Biblia Todo Logo
在线圣经

- 广告 -

1 ዜና መዋዕል 27 - አዲሱ መደበኛ ትርጒም


የሰራዊቱ ዋና ዋና ክፍሎች

1 የእስራኤል የቤተ ሰብ አለቆች፣ የሻለቆች፣ የመቶ አለቆች እንዲሁም ዓመቱን ሙሉ በየወሩ የሚመደቡትን ዋና ዋና ክፍሎች በተመለከተ ንጉሡን ያገለገሉ አለቆቻቸው ዝርዝር ይህ ነው። እያንዳንዱ ዋና ክፍል ሃያ አራት ሺሕ ሰው ነበረው።

2 በመጀመሪያው ወር፣ የመጀመሪያው ዋና ክፍል የበላይ የዘብድኤል ልጅ ያሾብዓም ሲሆን፣ በሥሩ የሚታዘዙ ሃያ አራት ሺሕ ሰዎች ነበሩ።

3 እርሱም የፋሬስ ዘር ሲሆን፣ በመጀመሪያው ወር የሰራዊቱ ሹማምት ሁሉ የበላይ ነበር።

4 በሁለተኛው ወር፣ የክፍለ ጦሩ የበላይ አዛዥ አሆሃዊው ዱዲ ሲሆን፣ የዚሁ ክፍል መሪ ደግሞ ሚቅሎት ነው፤ በሥሩም ሃያ አራት ሺሕ ሰው ነበረ።

5 በሦስተኛውም ወር፣ የሦስተኛው ክፍለ ጦር የበላይ አዛዥ የካህኑ የዮዳሄ ልጅ በናያስ ነበረ፤ ዋናው እርሱ ሲሆን፣ በሥሩ ሃያ አራት ሺሕ ሰው ነበረ።

6 ይህም በናያስ ከሠላሳዎቹ ይልቅ ኀያል ሲሆን፣ የሠላሳዎቹ የበላይ ነበረ፤ ልጁ ዓሚዛ ባድም የክፍሉ ሰራዊት አዛዥ ነበረ።

7 በአራተኛው ወር፣ አራተኛው የበላይ አዛዥ የኢዮአብ ወንድም አሣሄል ሲሆን፣ በእግሩ የተተካውም ልጁ ዝባድያ ነው፤ በሥሩም ሃያ አራት ሺሕ ሰው ነበረ።

8 በዐምስተኛው ወር፣ ዐምስተኛው የበላይ አዛዥ ይዝራዊው ሸምሁት ሲሆን፣ በሥሩም ሃያ አራት ሺሕ ሰው ነበረ።

9 በስድስተኛው ወር፣ ስድስተኛው የበላይ አዛዥ የቴቁሐዊው የዒስካ ልጅ ዒራስ ሲሆን፣ በሥሩም ሃያ አራት ሺሕ ሰው ነበረ።

10 በሰባተኛው ወር፣ ሰባተኛው የበላይ አዛዥ የኤፍሬም ወገን የሆነው ፍሎናዊው ሴሌስ ሲሆን፣ በሥሩም ሃያ አራት ሺሕ ሰው ነበረ።

11 በስምንተኛው ወር፣ ስምንተኛው የበላይ አዛዥ ከካዛራውያን ወገን የሆነው ኩሳታዊው ሴቦካይ ሲሆን፣ በሥሩም ሃያ አራት ሺሕ ሰው ነበረ።

12 በዘጠነኛው ወር፣ ዘጠነኛው የበላይ አዛዥ ከብንያም ወገን የሆነው ዓናቶታዊው አቢዔዜር ሲሆን፣ በሥሩም ሃያ አራት ሺሕ ሰው ነበረ።

13 በዐሥረኛው ወር፣ ዐሥረኛው የበላይ አዛዥ ከዛራውያን ወገን የሆነው ነጦፋዊው ማህራይ ሲሆን፣ በሥሩም ሃያ አራት ሺሕ ሰው ነበረ።

14 በዐሥራ አንደኛው ወር፣ ዐሥራ አንደኛው የበላይ አዛዥ ከኤፍሬም ወገን የሆነው ጲርዓቶናዊው በናያስ ሲሆን፣ በሥሩም ሃያ አራት ሺሕ ሰው ነበረ።

15 በዐሥራ ሁለተኛው ወር፣ ዐሥራ ሁለተኛው የበላይ አዛዥ ከጎቶንያል ቤተ ሰብ የሆነው ነጦፋዊው ሔልዳይ ነበረ።


የየነገዱ የጦር ሹማምት

16 የየነገዱ የእስራኤል የጦር ሹማምት፤ በሮቤል ነገድ ላይ የተሾመው፣ የዝክሪ ልጅ አልዓዛር፤ በስምዖን ነገድ ላይ የተሾመው፣ የመዓካ ልጅ ሰፋጥያስ።

17 በሌዊ ነገድ ላይ የተሾመው፣ የቀሙኤል ልጅ ሐሸብያ፤ በአሮን ነገድ ላይ የተሾመው፣ ሳዶቅ።

18 በይሁዳ ነገድ ላይ የተሾመው፣ የዳዊት ወንድም ኤሊሁ፤ በይሳኮር ነገድ ላይ የተሾመው፣ የሚካኤል ልጅ ዖምሪ።

19 በዛብሎን ነገድ ላይ የተሾመው፣ የአብድዩ ልጅ ይሽማያ፤ በንፍታሌም ነገድ ላይ የተሾመው፣ የዓዝሪኤል ልጅ ለኢያሪሙት።

20 በኤፍሬም ነገድ ላይ የተሾመው፣ የዓዛዝያ ልጅ ሆሴዕ፤ በምናሴ ነገድ እኩሌታ ላይ የተሾመው፣ የፈዳያ ልጅ ኢዩኤል።

21 በገለዓድ ባለው የምናሴ ነገድ እኩሌታ ላይ የተሾመው፣ የዘካርያስ ልጅ አዶ፤ በብንያም ነገድ ላይ የተሾመው፣ የአበኔር ልጅ የዕሢኤል።

22 በዳን ነገድ ላይ የተሾመው፣ የይሮሐም ልጅ ዓዛርኤል። እንግዲህ የእስራኤል ነገድ አለቆች እነዚህ ነበሩ።

23 እግዚአብሔር እስራኤልን እንደ ሰማይ ከዋክብት እንደሚያበዛቸው ተስፋ ሰጥቶ ስለ ነበር፣ ዳዊት ዕድሜያቸው ሃያና ከዚያ በታች የሆነውን አልቈጠረም ነበር።

24 የጽሩያ ልጅ ኢዮአብ መቍጠር ጀመረ፤ ሆኖም አልፈጸመውም፤ መቈጠራቸው በእስራኤል ላይ ቍጣ ስላመጣ፣ የተቈጠረውም በንጉሡ ዳዊት መዝገብ አልገባም።


ንጉሡ የሾማቸው የበላይ ተቈጣጣሪዎች

25 የዓዲኤል ልጅ ዓዝሞት የቤተ መንግሥቱ ዕቃ ቤት ኀላፊ ነበረ፤ የዖዚያ ልጅ ዮናታን በየአውራጃው በየከተማው፣ በየመንደሩና በየቃፊር መጠበቂያው ላሉት ዕቃ ቤቶች ኀላፊ ነበረ።

26 የክሉብ ልጅ ዔዝሪ ምድሪቱን ለሚያርሱት ገበሬዎች ኀላፊ ነበረ።

27 ራማታዊው ሰሜኢ የወይን ተክል ቦታዎች ኀላፊ ነበረ፤ ሸፋማዊው ዘብዲ የወይን ጠጅ ዕቃ ቤት ኀላፊ ነበረ።

28 ጌድራዊው በአልሐናን በምዕራባዊው ኰረብቶች ግርጌ ለሚገኙት የወይንና የወርካ ዛፎች ጥበቃ ኀላፊ ነበረ፤ በዘይቱም ቤቶች ላይ ኢዮአስ ሹም ነበረ።

29 ሳሮናዊው ሰጥራይ በሳሮን ለሚሰማሩት የከብት መንጋዎች ኀላፊ ነበረ፤ የዓድላይ ልጅ ሻፋጥ በሸለቆው ውስጥ ላሉት የከብት መንጋዎች ኀላፊ ነበረ።

30 እስማኤላዊው ኡቢያስ የግመሎች ኀላፊ ነበረ። ሜሮኖታዊው ዬሕድያ የአህዮች ኀላፊ ነበረ።

31 አጋራዊው ያዚዝ የበግና የፍየል መንጋዎች ኀላፊ ነበረ። እነዚህ ሁሉ የንጉሥ ዳዊት ንብረት ኀላፊዎች ነበሩ።

32 አስተዋይ የሆነው የዳዊት አጎት ዮናታን አማካሪና ጸሓፊ ነበረ፤ የሐክሞኒም ልጅ ይሒኤል ደግሞ የንጉሡ ልጆች ሞግዚት ነበረ።

33 አኪጦፌል የንጉሡ አማካሪ ሲሆን፣ አርካዊው ኩሲ ደግሞ የንጉሡ ወዳጅ ነበረ።

34 የበናያስ ልጅ ዮዳሄና አብያታር በአኪጦፌል እግር ተተኩ። ኢዮአብም የንጉሡ የክብር ዘብ አዛዥ ሆነ።

መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™

የቅጂ መብት © 2001, 2024 በBiblica, Inc.

በፈቃድ የሚወሰድ። በዓለም ዐቀፍ ባለቤትነቱ።

The Holy Bible, New Amharic Standard Version™

Copyright © 2001, 2024 by Biblica, Inc.

Used with permission. All rights reserved worldwide. 

Biblica, Inc.
跟着我们:



广告