1 ነገሥት 15 - አዲሱ መደበኛ ትርጒምየይሁዳ ንጉሥ አብያ 15፥1-2 ፤ 15፥7-8 ተጓ ምብ – 2ዜና 13፥1-2 ፤ 13፥22–14፥1 1 የናባጥ ልጅ ኢዮርብዓም በነገሠ በዐሥራ ስምንተኛው ዓመት አብያ በይሁዳ ነገሠ፤ 2 በኢየሩሳሌም ተቀምጦም ሦስት ዓመት ገዛ፤ እናቱ መዓካ የተባለች የአቤሴሎም ልጅ ነበረች። 3 እርሱም አባቱ ከርሱ በፊት የሠራውን ኀጢአት ሁሉ ሠራ፤ እንደ አባቱ እንደ ዳዊትም በፍጹም ልቡ በታማኝነት ለእግዚአብሔር አልተገዛም። 4 ነገር ግን ከርሱ ቀጥሎ እንዲነግሥና ኢየሩሳሌምን እንዲያጸናት፣ አምላክ እግዚአብሔር ስለ ዳዊት ሲል በኢየሩሳሌም መብራት ሰጠው። 5 ዳዊት በኬጢያዊው በኦርዮ ላይ ካደረሰው በደል በቀር፣ በእግዚአብሔር ፊት ትክክል የሆነውን ነገር አድርጓል፤ በሕይወት ዘመኑም ሁሉ ከእግዚአብሔር ትእዛዝ ፈቀቅ ያለበት ጊዜ አልነበረም። 6 አብያም በሕይወት በነበረበት ዘመን ሁሉ በሮብዓምና በኢዮርብዓም መካከል ጦርነት ነበር። 7 ሌላው አብያ በዘመኑ የፈጸመውና ያደረገው ሁሉ፣ በይሁዳ ነገሥታት ታሪክ ተጽፎ የሚገኝ አይደለምን? በአብያና በኢዮርብዓም መካከልም ጦርነት ነበር። 8 አብያም ከአባቶቹ ጋራ አንቀላፋ፤ በዳዊትም ከተማ ተቀበረ። ልጁም አሳ በርሱ ፈንታ ነገሠ። የይሁዳ ንጉሥ አሳ 15፥23-24 ተጓ ምብ – 2ዜና 16፥11–17፥1 9 የእስራኤል ንጉሥ ኢዮርብዓም በነገሠ በሃያኛው ዓመት፣ አሳ የይሁዳ ንጉሥ ሆነ፤ 10 በኢየሩሳሌምም አርባ አንድ ዓመት ነገሠ፤ እናቱ መዓካ ትባላለች፤ እርሷም የአቤሴሎም ልጅ ነበረች። 11 አሳ አባቱ ዳዊት እንዳደረገው ሁሉ፣ በእግዚአብሔር ፊት መልካም የሆነውን ነገር አደረገ። 12 የቤተ ጣዖት ወንደቃዎችን ከምድሪቱ አባረረ፤ አባቶቹ የሠሯቸውን ጣዖታት ሁሉ አስወገደ። 13 አሳም ለአስጸያፊዋ የአሼራ ጣዖት ዐምድ በማቆሟ፣ አያቱን መዓካን ከእቴጌነቷ ሻራት፤ ጣዖቷንም በቄድሮን ሸለቆ አቃጠለው። 14 አሳ የማምለኪያ ኰረብቶችን ፈጽሞ ባያስወግድም እንኳ በዘመኑ ሁሉ፣ ልቡ ለእግዚአብሔር ፍጹም ነበር። 15 እርሱና አባቱ የቀደሱትን ብር፣ ወርቅና ልዩ ልዩ ዕቃዎችን ወደ እግዚአብሔር ቤተ መቅደስ አስገባ። 16 አሳና የእስራኤል ንጉሥ ባኦስ ዘመነ መንግሥታቸውን ያሳለፉት፣ እርስ በርስ በመዋጋት ነበር። 17 የእስራኤል ንጉሥ ባኦስ በይሁዳ ላይ ዘምቶ፣ ወደ ይሁዳ ንጉሥ ወደ አሳ ግዛት ማንም እንዳይገባና እንዳይወጣ ለመቈጣጠር ራማን ምሽግ አድርጎ ሠራት። 18 አሳም ከእግዚአብሔር ቤትና ከራሱም ቤተ መንግሥት ግምጃ ቤት የቀረውን ብርና ወርቅ በሙሉ ወሰደ፤ ከዚያም በሹማምቱ እጅ በደማስቆ ተቀምጦ ይገዛ ለነበረው፣ ለጠብሪሞን ልጅ፣ የአዚን የልጅ ልጅ ለሆነው ለሶርያ ንጉሥ ለቤን ሃዳድ ላከ። 19 “ቀድሞ በአባቴና በአባትህ መካከል የስምምነት ውል እንደ ነበረ ሁሉ፣ ዛሬም በእኔና በአንተ መካከል የስምምነት ውል ይኑር። እነሆ፤ የብርና ወርቅ ገጸ በረከት ልኬልሃለሁ። አሁንም ከእኔ ተመልሶ ይሄድ ዘንድ ከእስራኤል ንጉሥ ከባኦስ ጋራ ያደረግኸውን የስምምነት ውል አፍርስ” አለው። 20 ቤን ሃዳድም የንጉሥ አሳን ሐሳብ ተቀብሎ፣ የጦር አዛዦቹን በእስራኤል ከተሞች ላይ አዘመተ፤ እርሱም ዒዮንን፣ ዳንን፣ አቤል ቤት ማዕካን እንዲሁም ንፍታሌምን ጨምሮ ኪኔሬትን በሙሉ ድል አድርጎ ያዘ። 21 ባኦስም ይህን በሰማ ጊዜ፣ ራማን መገንባቱን አቁሞ ወደ ቴርሳ ተመለሰ። 22 ንጉሥ አሳ አንድም ሰው እንዳይቀር በይሁዳ ሁሉ ዐዋጅ አስነገረ፤ ከዚያም ሕዝቡ ባኦስ በራማ ሲሠራበት የነበረውን ድንጋይና ዕንጨት አጋዘ፤ በእነርሱም ንጉሡ አሳ የብንያምን ጌባዕና ምጽጳን ሠራበት። 23 በአሳ ዘመነ መንግሥት የተከናወነው ሌላው ነገር በሙሉ፣ ጀግንነቱ፣ ያደረገውም ሁሉና የሠራቸውም ከተሞች በይሁዳ ነገሥታት ታሪክ መጽሐፍ የተጻፉ አይደሉምን? ንጉሥ አሳ በሸመገለ ጊዜ ግን እግሮቹን ታመመ። 24 አሳ ከአባቶቹ ጋራ አንቀላፋ፤ እነርሱ በተቀበሩበትም በአባቱ በዳዊት ከተማ ተቀበረ፤ ልጁ ኢዮሣፍጥም በርሱ ፈንታ ነገሠ። የእስራኤል ንጉሥ ናዳብ 25 በይሁዳ ንጉሥ በአሳ ዘመነ መንግሥት በሁለተኛው ዓመት የኢዮርብዓም ልጅ ናዳብ በእስራኤል ላይ ነገሠ፤ ሁለት ዓመትም ገዛ። 26 እርሱም በአባቱ መንገድ በመሄድ፣ አባቱ የሠራውንና እስራኤልም እንዲሠሩ ያደረገውን ኀጢአት በመሥራት በእግዚአብሔር ፊት ክፉ ድርጊት ፈጸመ። 27 ናዳብና መላው እስራኤል በፍልስጥኤም የምትገኘውን የገባቶንን ከተማ ከብበው ሳሉ፣ ከይሳኮር ነገድ የተወለደው የአኪያ ልጅ ባኦስ ዐምፆ በመነሣት ናዳብን በገባቶን ገደለው። 28 ባኦስ ናዳብን የገደለውና በእግሩ ተተክቶ የነገሠው፣ የይሁዳ ንጉሥ አሳ በነገሠ በሦስተኛው ዓመት ነው። 29 ወዲያውኑ እንደ ነገሠም የኢዮርብዓምን ቤተ ሰብ በሙሉ ፈጀ። እግዚአብሔር በሴሎናዊው ባሪያው በአኪያ በኩል እንደ ተናገረው፣ ከኢዮርብዓም ቤተ ሰብ አንድም ሰው በሕይወት ሳያስቀር፣ ሁሉንም አጠፋቸው፤ 30 ይህም የሆነው ኢዮርብዓም በሠራው ኀጢአትና እስራኤልም እንዲሠሩ በማድረጉ ምክንያት፣ የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔርን ለቍጣ በማነሣሣቱ ነው። 31 ሌላው በናዳብ ዘመነ መንግሥት የተከናወነው፣ እርሱም ያደረገው ሁሉ በእስራኤል ነገሥታት ታሪክ ተጽፎ የሚገኝ አይደለምን? 32 አሳና የእስራኤል ንጉሥ ባኦስ ዘመነ መንግሥታቸውን ያሳለፉት እርስ በርስ በመዋጋት ነበር። የእስራኤል ንጉሥ ባኦስ 33 የይሁዳ ንጉሥ አሳ በነገሠ በሦስተኛው ዓመት የአኪያ ልጅ ባኦስ በቴርሳ ከተማ፣ በእስራኤል ሁሉ ላይ ነገሠ፤ ሃያ አራት ዓመትም ገዛ። 34 በኢዮርብዓም መንገድ በመሄድና እስራኤልም እንዲሠሩ ያደረገውን ኀጢአት በመፈጸም በእግዚአብሔር ፊት ክፉ ሥራ ሠራ። |
መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™
የቅጂ መብት © 2001, 2024 በBiblica, Inc.
በፈቃድ የሚወሰድ። በዓለም ዐቀፍ ባለቤትነቱ።
The Holy Bible, New Amharic Standard Version™
Copyright © 2001, 2024 by Biblica, Inc.
Used with permission. All rights reserved worldwide.
Biblica, Inc.