1 ነገሥት 13 - አዲሱ መደበኛ ትርጒምከይሁዳ የመጣ የእግዚአብሔር ሰው 1 ኢዮርብዓም መሥዋዕት ለማቅረብ በመሠዊያው አጠገብ ቆሞ ሳለ፣ በእግዚአብሔር ቃል ታዝዞ አንድ የእግዚአብሔር ሰው ከይሁዳ ወደ ቤቴል መጣ። 2 መሠዊያውንም በእግዚአብሔር ቃል በመቃወም እንዲህ አለ፤ “አንተ መሠዊያ ሆይ! እንግዲህ እግዚአብሔር የሚለው ይህ ነው፤ ‘እነሆ፤ ኢዮስያስ የተባለ ለዳዊት ቤት ይወለዳል፤ እርሱም አሁን እዚህ መሥዋዕት የሚያቀርቡትን የኰረብታ ማምለኪያ ካህናት በላይህ ይሠዋቸዋል፤ የሰዎችም ዐጥንት በአንተ ላይ ይነድዳል።’ ” 3 በዚያች ዕለት ያ የእግዚአብሔር ሰው፣ እንዲህ ሲል ምልክት ሰጠ፤ “እግዚአብሔር የሰጠውም ምልክት፣ ‘እነሆ፣ መሠዊያው ይሰነጠቃል፤ በላዩም ላይ ያለው ዐመድ ይፈስሳል’ ” የሚል ነው። 4 ንጉሥ ኢዮርብዓምም ያ የእግዚአብሔር ሰው በቤቴል መሠዊያ ላይ ጮኾ የተናገረውን ሲሰማ፣ እጁን መሠዊያው ካለበት በመዘርጋት፣ “ያዙት!” አለ፤ ነገር ግን ያች የዘረጋት እጁ ደርቃ ቀረች፤ ሊመልሳትም አልቻለም 5 እንዲሁም ያ የእግዚአብሔር ሰው በእግዚአብሔር ቃል ተመርቶ በሰጠው ምልክት መሠረት መሠዊያው ተሰነጠቀ፤ ዐመዱም ፈሰሰ። 6 ከዚያም ንጉሡ የእግዚአብሔርን ሰው፣ “እጄ ወደ ቦታዋ እንድትመለስ ወደ አምላክህ ወደ እግዚአብሔር ለምንልኝ፤ ጸልይልኝም” አለው፤ ስለዚህም የእግዚአብሔር ሰው እግዚአብሔርን ለመነ፤ የንጉሡ እጅ ወደ ቦታዋ ተመለሰች፤ እንደ ቀድሞዋም ሆነች። 7 ንጉሡም የእግዚአብሔርን ሰው፣ “ዐብረኸኝ ወደ ቤት እንሂድ፤ አንድ ነገር ቅመስ፤ ስጦታም አደርግልሃለሁ” አለው። 8 የእግዚአብሔር ሰው ግን ለንጉሡ እንዲህ ሲል መለሰለት፤ “ግማሽ ሀብትህን ብትሰጠኝ እንኳ፣ ዐብሬህ አልሄድም፤ እዚህ፣ እንጀራ አልበላም፤ ውሃም አልጠጣም። 9 በእግዚአብሔር ቃል፤ ‘እንጀራ እንዳትበላ፣ ውሃም እንዳትጠጣ፣ በሄድህበትም መንገድ እንዳትመለስ’ ተብዬ ታዝዣለሁና።” 10 ስለዚህም በመጣበት ሳይሆን በሌላ መንገድ ወደ ቤቴል ተመለሰ። 11 በዚያ ጊዜ በቤቴል የሚኖር አንድ ሽማግሌ ነቢይ ነበር፤ ልጆቹም መጥተው በዚያች ዕለት የእግዚአብሔር ሰው እዚያ ያደረገውን ሁሉና ንጉሡንም ምን እንዳለው ለአባታቸው ነገሩት። 12 አባታቸውም፣ “ለመሆኑ የተመለሰው በየትኛው መንገድ ነው?” በማለት ጠየቃቸው፤ ልጆቹም ከይሁዳ የመጣው የእግዚአብሔር ሰው የተመለሰበትን መንገድ ለአባታቸው አሳዩት። 13 ስለዚህም ልጆቹን፣ “በሉ አህያውን ጫኑልኝ” አላቸው። እነርሱም አህያውን ጫኑለትና ተቀምጦበት 14 እየጋለበ ያን የእግዚአብሔር ሰው ተከተለው። ከዚያም በአንድ የወርካ ዛፍ ሥር ተቀምጦ አገኘውና፣ “ከይሁዳ የመጣኸው የእግዚአብሔር ሰው አንተ ነህን?” ሲል ጠየቀው። እርሱም፣ “አዎን እኔ ነኝ” ብሎ መለሰለት። 15 ስለዚህ ነቢዩ፣ “ዐብረን ወደ ቤት እንሂድና ምግብ ብላ” አለው። 16 የእግዚአብሔርም ሰው እንዲህ ሲል መለሰለት፤ “ተመልሼ ከአንተ ጋራ አልሄድም፤ በዚህ ቦታም ዐብሬህ እንጀራ አልበላም፤ ውሃም አልጠጣም፤ 17 ‘እዚያ እንጀራ እንዳትበላ፣ ውሃም እንዳትጠጣ፣ በሄድህበትም መንገድ እንዳትመለስ’ ተብዬ በእግዚአብሔር ቃል ታዝዣለሁና” አለው። 18 ሽማግሌው ነቢይ ግን፣ “እኔም እኮ እንደ አንተው ነቢይ ነኝ፤ መልአክ በእግዚአብሔር ቃል፣ ‘እንጀራ እንዲበላና ውሃ እንዲጠጣ መልሰህ ወደ ቤትህ አምጣው’ ብሎኝ ነው” አለው፤ ነገር ግን ውሸቱን ነበር። 19 ስለዚህ የእግዚአብሔርም ሰው ዐብሮት ተመልሶ በቤቱ በላ፤ ጠጣም። 20 በማእድ ተቀምጠው ሳሉ፣ የእግዚአብሔር ቃል መልሶ ወደ አመጣው ወደ ሽማግሌው ነቢይ መጣ፤ 21 ከይሁዳ ለመጣውም የእግዚአብሔር ሰው፣ “እግዚአብሔር የሚለው ይህ ነው፣ ‘የእግዚአብሔርን ቃል አቃልለሃል፤ አምላክህ እግዚአብሔር የሰጠህንም ትእዛዞች አልጠበቅህም፤ 22 ተመልሰህ በመምጣት እንዳትበላና እንዳትጠጣ በነገረህ ቦታ እንጀራ በላህ፤ ውሃም ጠጣህ። ስለዚህ ሬሳህ በአባቶችህ መቃብር አይቀበርም’ ” ሲል ጮኾ ተናገረው። 23 የእግዚአብሔርም ሰው በልቶና ጠጥቶ ካበቃ በኋላ፣ ያ መልሶ ያመጣው ነቢይ አህያውን ጫነለት። 24 ሲሄድ ሳለም አንበሳ መንገድ ላይ አግኝቶ ገደለው፤ ሬሳውም በመንገድ ላይ ተጋደመ፤ አህያውና አንበሳውም አጠገቡ ቆመው ነበር። 25 በዚያ ያለፉ ሰዎች ሬሳው በመንገድ ላይ ተጋድሞ፣ አንበሳውም አጠገቡ ቆሞ ስላዩ፣ ሽማግሌው ነቢይ ወዳለበት ከተማ ሄደው ይህንኑ ተናገሩ። 26 ያም ከመንገድ የመለሰው ነቢይ ይህን ሲሰማ፣ “ይህ የእግዚአብሔርን ቃል ያቃለለው ያ የእግዚአብሔር ሰው ነው፤ እግዚአብሔር ባስጠነቀቀው ቃል መሠረት አሳልፎ ሰጥቶት አንበሳ ሰብሮ ገድሎታል” አለ። 27 ከዚያም ነቢዩ ልጆቹን፣ “በሉ አህያ ጫኑልኝ” አላቸውና ጫኑለት። 28 ከዚያም ሄዶ ሬሳው መንገድ ላይ ተጋድሞ አንበሳውና አህያው በአጠገቡ ቆመው አገኘ፤ አንበሳው ሬሳውን አልበላውም፤ አህያውንም አልሰበረውም። 29 ስለዚህ፣ ነቢዩ የዚያን የእግዚአብሔር ሰው ሬሳ አንሥቶ በአህያው ላይ ጫነ፤ አልቅሶ ለመቅበርም ራሱ ወደሚኖርበት ከተማ አመጣው። 30 ከዚያም ሬሳውን በራሱ መቃብር ቀበረው፤ “ዋይ ወንድሜን” እያሉም አለቀሱለት። 31 ከቀበሩትም በኋላ ልጆቹን እንዲህ አላቸው፤ “እኔም በምሞትበት ጊዜ የእግዚአብሔር ሰው በተቀበረበት መቃብር ቅበሩኝ፤ ዐጥንቶቼንም በዐጥንቶቹ አጠገብ አኑሩ። 32 በቤቴል ባለው መሠዊያ፣ በሰማርያ ከተሞችና በየኰረብታው ባሉ ማምለኪያ ስፍራዎች ላይ በእግዚአብሔር ቃል ጮኾ ያሰማው መልእክት በትክክል የሚፈጸም ነውና።” 33 ይህም ሁሉ ሆኖ ኢዮርብዓም ከክፉ መንገዱ አልተመለሰም፤ ይልቁንም በኰረብታ ማምለኪያዎች ከሁሉም የሕዝብ ክፍል እንደ ገና ካህናትን ይሾም ጀመር፤ ካህን ለመሆን የሚፈልገውንም ሁሉ ለየኰረብታ ማምለኪያዎቹ ለየ። 34 ይህም ኀጢአት የኢዮርብዓም ቤት እንዲወድቅና ከምድር ገጽም እንዲደመሰስ ምክንያት ሆነ። |
መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™
የቅጂ መብት © 2001, 2024 በBiblica, Inc.
በፈቃድ የሚወሰድ። በዓለም ዐቀፍ ባለቤትነቱ።
The Holy Bible, New Amharic Standard Version™
Copyright © 2001, 2024 by Biblica, Inc.
Used with permission. All rights reserved worldwide.
Biblica, Inc.