Biblia Todo Logo
在线圣经

- 广告 -

1 ነገሥት 14 - አዲሱ መደበኛ ትርጒም


አኪያ በኢዮርብዓም ላይ የተናገረው ትንቢት

1 በዚያ ጊዜ የኢዮርብዓም ልጅ አብያ ታመመ፤

2 ኢዮርብዓም ሚስቱን እንዲህ አላት፤ “ተነሺ፣ የኢዮርብዓም ሚስት መሆንሽ እንዳይታወቅብሽ ሆነሽ፣ ወደ ሴሎ ሂጂ፤ በዚህ ሕዝብ ላይ እንደምነግሥ የነገረኝ ነቢይ አኪያ እነሆ፤ በዚያ ይገኛል።

3 ስትሄጂም ዐሥር እንጀራ፣ ጥቂት ሙልሙል ዳቦ እና አንድ እንስራ ማር ይዘሽ ሂጂ፤ እርሱም በልጁ ላይ የሚደርሰውን ይነግርሻል።”

4 ስለዚህ የኢዮርብዓም ሚስት ያላትን አድርጋ በሴሎ ወደሚገኘው ወደ አኪያ ቤት ሄደች። በዚህ ጊዜ አኪያ ከማርጀቱ የተነሣ ዐይኖቹ ፈዝዘው ነበር።

5 እግዚአብሔር ግን ለአኪያ፣ “እነሆ፤ የኢዮርብዓም ሚስት ስለ ታመመው ልጇ ልትጠይቅህ ሌላ ሴት መስላ ትመጣለችና እንዲህ ብለህ መልሳት” ብሎ ነገረው።

6 አኪያም የእግሯን ኮቴ ድምፅ እበሩ ላይ እንደ ሰማ እንዲህ አላት፤ “የኢዮርብዓም ሚስት ሆይ ግቢ፤ ግን ለምንድን ነው ሌላ ሴት መስለሽ ለመታየት የፈለግሽው? ለአንቺ ከባድ ነገር እንድነግርሽ ተልኬአለሁ።

7 አሁንም ሂጂና ኢዮርብዓምን የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር የሚለው ይህ ነው ብለሽ ንገሪው፤ ‘ከሕዝቡ መካከል አንሥቼ የሕዝቤ የእስራኤል መሪ አደረግሁህ፤

8 ከዳዊት ቤት መንግሥቱን ቀድጄ ለአንተ ሰጠሁህ፤ አንተ ግን በፊቴ መልካም ነገር በማድረግ ብቻ ትእዛዜን እንደ ጠበቀው፣ በፍጹም ልቡም እንደ ተከተለኝ እንደ ባሪያዬ እንደ ዳዊት አልሆንህም።

9 ከአንተ በፊት ከነበሩት ሁሉ ይልቅ አንተ የከፋ ሥራ ሠራህ፤ ለራስህም ከቀለጠ ብረት ሌሎች አማልክትን ሠራህ፤ ቍጣዬን አነሣሣህ፤ ወደ ኋላህም ጣልኸኝ።

10 “ ‘ስለዚህ እኔም በኢዮርብዓም ቤት ላይ ጥፋትን አመጣለሁ፤ ባሪያም ይሁን ነጻ ዜጋ የኢዮርብዓምን ወንድ ልጅ ሁሉ ከእስራኤል አስወግዳለሁ፤ ኩበትም ዐመድ እስኪሆን ድረስ እንደሚቃጠል፣ እኔም የኢዮርብዓምን ቤት እንዲሁ አቃጥላለሁ።

11 ከኢዮርብዓም ወገን በከተማ የሞተውን ውሾች፣ በባላገር የሞተውን ደግሞ የሰማይ አሞሮች ይበሉታል፤ እግዚአብሔር ተናግሯልና!’

12 “እንግዲህ አንቺም ወደ ቤትሽ ሂጂ፤ የምትኖሪበትን ከተማ እግርሽ እንደ ረገጠ፣ ልጁ ይሞታል፤

13 እስራኤልም ሁሉ አልቅሰው ይቀብሩታል። የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር ከኢዮርብዓም ቤት ሁሉ መልካም ነገር ያገኘበት እርሱ ብቻ ስለ ሆነ፣ በወግ በማዕርግ የሚቀበር እርሱ ብቻ ነው።

14 “ከዚህም በላይ፣ እግዚአብሔር የኢዮርብዓምን ቤተ ሰብ የሚያስወግድ ንጉሥ በእስራኤል ላይ ለራሱ ያስነሣል፤ ይህም ዛሬ፣ አሁኑኑ ይሆናል።

15 እግዚአብሔር እስራኤልን በውሃ ውስጥ እንደሚንቀጠቀጥ ሸንበቆ ያንቀጠቅጠዋል፤ የአሼራን ምስል ዐምድ በመሥራት እግዚአብሔርን ለቍጣ ያነሣሡት ስለ ሆነ፣ እግዚአብሔር ለቀድሞ አባቶቻቸው ከሰጣቸው ከዚህች ከመልካሚቱ ምድር እስራኤልን ይነቅላቸዋል፤ ከወንዙም ማዶ ይበትናቸዋል።

16 ኢዮርብዓም ኀጢአት ሠርቶ፣ እስራኤልንም እንዲሠሩ በማድረጉ፣ እግዚአብሔር እስራኤልን ይተዋቸዋል።”

17 የኢዮርብዓም ሚስትም ተነሥታ ወደ ቴርሳ ሄደች፤ የቤቱን መድረክ ወዲያው እንደ ተራመደች ልጁ ሞተ፤

18 ከዚያም ቀበሩት፤ እግዚአብሔር በባሪያው በአኪያ አማካይነት እንደ ተናገረ፣ እስራኤል ሁሉ አለቀሱለት።

19 የቀረው የኢዮርብዓም ታሪክ፣ ያደረገው ጦርነትና አገዛዙም ሁሉ በእስራኤል ነገሥታት ታሪክ ተጽፏል።

20 ኢዮርብዓምም ሃያ ሁለት ዓመት ነግሦ ከአባቶቹ ጋራ አንቀላፋ፤ ልጁ ናዳብም በእግሩ ተተክቶ ነገሠ።


የይሁዳ ንጉሥ ሮብዓም
14፥21 ፤ 14፥25-31 ተጓ ምብ – 2ዜና 12፥9-16

21 የሰሎሞን ልጅ ሮብዓም በይሁዳ ነገሠ፤ በነገሠም ጊዜ ዕድሜው አርባ አንድ ዓመት ነበር፤ እርሱም እግዚአብሔር ስሙን በዚያ ለማኖር ከእስራኤል ነገዶች ሁሉ በመረጣት በኢየሩሳሌም ከተማ ተቀምጦም ዐሥራ ሰባት ዓመት ገዛ። እናቱም ናዓማ የተባለች አሞናዊት ነበረች።

22 ይሁዳ በእግዚአብሔር ፊት ክፉ ነገር አደረገ፤ ከአባቶቻቸው ይልቅ እነርሱ በሠሩት ኀጢአት ይበልጥ የቅናት ቍጣውን አነሣሡ፤

23 እንዲሁም በእያንዳንዱ ኰረብታና በየትልልቁ ዛፍ ጥላ ሥር የማምለኪያ ኰረብቶችን አዕማደ ጣዖታት፣ የአሼራን ምስል ዐምድ ለራሳቸው አቆሙ።

24 ከዚያም ይልቅ፣ የቤተ ጣዖት ወንደቃዎች በምድሪቱ ላይ ነበሩ፤ እግዚአብሔር ከእስራኤላውያን ፊት አሳድዶ ያስወጣቸው አሕዛብ የፈጸሙትን አስጸያፊ ድርጊት ሁሉ እነዚህም ፈጸሙ።

25 ሮብዓም በነገሠ በዐምስተኛው ዓመት፣ የግብጽ ንጉሥ ሺሻቅ በኢየሩሳሌም ላይ ዘመተ፤

26 የእግዚአብሔርን ቤተ መቅደስ ንብረትና የቤተ መንግሥቱን ንብረት ዘርፎ ወሰደ፤ ሰሎሞን ያሠራው የወርቅ ጋሻ፤ ሰሎሞን ያሠራቸው የወርቅ ጋሻዎች ሁሉ እንኳ ሳይቀሩ ሁሉንም ነገር አጋዘ።

27 ስለዚህ ንጉሥ ሮብዓም እነዚህን ለመተካት ሲል፣ የናስ ጋሻዎች ሠርቶ የቤተ መንግሥቱን ቅጥር በር ለሚጠብቁ የዘብ አለቆች በኀላፊነት ሰጠ።

28 ንጉሡ ወደ እግዚአብሔር ቤተ መቅደስ በሚሄድበት ጊዜ ሁሉ፣ ዘቦቹ ጋሻዎቹን አንግበው ያጅቡት ነበር፤ ከዚያም በዘብ ጥበቃው ክፍል መልሰው ያስቀምጡ ነበር።

29 የቀረው የሮብዓም አገዛዝ፣ ያደረገውም ሁሉ በይሁዳ ነገሥታት ታሪክ ተጽፎ የሚገኝ አይደለምን?

30 በሮብዓምና በኢዮርብዓም መካከል የማያቋርጥ ጦርነት ነበር።

31 ሮብዓምም ከአባቶቹ ጋራ አንቀላፋ፤ እነርሱ በተቀበሩበትም በዳዊት ከተማ ተቀበረ። እናቱ ናዓማ የተባለች አሞናዊት ነበረች። ልጁ አብያም በርሱ ፈንታ ነገሠ።

መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™

የቅጂ መብት © 2001, 2024 በBiblica, Inc.

በፈቃድ የሚወሰድ። በዓለም ዐቀፍ ባለቤትነቱ።

The Holy Bible, New Amharic Standard Version™

Copyright © 2001, 2024 by Biblica, Inc.

Used with permission. All rights reserved worldwide. 

Biblica, Inc.
跟着我们:



广告