1 ዜና መዋዕል 9 - አዲሱ መደበኛ ትርጒም1 እስራኤል ሁሉ በየትውልድ ሐረጋቸው ተቈጥረው ስማቸው በእስራኤል ነገሥታት መዝገብ ላይ ሰፈረ። የይሁዳ ሕዝብ ከፈጸሙት በደል የተነሣ ተማርከው ወደ ባቢሎን ተወሰዱ። የኢየሩሳሌም ከተማ ሕዝብ 9፥1-17 ተጓ ምብ – ነህ 11፥3-19 2 በመጀመሪያ በየርስታቸውና በየከተሞቻቸው ተመልሰው የሰፈሩት ጥቂት እስራኤላውያን፣ ካህናት፣ ሌዋውያንና በቤተ መቅደሱ ውስጥ የጕልበት ሥራ የሚሠሩ አገልጋዮች ነበሩ። 3 በኢየሩሳሌም ይኖሩ የነበሩ የይሁዳ፣ የብንያም፣ የኤፍሬምና የምናሴ ነገዶች የሚከተሉት ናቸው፤ 4 ከይሁዳ ልጅ፣ ከፋሬስ ዘሮች፣ የባኒ ልጅ፣ የአምሪ ልጅ፣ የዖምሪ ልጅ፣ የዓሚሁድ ልጅ ዑታይ። 5 ከሴሎናውያን፦ የበኵር ልጁ ዓሣያና ወንዶች ልጆቹ። 6 ከዛራውያን፦ ይዑኤል፤ የሕዝቡ ቍጥር ስድስት መቶ ዘጠና ነበረ። ከይሁዳ ነገድ የሰው ቍጥር ስድስት መቶ ዘጠና ነበር። 7 ከብንያማውያን፦ የሐስኑአ ልጅ፣ የሆዳይዋ ልጅ፣ የሜሱላም ልጅ ሰሉ። 8 የይሮሐም ልጅ ብኔያ፤ የሚክሪ ልጅ፣ የኦዚ ልጅ ኤላ፤ የይብንያ ልጅ፣ የራጉኤል ልጅ፣ የሰፋጥያ ልጅ ሜሱላም። 9 በትውልድ ሐረግ መዝገቡ ላይ በተጻፈው መሠረት ከብንያም ነገድ የሕዝቡ ቍጥር ዘጠኝ መቶ ኀምሳ ስድስት ነበረ፤ እነዚህ ሁሉ ወንዶች የቤተ ሰብ አለቆች ነበሩ። 10 ከካህናቱ፦ ዮዳኤ፣ ዮአሪብ፣ ያኪን፤ 11 የእግዚአብሔር ቤት አለቃ የሆነው የአኪጦብ ልጅ፣ የመራዮት ልጅ፣ የሳዶቅ ልጅ፣ የሜሱላም ልጅ፣ የኬልቅያስ ልጅ ዓዛርያስ። 12 የመልክያ ልጅ፣ የፋስኮር ልጅ፣ የይሮሐም ልጅ ዓዳያ፤ የኢሜር ልጅ፣ የምሺላሚት ልጅ፣ የሜሱላም ልጅ፣ የየሕዜራ ልጅ፣ የዓዲኤል ልጅ መዕሣይ። 13 የቤተ ሰብ አለቃ የነበሩት ካህናት ቍጥር አንድ ሺሕ ሰባት መቶ ስድሳ ነበረ፤ እነዚህም በእግዚአብሔር ቤት ለሚከናወነው አገልግሎት ብቁ ሰዎች ነበሩ። 14 ከሌዋውያን ወገን፦ ከሜራሪ ዘሮች የአሳብያ ልጅ፣ የዓዝሪቃም ልጅ፣ የአሱብ ልጅ ሸማያ፣ 15 በቅበቃር፣ ኤሬስ፣ ጋላልና የአሳፍ ልጅ፣ የዝክሪ ልጅ፣ የሚካ ልጅ መታንያ። 16 የኤዶታም ልጅ፣ የጋላል ልጅ፣ የሰሙስ ልጅ አብድያ። እንዲሁም በነጦፋውያን ከተሞች የኖረው የሕልቃና ልጅ፣ የአሳ ልጅ በራክያ። 17 የቤተ መቅደሱ በር ጠባቂዎች፦ ሰሎም፣ ዓቁብ፣ ጤልሞን፣ አሒማንና ወንድሞቻቸው፤ አለቃቸውም ሰሎም ነበረ፤ 18 እርሱም በስተምሥራቅ በሚገኘው በንጉሡ በር እስካሁን ድረስ ተመድቧል። እነዚህም የሌዋውያኑ ሰፈር በር ጠባቂዎች ነበሩ። 19 የቆሬ ልጅ የአብያሳፍ ልጅ፣ የቆሬ ልጅ ሰሎምና ከርሱም ቤተ ሰብ የሆኑት ቆሬያውያን ወደ እግዚአብሔር ማደሪያ የሚያስገባውን በር ይጠብቁ እንደ ነበር ሁሉ፣ እነዚህም ወደ ቤተ መቅደሱ የሚያስገባውን በር ይጠብቁ ነበር። 20 በቀድሞ ጊዜ የበር ጠባቂዎቹ አለቃ የአልዓዛር ልጅ ፊንሐስ ነበረ፤ እግዚአብሔርም ከርሱ ጋራ ነበረ። 21 ወደ መገናኛው ድንኳን የሚያስገባውን በር የሚጠብቀው ደግሞ የሜሱላም ልጅ ዘካርያስ ነበረ። 22 መግቢያ በሮቹን በኀላፊነት እንዲጠብቁ የተመረጡት በአጠቃላይ ሁለት መቶ ዐሥራ ሁለት ነበሩ። እነርሱም በትውልድ ሐረጋቸው መሠረት በሚኖሩባቸው መንደሮች ተቈጥረው ተመዘገቡ፤ በር ጠባቂዎቹን በዚያ ቦታ ላይ የመደቧቸው ዳዊትና ባለራእዩ ሳሙኤል ነበሩ። 23 የማደሪያውን ድንኳን፣ ማለትም የእግዚአብሔርን ቤት የሚጠብቁትም እነርሱና ዘሮቻቸው ነበሩ። 24 በር ጠባቂዎቹም በምሥራቅ፣ በምዕራብ፣ በሰሜንና፣ በደቡብ በሚገኙት በአራቱም ማእዘኖች ላይ ነበሩ። 25 ወንድሞቻቸውም በየመንደሮቻቸው ሆነው በየጊዜው እየወጡ የጥበቃውን ሥራ ሰባት ሰባት ቀን ያግዟቸው ነበር። 26 ሌዋውያን የነበሩት አራቱ የበር ጠባቂ አለቆች ግን በእግዚአብሔር ቤት ውስጥ የሚገኙትን ክፍሎችና ግምጃ ቤቶች በኀላፊነት ይጠብቁ ነበር። 27 የጥበቃውን ሥራ የሚያከናውኑት እነርሱ በመሆናቸው የሚያድሩትም በዚያው በእግዚአብሔር ቤት አካባቢ ነበረ፤ ጧት ጧትም ደጆቹን የሚከፍቱት እነርሱ ነበሩ። 28 ከእነርሱም አንዳንዶቹ ለቤተ መቅደሱ አገልግሎት የሚውሉ ዕቃዎችን በኀላፊነት ይጠብቁ ነበር፤ ዕቃዎቹም በሚገቡበትና በሚወጡበት ጊዜ ሁሉ ይቈጥሩ ነበር። 29 ሌሎቹ ሌዋውያን ደግሞ ዕቃዎቹንና የቤተ መቅደሱን ንዋያተ ቅድሳት፣ ዱቄቱን፣ የወይን ጠጁን፣ የወይራ ዘይቱን፣ ዕጣኑን፣ የሽቱውን ቅመማ ቅመም እንዲጠብቁ ተመድበው ነበር። 30 ከካህናቱም አንዳንዶቹ የሽቱውን ቅመማ ቅመም ይለውሱና ያዘጋጁ ነበር። 31 የቆሬያዊው የሰሎም በኵር ልጅ ሌዋዊው ማቲትያ የቍርባኑን እንጀራ የመጋገር ኀላፊነት ተሰጥቶት ነበር። 32 በየሰንበቱ ለሚዘጋጀው ገጸ ኅብስትም ኀላፊነቱ የተሰጠው ከቀዓታውያን ወንድሞቻቸው መካከል ለአንዳንዶቹ ነበር። 33 የሌዋውያን ቤተ ሰብ አለቆች የነበሩት መዘምራኑ ደግሞ በቤተ መቅደሱ ክፍሎች ውስጥ እንዲኖሩና ከሌላው ሥራ ሁሉ ነጻ እንዲሆኑ ተደርጎ ነበር፤ ምክንያቱም ቀንና ሌሊት የሚሠሩት ሥራ ነበራቸው። 34 እነዚህ ሁሉ የሌዋውያን ቤተ ሰብ አለቆች ሲሆኑ፣ በትውልድ ሐረጋቸው መሠረት ተመዘገቡ፤ የሚኖሩትም በኢየሩሳሌም ነበረ። የሳኦል ትውልድ ሐረግ 9፥34-44 ተጓ ምብ – 1ዜና 8፥28-38 35 የገባዖን አባት ይዒኤል በገባዖን ኖረ፤ የሚስቱም ስም መዓካ ይባላል። 36 የበኵር ልጁም አብዶን ይባል ነበር፤ የእርሱም ተከታዮች ጹር፣ ቂስ፣ ባኣል፣ ኔር፣ ናዳብ፣ 37 ጌዶር፣ አሒዮ፣ ዘካርያስ እና ሚቅሎት ነበሩ። 38 ሚቅሎት ሺሜዓን ወለደ፤ እነርሱም ደግሞ ከሥጋ ዘመዶቻቸው ጋራ በኢየሩሳሌም አቅራቢያ ይኖሩ ነበር። 39 ኔርም ቂስን ወለደ፤ ቂስም ሳኦልን ወለደ፤ ሳኦልም ዮናታንን፣ ሜልኪሳን፣ አሚናዳብን፣ አስበኣልን ወለደ። 40 የዮናታን ወንድ ልጅ መሪበኣል ነው፤ መሪበኣልም ሚካን ወለደ። 41 የሚካ ወንዶች ልጆች፤ ፒቶን፣ ሜሌክ፣ ታሬዓ፣ አካዝ። 42 አካዝ የዕራን ወለደ፤ የዕራም ዓሌሜትን፣ ዓዝሞትን፣ ዚምሪን ወለደ፤ ዚምሪን ሞጻን ወለደ። 43 ሞጻ ቢንዓን ወለደ፤ ልጁ ረፋያ ነበረ፤ ልጁ ኤልዓሣ፣ ልጁ ኤሴል። 44 ኤሴል ስድስት ወንዶች ልጆች ነበሩት፤ ስማቸውም፦ ዓዝሪቃም፣ ቦክሩ፣ እስማኤል፣ ሸዓርያ፣ አብድዩ፣ ሐናን ይባላል፤ እነዚህ የኤሴል ወንዶች ልጆች ናቸው። |
መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™
የቅጂ መብት © 2001, 2024 በBiblica, Inc.
በፈቃድ የሚወሰድ። በዓለም ዐቀፍ ባለቤትነቱ።
The Holy Bible, New Amharic Standard Version™
Copyright © 2001, 2024 by Biblica, Inc.
Used with permission. All rights reserved worldwide.
Biblica, Inc.