሎች መልክተኞችን ወደ አክዓብ ላከ። 11 የእስራኤልም ንጉሥ፣ “ ‘ታጥቆ ለጦርነት የሚወጣ ሰው የጦር ትጥቁን እንደ ፈታ ሰው መደንፋት የለበትም’ ብላችሁ ንገሩት” አላቸው። 12 ቤን ሃዳድ ይህን መልእክት የሰማው ዐብረውት የነበሩት ነገሥታት በድንኳኖቻቸው ውስጥ ሆነው በሚጠጡበት ጊዜ ነበር፤ ቤን ሃዳድ ሰዎቹን፣ “በሉ ለጦርነት ተዘጋጁ” አላቸው፤ ስለዚህ ከተማዪቱን ለመውጋት ተዘጋጁ። አክዓብ ቤን ሃዳድን ድል አደረገ 13 በዚያ ጊዜ አንድ ነቢይ ወደ እስራኤል ንጉሥ ወደ አክዓብ መጥቶ፣ “እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ ‘ይህን ብዙ ሰራዊት ታያለህን? ዛሬ በእጅህ አሳልፌ እሰጥሃለሁ፤ ከዚያም እኔ እግዚአብሔር መሆኔን ታውቃለህ’ ” አለው። 14 አክዓብም፣ “ይህን የሚያደርገው ማን ነው?” ሲል ጠየቀ። ነቢዩም፣ “እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ ‘ይህን የሚያደርጉት የየአውራጃው አዛዥ የሆኑ ወጣት መኰንኖች ናቸው’ ” አለው። “ታዲያ ጦርነቱን የሚጀምረው ማን ነው?” ሲል ጠየቀ። ነቢዩም፣ “አንተው ትጀምራለህ” ብሎ መለሰ። 15 ስለዚህ አክዓብ የየአውራጃው አዛዥ የሆኑትን ሁለት መቶ ሠላሳ ሁለት ወጣት መኰንኖች ጠራ፤ ከዚያም የቀሩትን እስራኤላውያን ሰበሰበ፤ እነዚህም በአጠቃላይ ሰባት ሺሕ ነበሩ። 16 እነርሱም ቤን ሃዳድና ከርሱ ጋራ ተባብረው የነበሩት ሠላሳ ሁለቱ ነገሥታት በድንኳኖቻቸው ውስጥ ሰክረው ሳለ እኩለ ቀን ላይ መጡ። 17 በግንባር ቀደምትነት የወጡት ግን፣ የየአውራጃው አዛዥ የሆኑት ወጣት መኰንኖች ነበሩ። በዚህ ጊዜ ቤን ሃዳድ ሰላዮች ልኮ ነበርና እነርሱም፣ “ሰዎች ከሰማርያ ወጥተው ወደዚህ በመምጣት ላይ ናቸው” ብለው ነገሩት። 18 እርሱም፣ “አመጣጣቸው ለሰላምም ይሁን ለጦርነት ከነሕይወታቸው ይዛችሁ አምጧቸው” አለ። 19 የየአውራጃው አዛዥ የሆኑ ወጣት መኰንኖችም ሰራዊቱን አስከትለው ከከተማዪቱ ወጡ፤ 20 እያንዳንዱም በፊቱ የገጠመውን ጠላት ገደለ፤ ሶርያውያን ሸሹ፤ እስራኤላውያንም ያሳድዷቸው ጀመር። የሶርያ ንጉሥ ቤን ሃዳድ ግን በፈረሱ ላይ ሆኖ ከጥቂት ፈረሰኞቹ ጋራ አመለጠ። 21 የእስራኤል ንጉሥ አክዓብም ወደ ፊት በመግፋት ፈረሶችንና ሠረገሎችን ማረከ፤ በሶርያውያንም ላይ ከባድ ጕዳት አደረሰባቸው። 22 ከዚያም በኋላ ነቢዩ ወደ እስራኤል ንጉሥ መጥቶ፣ “በሚመጣው የጸደይ ወራት የሶርያ ንጉሥ ተመልሶ ይመጣብሃልና በርታ፤ ምን ማድረግ እንዳለብህም ዕወቅ” አለው። 23 በዚያ ጊዜም የሶርያ ንጉሥ ሹማምት እንዲህ ሲሉ መከሩት፤ “አማልክታቸው የኰረብታ አማልክት ናቸው፤ ያየሉብንም ከዚህ የተነሣ ነው። በሜዳ ላይ ብንገጥማቸው ግን እኛ እንደምናይልባቸው አያጠራጥርም። 24 እንግዲህ እንዲህ አድርግ፤ ነገሥታቱን በሙሉ ከአዛዥነታቸው አስነሣ፤ በቦታቸውም ሌሎች ሹማምት አድርግ። 25 ከእስራኤል ጋራ በሜዳው ላይ እንዲጋጠም በፈረሱ ፈንታ ፈረስ፣ በሠረገላው ፈንታ ሠረገላ በመተካት፣ እንደ ተደመሰሰው ያለ ሰራዊት አቋቁም፤ ከዚያ በኋላ ከእነርሱ ይበልጥ እኛ እንደምንበረታ አያጠራጥርም።” ንጉሡም ባቀረቡት ሐሳብ ተስማማ፤ እንዳሉትም አደረገ። 26 በተከታዩም የጸደይ ወራት ቤን ሃዳድ ሶርያውያንን አሰባስቦ እስራኤልን ለመውጋት ወደ አፌቅ ወጣ። 27 እስራኤላውያንም እንደዚሁ ተሰብስበው ስንቅ ከተሰጣቸው በኋላ ሊገጥሟቸው ተሰልፈው ወጡ። ሶርያውያን አገር ምድሩን ሞልተውት ሳለ፣ እስራኤላውያን ግን እንደ ሁለት ትንንሽ የፍየል መንጋ ሆነው ከፊት ለፊታቸው ሰፈሩ። 28 የእግዚአብሔርም ሰው ወጥቶ ለእስራኤል ንጉሥ፣ “እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ ‘ሶርያውያን እግዚአብሔር የኰረብታ እንጂ የሸለቆ አምላክ አይደለም ብለዋልና ይህን ስፍር ቍጥር የሌለው ሰራዊት በእጅህ አሳልፌ እሰጥሃለሁ፤ አንተም እኔ እግዚአብሔር መሆኔን ታውቃለህ’ ” አለው። 29 በየሰፈሩበትም ቦታ ሰባት ቀን ከተፋጠጡ በኋላ በሰባተኛው ቀን ጦርነት ገጠሙ። እስራኤላውያንም በአንዲት ጀምበር ከሶርያውያን ሰራዊት መቶ ሺሕ እግረኛ ገደሉ። 30 የቀሩት ወደ አፌቅ ከተማ ሸሹ፤ በዚያም በሃያ ሰባቱ ሺሕ ላይ ቅጥሩ ተንዶ ወደቀባቸው። ቤን ሃዳድም ወደ ከተማዪቱ ሸሽቶ በመሄድ ወደ አንዲት እልፍኝ ገብቶ ተደበቀ። 31 ሹማምቱም፣ “የእስራኤል ቤት ነገሥታት መሓሪዎች መሆናቸውን ሰምተናል፤ አሁንም እንነሣና በወገባችን ላይ ማቅ ታጥቀን፣ በራሳችን ላይ ገመድ ጠምጥመን ወደ እስራኤል ንጉሥ እንሂድ፤ ምናልባትም ሕይወትህን ያተርፋት ይሆናል” አሉት። 32 እነርሱም በወገባቸው ላይ ማቅ ታጥቀው፣ በራሳቸው ላይ ገመድ ጠምጥመው ወደ እስራኤል ንጉሥ በመሄድ፣ “አገልጋይህ ቤን ሃዳድ፣ ‘እባክህ በሕይወት እንድኖር ፍቀድልኝ’ ብሎ ይለምንሃል” አሉት። ንጉሡም፣ “እስካሁን በሕይወት አለን? ወንድሜ እኮ ነው” አለ። 33 ሰዎቹም ይህን በደግ በመተርጐም ቃሉን ከአፉ ቀበል አድርገው፤ “አዎን ቤን ሃዳድ ወንድምህ ነው” አሉት። ንጉሡም፣ “በሉ ሂዱና አምጡት” አላቸው፤ ቤን ሃዳድም በመጣ ጊዜ፣ አክዓብ ሠረገላው ላይ እንዲወጣ አደረገው። 34 ቤን ሃዳድም፣ “አባቴ ከአባትህ የወሰዳቸውን ከተሞች እመልሳለሁ፤ አባቴ በሰማርያ እንዳደረገው ሁሉ፣ አንተም በደማስቆ የራስህን ገበያ ማቋቋም ትችላለህ” አለው። አክዓብም፣ “እንግዲያውስ ስምምነት አድርገን በነጻ እለቅቅሃለሁ” አለው፤ ስለዚህም ከርሱ ጋራ የውል ስምምነት አድርጎ ለቀቀው። አንድ ነቢይ በአክዓብ ላይ ፈረደ 35 ከነቢያት ልጆች አንዱ ጓደኛውን በእግዚአብሔር ቃል ታዞ፣ “ምታኝ” አለው፤ ሰውየው ግን ፈቃደኛ አልሆነም። 36 ስለዚህም ነቢዩ፣ “ለእግዚአብሔር ባለመታዘዝህ፣ ከእኔ ተለይተህ እንደ ሄድህ አንበሳ ይገድልሃል” አለው። ሰውየው ከሄደ በኋላ አንበሳ አግኝቶ ገደለው። 37 ነቢዩም ሌላ ሰው አግኝቶ፣ “እባክህ ምታኝ” አለው። ስለዚህ ያ ሰው መትቶ አቈሰለው። 38 ከዚያም ነቢዩ ሄዶ ከመንገድ ዳር በመቆም፣ ንጉሡን ይጠባበቅ ጀመር። የራሱን መጠምጠሚያ ወደ ታች አውርዶ ዐይኖቹን በመሸፈንም፣ ማንነቱ እንዳይታወቅ አደረገ። 39 ንጉሡ በዚያ በሚያልፍበትም ጊዜ፣ ነቢዩ ጠርቶት እንዲህ አለው፤ “እኔ አገልጋይህ በተፋፋመው ጦርነት መካከል ገብቼ ሳለሁ፣ አንድ ሰው ምርኮኛ ይዞ መጥቶ ‘ይህን ሰው ጠብቅ፤ ቢያመልጥ በገመዱ ትገባለህ ወይም አንድ መክሊት ብር ትከፍላለህ’ አለኝ። 40 ‘ታዲያ እኔ አገልጋይህ ሥራ በዝቶብኝ ወዲያ ወዲህ ስል ሰውየው አምልጦ ሄደ።’ ” የእስራኤልም ንጉሥ፣ “ራስህ ፈርደሃል፤ ይኸው ይፈጸምብሃል” አለው። 41 ከዚያም ነቢዩ መጠምጠሚያውን በፍጥነት ከዐይኑ ላይ አነሣ፤ የእስራኤልም ንጉሥ ያ ሰው ከነቢያት አንዱ መሆኑን ዐወቀ። 42 ነቢዩም ንጉሡን አለው፤ “እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ ‘እኔ ፈጽሞ ይገደል ያልሁትን ሰው ለቅቀኸዋልና በገመዱ ትገባለህ፤ በሕዝቡም ፈንታ ያንተ ሕዝብ በገመዱ ይገባል።’ ” 43 የእስራኤልም ንጉሥ ተበሳጭቶና ተቈጥቶ ሰማርያ ወዳለው ቤተ መንግሥቱ ሄደ። |
መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™
የቅጂ መብት © 2001, 2024 በBiblica, Inc.
በፈቃድ የሚወሰድ። በዓለም ዐቀፍ ባለቤትነቱ።
The Holy Bible, New Amharic Standard Version™
Copyright © 2001, 2024 by Biblica, Inc.
Used with permission. All rights reserved worldwide.
Biblica, Inc.