1 ዜና መዋዕል 28 - አዲሱ መደበኛ ትርጒምዳዊት ስለ ቤተ መቅደሱ ያወጣው ዕቅድ 1 ዳዊት በኢየሩሳሌም እንዲሰበሰቡ የነገዱን የጦር አለቆች፣ ንጉሡን የሚያገለግሉትን የከፍለ ጦር አዛዦች፣ የሻለቆቹን፣ የመቶ አለቆቹን፣ የንጉሡና የልጆቹ ንብረትና ከብት ሁሉ ኀላፊ የሆኑትን፣ እንዲሁም የቤተ መንግሥቱን ሹማምት፣ ኀያላንና ጀግና ተዋጊዎቹን፣ በአጠቃላይ የእስራኤልን ሹማምት ሁሉ ጠራ። 2 ከዚያም ንጉሥ ዳዊት በእግሩ ቆሞ እንዲህ አላቸው፤ “ወንድሞቼና ወገኖቼ ሆይ፤ ስሙኝ፤ ለእግዚአብሔር ለቃል ኪዳኑ ታቦት ማደሪያና ለአምላካችን እግር ማረፊያ የሚሆን ቤት ለመሥራት ዐስቤ ዕቅድ አውጥቼ ነበር። 3 እግዚአብሔር ግን እንዲህ አለኝ፤ ‘ጦረኛ ሰው ስለ ሆንህና ደምም ስላፈሰስህ፣ አንተ ለስሜ ቤት አትሠራም።’ 4 “ነገር ግን የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር በእስራኤል ላይ ለዘላለም እንድነግሥ ከቤተ ሰቤ ሁሉ እኔን መረጠ፤ መሪ እንዲሆንም ይሁዳን መረጠ፤ ከይሁዳም ቤት የእኔን ቤተ ሰብ መረጠ፤ ከአባቴ ልጆች መካከል ደግሞ በመላው እስራኤል ላይ እንድነግሥ ፈቃዱ ሆነ። 5 እግዚአብሔር ብዙ ልጆች ሰጥቶኛል፤ ከወንዶቹ ልጆቼ ሁሉ በእግዚአብሔር መንግሥት ዙፋን ላይ ተቀምጦ በእስራኤል ሁሉ ላይ እንዲነግሥ ደግሞ ልጄን ሰሎሞንን መርጦታል። 6 እንዲህም አለኝ፤ ‘ቤቴንና አደባባዮቼን የሚሠራልኝ ልጅህ ሰሎሞን ነው፤ ምክንያቱም ልጄ እንዲሆን መርጬዋለሁ፤ እኔም አባት እሆነዋለሁ። 7 አሁን እንደሚያደርገው ሁሉ፣ ትእዛዞቼንና ሕጎቼን ምን ጊዜም ሳያወላውል የሚፈጽም ከሆነ፣ መንግሥቱን ለዘላለም አጸናታለሁ።’ 8 “እንግዲህ አሁንም ይህችን መልካሚቱን ምድር እንድትወርሱና ለልጆቻችሁም የዘላለም ርስት አድርጋችሁ እንድታወርሷቸው፣ የአምላካችሁን የእግዚአብሔርን ትእዛዝ ሁሉ በጥንቃቄ እንድታከብሩ በእስራኤል ሁሉ ፊት፣ በእግዚአብሔር ጉባኤና እግዚአብሔርም እየሰማ አዝዛችኋለሁ። 9 “አንተም ልጄ ሰሎሞን ሆይ፤ እግዚአብሔር ልብን ሁሉ ስለሚመረምርና ሐሳብን ሁሉ ስለሚያውቅ፣ የአባትህን አምላክ ዕወቅ፤ በፍጹም ልብና በበጎ ፈቃድ አገልግለው። ከፈለግኸው ታገኘዋለህ፤ ከተውኸው ግን እርሱም ለዘላለም ይተውሃል። 10 ለመቅደስ የሚሆን ቤት እንድትሠራ እግዚአብሔር የመረጠህ መሆኑን አሁንም ዐስብ፤ በርትተህም ሥራ።” 11 ከዚያም ዳዊት የቤተ መቅደሱን መመላለሻ፣ የሕንጻውን፣ የዕቃ ቤቶቹን፣ የፎቁንና የውስጥ ክፍሎቹን እንዲሁም የማስተስረያውን ቦታ ንድፍ ለልጁ ለሰሎሞን ሰጠው። 12 ደግሞም መንፈስ ቅዱስ በልቡ ያሳደረውን የእግዚአብሔርን ቤተ መቅደስ አደባባይ፣ በዙሪያው ያሉትን ክፍሎች ሁሉ፣ የአምላክን ቤተ መቅደስ ዕቃ ቤቶችና የንዋየ ቅድሳቱን ግምጃ ቤቶች ንድፍ ሁሉ ሰጠው፤ 13 እንዲሁም የካህናቱንና የሌዋውያኑን አመዳደብ፣ በእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ አገልግሎት ሥራና ለአገልግሎቱ ስለሚጠቀምባቸው ዕቃዎች ሁሉ መመሪያ ሰጠው። 14 ለልዩ ልዩ አገልግሎት የሚውሉትን የወርቅ ዕቃዎች ሁሉ መጠን፣ ለልዩ ልዩ አገልግሎት የሚውሉትን የብር ዕቃዎች ሁሉ መጠን አሳወቀው፤ 15 እንደየመቅረዙ አገልግሎት ዐይነት ለወርቁ መቅረዞችና ለቀንዲሎቻቸው የሚሆነውን የእያንዳንዳቸውን የወርቅ መጠን፣ ለብሩ መቅረዞችና ለቀንዲሎቻቸው የሚያስፈልገውን የእያንዳንዳቸውን የብር መጠን፣ 16 ለእያንዳንዱ፣ ገጸ ኅብስት ጠረጴዛ የሚያስፈልገውን የወርቅ መጠን፣ ለእያንዳንዱም የብር ጠረጴዛ የሚያስፈልገውን የብር መጠን፣ 17 ለሹካዎቹ፣ ለጐድጓዳ ሳሕኖቹ፣ ለማንቈርቈርያዎቹ የሚያስፈልገውን ንጹሕ የወርቅ መጠን፣ ለእያንዳንዱ የብር ሳሕን የሚያስፈልገውን የብር መጠን፣ 18 ለዕጣኑ መሠዊያ የሚሆነውን የጠራ ወርቅ መጠን እንዲሁም ክንፎቻቸውን ዘርግተው የእግዚአብሔርን የቃል ኪዳኑን ታቦት የሚሸፍኑትን ከወርቅ የተሠሩትን የኪሩቤል ሠረገሎች ንድፍ ሰጠው። 19 ዳዊትም፣ “ይህ ሁሉ፣ በእኔ ላይ ባለው በእግዚአብሔር እጅ በጽሑፍ ተገለጠልኝ፤ የንድፉንም ዝርዝር እንድረዳ ማስተዋልን ሰጠኝ” አለ። 20 ደግሞም ዳዊት ልጁን ሰሎሞንን እንዲህ አለው፤ “እንግዲህ በርታ፤ ጠንክር፤ ሥራውንም ጀምር። አትፍራ፤ ተስፋም አትቍረጥ፤ እግዚአብሔር አምላኬ ከአንተ ጋራ ነውና፤ እርሱም የእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ አገልግሎት ሥራ እስኪፈጸም ድረስ አይተውህም፤ አይጥልህም። 21 ለእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ሥራ ሁሉ የሚያስፈልጉት ካህናትና ሌዋውያን ምድብም ዝግጁ ነው። በሁሉም የእጅ ሙያ የሠለጠኑ ፈቃደኛ ሰዎች በሥራው ሁሉ ይረዱሃል። ሹማምቱና ሕዝቡ ሁሉ ትእዛዝህን ይፈጽማሉ።” |
መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™
የቅጂ መብት © 2001, 2024 በBiblica, Inc.
በፈቃድ የሚወሰድ። በዓለም ዐቀፍ ባለቤትነቱ።
The Holy Bible, New Amharic Standard Version™
Copyright © 2001, 2024 by Biblica, Inc.
Used with permission. All rights reserved worldwide.
Biblica, Inc.