Biblia Todo Logo
在线圣经

- 广告 -

1 ቆሮንቶስ 11 - አዲሱ መደበኛ ትርጒም

1 እኔ የክርስቶስን ምሳሌ እንደምከተል እናንተም የእኔን ተከተሉ።


ሥርዐት ያለው አምልኮ

2 በሁሉም ነገር ስለምታስቡልኝና ከእኔ የተቀበላችሁትን ትምህርት አጥብቃችሁ ስለ ያዛችሁ አመሰግናችኋለሁ።

3 ነገር ግን ይህን እንድታውቁ እወድዳለሁ፤ የወንድ ሁሉ ራስ ክርስቶስ ነው፤ የሴትም ራስ ወንድ ነው፤ የክርስቶስም ራስ እግዚአብሔር ነው።

4 ራሱን ተከናንቦ የሚጸልይ ወይም ትንቢት የሚናገር ማንኛውም ወንድ የርሱን ራስ ያዋርዳል፤

5 ራሷን ሳትሸፍን የምትጸልይ ወይም ትንቢት የምትናገር ማንኛዋም ሴት የእርሷን ራስ ታዋርዳለች፤ ጠጕሯን እንደ ተላጨች ይቈጠራልና።

6 ሴት ራሷን የማትሸፍን ከሆነ፣ ጠጕሯን ትቈረጥ፤ ጠጕሯን መቈረጥ ወይም መላጨት የሚያሳፍር መስሎ ከታያት ግን ራሷን ትሸፈን።

7 ወንድ ራሱን መከናነብ የለበትም፤ ወንድ የእግዚአብሔር ምሳሌና ክብር ነውና፤ ሴት ግን የወንድ ክብር ናት፤

8 ምክንያቱም ሴት ከወንድ ተገኘች እንጂ ወንድ ከሴት አልተገኘም።

9 ደግሞም ሴት ለወንድ ተፈጠረች እንጂ ወንድ ለሴት አልተፈጠረም።

10 በዚህ ምክንያት፣ በመላእክትም ምክንያት፣ ሴት በሥልጣን ሥር መሆኗን የሚያሳይ ምልክት በራሷ ላይ ታድርግ።

11 በጌታ ዘንድ ግን ሴት ያለ ወንድ፣ ወንድም ያለ ሴት አይሆንም።

12 ሴት ከወንድ እንደ ተገኘች ሁሉ፣ ወንድም ከሴት ይወለዳልና፤ ነገር ግን የሁሉም መገኛ እግዚአብሔር ነው።

13 እስኪ እናንተ ፍረዱ፤ ሴት ራሷን ሳትሸፍን ወደ እግዚአብሔር መጸለይ ይገባታልን?

14 ወንድ ጠጕሩን ቢያስረዝም ነውር እንደሚሆንበት ተፈጥሮ እንኳ አያስተምራችሁምን?

15 ሴት ግን ጠጕሯን ብታስረዝም ክብሯ አይደለምን? ረዥም ጠጕር የተሰጣት መጐናጸፊያ እንዲሆናት ነውና።

16 እንግዲህ ማንም በዚህ ጕዳይ ላይ መከራከር ቢፈልግ፣ እኛም ሆንን የእግዚአብሔር አብያተ ክርስቲያናት ከዚህ የተለየ ልማድ የለንም።


የጌታ እራት
11፥23-25 ተጓ ምብ – ማቴ 26፥26-28 ፤ ማር 14፥22-24 ፤ ሉቃ 22፥17-20

17 ነገር ግን በምትሰበሰቡበት ጊዜ ለሚጐዳ እንጂ ለሚጠቅም ስላልሆነ፣ ይህን ትእዛዝ ስሰጥ እያመሰገንኋችሁ አይደለም።

18 ከሁሉ አስቀድሞ በቤተ ክርስቲያን በምትሰበሰቡበት ጊዜ በመካከላችሁ መለያየት እንዳለ ሰምቻለሁ፤ ይህም ሊሆን እንደሚችል በከፊል አምናለሁ።

19 ከእናንተ መካከል እውነተኞቹ ተለይተው ይታወቁ ዘንድ፣ ይህ መለያየት በመካከላችሁ መኖሩ የግድ ነው።

20 በምትሰበሰቡበት ጊዜ የምትበሉት የጌታን እራት አይደለም፤

21 በምትበሉበት ጊዜ አንዱ ሌላውን ሳይጠብቅ ምግቡን ይበላልና፤ አንዱ እየተራበ ሌላው ይሰክራል።

22 ለመሆኑ የምትበሉበትና የምትጠጡበት ቤት የላችሁምን? ወይስ የእግዚአብሔርን ቤተ ክርስቲያን በመናቅ፣ ምንም የሌላቸውን ታሳፍራላችሁን? እንግዲህ ምን ልበላችሁ? በዚህ ነገር ላመስግናችሁን? ፈጽሞ አላመሰግናችሁም!

23 እኔ ከጌታ የተቀበልሁትን ለእናንተ አስተላልፌአለሁና፤ ጌታ ኢየሱስ ዐልፎ በተሰጠባት ሌሊት እንጀራን አንሥቶ

24 ከባረከ በኋላ ቈርሶ፣ “ይህ ስለ እናንተ የሚሆን ሥጋዬ ነው፤ ለመታሰቢያዬም አድርጉት” አለ።

25 እንዲሁም ከእራት በኋላ ጽዋውን አንሥቶ፣ “ይህ ጽዋ በደሜ የሚሆን አዲስ ኪዳን ነው፤ ስለዚህ ከጽዋው በምትጠጡበት ጊዜ ይህን ለመታሰቢያዬ አድርጉት” አለ።

26 ይህን እንጀራ በምትበሉበት ጊዜ፣ ይህንም ጽዋ በምትጠጡበት ጊዜ ሁሉ ጌታ እስከሚመጣ ድረስ ሞቱን ትናገራላችሁ።

27 እንግዲህ ማንም ሳይገባው፣ ይህን እንጀራ ቢበላ ወይም የጌታን ጽዋ ቢጠጣ፣ የጌታ ሥጋና ደም ባለዕዳ ይሆናል።

28 ማንም ሰው ከዚህ እንጀራ ከመብላቱና ከዚህ ጽዋ ከመጠጣቱ በፊት፣ ራሱን ይመርምር፤

29 ምክንያቱም ማንም የጌታን ሥጋ ሳይገባው ቢበላና ቢጠጣ ፍርድ የሚያመጣበትን ይበላል፤ ይጠጣልም።

30 ከእናንተ መካከል ብዙዎች የደከሙትና የታመሙት፣ አንዳንዶችም ያንቀላፉት በዚህ ምክንያት ነው።

31 ራሳችንን ብንመረምር ግን ባልተፈረደብን ነበር።

32 ነገር ግን ጌታ በሚፈርድብን ጊዜ እንገሠጻለን፤ ይኸውም ከዓለም ጋራ ዐብረን እንዳንኰነን ነው።

33 ስለዚህ ወንድሞቼ ሆይ፤ ለመብላት በምትሰበሰቡበት ጊዜ እርስ በርሳችሁ ተጠባበቁ።

34 በምትሰበሰቡበት ጊዜ ለፍርድ እንዳይሆንባችሁ፣ ማንም የራበው ሰው ቢኖር በቤቱ ይብላ። ስለ ቀረው ነገር ደግሞ በምመጣበት ጊዜ እደነግጋለሁ።

መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™

የቅጂ መብት © 2001, 2024 በBiblica, Inc.

በፈቃድ የሚወሰድ። በዓለም ዐቀፍ ባለቤትነቱ።

The Holy Bible, New Amharic Standard Version™

Copyright © 2001, 2024 by Biblica, Inc.

Used with permission. All rights reserved worldwide. 

Biblica, Inc.
跟着我们:



广告