Biblia Todo Logo
在线圣经

- 广告 -

1 ነገሥት 10 - አዲሱ መደበኛ ትርጒም


ንግሥተ ሳባ ሰሎሞንን እንደ ጐበኘች
10፥1-13 ተጓ ምብ – 2ዜና 9፥1-12

1 የሳባ ንግሥት የሰሎሞንን ዝና እና ከእግዚአብሔር ስም ጋራ ያለውን ግንኙነት በሰማች ጊዜ፣ አስቸጋሪ በሆኑ ጥያቄዎች ልትፈትነው መጣች።

2 ታላቅ አጀብ አስከትላ ሽቱ፣ እጅግ ብዙ ወርቅና የከበሩ ድንጋዮችን በግመሎች አስጭና ኢየሩሳሌም ከደረሰች በኋላ፣ ወደ ሰሎሞን ገብታ በልቧ ያለውን ጥያቄ ሁሉ አቀረበችለት።

3 ሰሎሞንም የጠየቀችውን ሁሉ መለሰላት፤ ከንጉሡ የተሰወረና ሊመልስላት ያልቻለው አንድም ጥያቄ አልነበረም።

4 የሳባ ንግሥት የሰሎሞንን ጥበብ ሁሉ፣ የሠራውንም ቤተ መንግሥት ስትመለከት

5 እንዲሁም በገበታው ላይ የሚቀርበውን መብል፣ የሹማምቱን አቀማመጥ፣ የአስተናባሪዎቹን አቋቋምና የደንብ ልብሳቸውን፣ ጠጅ አሳላፊዎቹን፣ እንዲሁም በእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ያቀረባቸውን የሚቃጠሉ መሥዋዕቶች ባየች ጊዜ እጅግ ተደነቀች።

6 ንጉሡንም እንዲህ አለችው፤ “ስለ ተናገርሃቸው ነገሮችና ስለ ጥበብህ በአገሬ ሳለሁ የሰማሁት እውነት ነው፤

7 ይሁን እንጂ፣ መጥቼ እነዚህን ነገሮች በዐይኔ እስካይ ድረስ የተነገረኝን አላመንሁም ነበር፤ በርግጥ ግማሹ እንኳ አልተነገረኝም፤ ጥበብህና ብልጽግናህ ከሰማሁት እጅግ ይልቃል።

8 ሰዎችህ እንዴት ብፁዓን ናቸው! ዘወትር በፊትህ ቆመው ጥበብህን የሚሰሙ ሹማምትህ ምንኛ ብፁዓን ናቸው!

9 በአንተ ደስ ተሰኝቶ በእስራኤል ዙፋን ላይ ያስቀመጠህ እግዚአብሔር አምላክህ ቡሩክ ይሁን፤ እግዚአብሔር በዘላለም ፍቅሩም እስራኤልን ከመውደዱ የተነሣ፣ ፍትሕና ጽድቅ እንዲሰፍን አንተን ንጉሥ አደረገህ።”

10 ከዚያም ለንጉሡ አንድ መቶ ሃያ መክሊት ወርቅ፣ እጅግ ብዙ ቅመማ ቅመሞችና የከበሩ ድንጋዮች ሰጠችው፤ የሳባ ንግሥት ለንጉሥ ሰሎሞን ያበረከተችለትን ያን ያህል ብዛት ያለው ቅመማ ቅመም ከዚያ በኋላ ከቶ አልመጣም።

11 ከኦፊር ወርቅ ያመጡት የኪራም መርከቦች፣ እጅግ ብዙ የሰንደል ዕንጨትና የከበሩ ድንጋዮች አመጡ።

12 ንጉሡም የሰንደሉን ዕንጨት ለእግዚአብሔር ቤተ መቅደስና ለቤተ መንግሥቱ መደገፊያ፣ ለመዘምራኑ የመሰንቆና የበገና መሥሪያ አደረገው። ይህን ያህል ብዛት ያለው የሰንደል ዕንጨት እስከ ዛሬ ድረስ ከቶ አልመጣም፤ አልታየምም።

13 ንጉሥ ሰሎሞንም ለሳባ ንግሥት ከቤተ መንግሥቱ በልግስና ከሚሰጣት ሌላ፣ የፈለገችውንና የጠየቀችውን ሁሉ ሰጣት፤ ከዚያም ከአጃቢዎቿ ጋራ ወደ አገሯ ተመለሰች።


የሰሎሞን ብልጽግናና ክብር
10፥14-29 ተጓ ምብ – 2ዜና 1፥14-17 ፤ 9፥13-28

14 ለሰሎሞን በየዓመቱ የሚገባለት ስድስት መቶ ስድሳ ስድስት መክሊት የሚመዝን ወርቅ ነበር።

15 ይህም ከታላላቅና ከተራ ነጋዴዎች ከሚገባው ቀረጥ፣ መላው የዐረብ ነገሥታት ከሚያስገቡትና አገረ ገዦች ከሚሰበስቡት ግብር ሌላ ነበር።

16 ንጉሥ ሰሎሞን ከጥፍጥፍ ወርቅ ሁለት መቶ ትላልቅ ጋሻዎችን አበጀ፤ በእያንዳንዱም ጋሻ የገባው ስድስት መቶ ሰቅል ጥፍጥፍ ወርቅ ነበር።

17 እንዲሁም ከጥፍጥፍ ወርቅ ሦስት መቶ ትንንሽ ጋሻዎችን አበጀ፤ በእያንዳንዱ ጋሻ የገባው ጥፍጥፍ ወርቅ ሦስት ምናን ነበር። ንጉሡም ጋሻዎቹን የሊባኖስ ደን በተባለው ቤተ መንግሥት ውስጥ አኖረ።

18 ከዚያም ንጉሡ በዝኆን ጥርስ ትልቅ ዙፋን ሠርቶ በንጹሕ ወርቅ ለበጠው።

19 ዙፋኑ ባለስድስት ደረጃ ነው፤ በስተ ኋላውም ዐናቱ ላይ ክብ ቅርጽ ሲኖረው፣ ግራና ቀኙ ባለመደገፊያ ነው፤ መቀመጫውም ግራና ቀኙ መደገፊያ ያለው ሲሆን፣ በመደገፊያዎቹም አጠገብ ሁለት አንበሶች ቆመዋል።

20 በስድስቱም ደረጃዎች ጫፍ ላይ ግራና ቀኝ ዐሥራ ሁለት አንበሶች ቆመዋል። ይህን የመሰለ ዙፋን በማንኛውም አገር መንግሥት ተሠርቶ አያውቅም።

21 ንጉሥ ሰሎሞን የሚጠጣባቸው ዕቃዎች በሙሉ ከወርቅ የተሠሩ ነበሩ፤ “የሊባኖስ ደን” ተብሎ በሚጠራው ቤተ መንግሥት ውስጥ የነበሩትም ዕቃዎች ሁሉ ከንጹሕ ወርቅ የተሠሩ ነበሩ፤ በሰሎሞን ዘመን ብር ዋጋ እንደሌለው ስለሚቈጠር ከብር የተሠራ አንድም ነገር አልነበረም።

22 ንጉሡ ከኪራም መርከቦች ጋራ ዐብረው በባሕር ላይ የሚጓዙ የተርሴስ የንግድ መርከቦች ነበሩት። እነዚህም በየሦስት ዓመቱ አንድ ጊዜ ወርቅ፣ ብርና የዝሆን ጥርስ፣ ጦጣዎችና ዝንጀሮዎች ያመጡ ነበር።

23 ንጉሥ ሰሎሞን በሀብትም ሆነ በጥበብ ከምድር ነገሥታት ሁሉ ይበልጥ ነበር።

24 ዓለሙ ሁሉ እግዚአብሔር በልቡ ያኖረውን ጥበብ ለመስማት ከሰሎሞን ጋራ መገናኘት ይፈልግ ነበር።

25 በየዓመቱም የሚመጣው ሰው ሁሉ የብርና የወርቅ ዕቃ፣ ልብስ፣ የጦር መሣሪያ፣ ቅመማ ቅመም፣ ፈረስና በቅሎ ስጦታ አድርጎ ያመጣለት ነበር።

26 ሰሎሞን ሠረገሎችንና ፈረሶችን ሰበሰበ፤ እርሱም አንድ ሺሕ አራት መቶ ሠረገሎችና ዐሥራ ሁለት ሺሕ ፈረሶች ነበሩት፤ እነርሱንም በሠረገላ ከተሞችና ንጉሡ ባለበት በኢየሩሳሌም ከተማ አኖራቸው።

27 ንጉሡ በኢየሩሳሌም ብሩን እንደ ማንኛውም ድንጋይ፣ የዝግባውንም ዕንጨት ብዛት በየኰረብታው ግርጌ እንደሚበቅል ሾላ አደረገው።

28 የሰሎሞን ፈረሶች የመጡት ከግብጽና ከቀዌ ሲሆን፣ ከቀዌ የገዟቸውም የንጉሡ ነጋዴዎች ነበሩ።

29 ከግብጽ ያስመጧቸውም አንዱን ሠረገላ በስድስት መቶ ሰቅል ብር፣ አንዱን ፈረስ በአንድ መቶ ዐምሳ ሰቅል ብር ገዝተው ነው። እነዚህንም ደግሞ ለኬጢያውያንና ለሶርያውያን ነገሥታት ሁሉ ይሸጡላቸው ነበር።

መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™

የቅጂ መብት © 2001, 2024 በBiblica, Inc.

በፈቃድ የሚወሰድ። በዓለም ዐቀፍ ባለቤትነቱ።

The Holy Bible, New Amharic Standard Version™

Copyright © 2001, 2024 by Biblica, Inc.

Used with permission. All rights reserved worldwide. 

Biblica, Inc.
跟着我们:



广告