1 ዜና መዋዕል 24 - አዲሱ መደበኛ ትርጒምየካህናት አመዳደብ 1 የአሮን ልጆች አመዳደብ እንደሚከተለው ነበረ፤ የአሮን ልጆች ናዳብ፣ አብዩድ፣ አልዓዛር፣ ኢታምር ነበሩ። 2 ናዳብና አብዩድ ግን ዘር ሳይተኩ ከአባታቸው በፊት ሞቱ፤ ስለዚህ አልዓዛርና ኢታምር ካህናት ሆነው ያገለግሉ ነበር። 3 ዳዊትም የአልዓዛር ዘር የሆነው ሳዶቅና የኢታምር ዘር የሆነው አቢሜሌክ እየረዱት እንደየአገልግሎታቸው ሥርዐት እየለየ መደባቸው። 4 ከኢታምር ይልቅ በአልዓዛር ዘሮች መካከል ብዙ መሪዎች ተገኙ፤ አከፋፈላቸውም እንደሚከተለው ነበር፤ ከአልዓዛር ዘሮች ዐሥራ ስድስት የቤተ ሰብ አለቆች፤ ከኢታምርም ዘሮች ስምንት የቤተ ሰብ አለቆች። 5 ከአልዓዛርና ከኢታምር ዘሮች መካከል የመቅደሱ ሹማምትና የእግዚአብሔር ሹማምት ስለ ነበሩ፣ ያለ አድልዎ በዕጣ ለዩአቸው። 6 የሌዋዊው የናትናኤል ልጅ ጸሓፊው ሸማያ በንጉሡና በሹማምቱ፣ በካህኑ በሳዶቅ፣ በአብያታር ልጅ በአቢሜሌክ እንዲሁም በካህናቱና በሌዋውያኑ ቤተ ሰብ አለቆች ፊት ስማቸውን ጻፈ፤ የጻፈውም አንዱን ቤተ ሰብ ከአልዓዛር ሌላውን ደግሞ ከኢታምር በመውሰድ ነው። 7 የመጀመሪያው ዕጣ ለዮአሪብ፣ ሁለተኛውም ዕጣ ለዮዳሄ ወጣ፤ 8 ሦስተኛው ለካሪም፣ አራተኛው ለሥዖሪም፣ 9 ዐምስተኛው ለመልክያ፣ ስድስተኛው ለሚያሚን፣ 10 ሰባተኛው ለአቆስ፣ ስምንተኛው ለአብያ፣ 11 ዘጠነኛው ለኢያሱ፣ ዐሥረኛው ለሴኬንያ፣ 12 ዐሥራ አንደኛው ለኤሊያሴብ፣ ዐሥራ ሁለተኛው ለያቂም፣ 13 ዐሥራ ሦስተኛው ለኦፖ፣ ዐሥራ አራተኛው ለየሼብአብ፣ 14 ዐሥራ ዐምስተኛው ለቢልጋ፣ ዐሥራ ስድስተኛው ለኢሜር፣ 15 ዐሥራ ሰባተኛው ለኤዚር፣ ዐሥራ ስምንተኛው ለሃፊጼጽ፣ 16 ዐሥራ ዘጠነኛው ለፈታያ፣ ሃያኛው ለኤዜቄል፣ 17 ሃያ አንደኛው ለያኪን፣ ሃያ ሁለተኛው ለጋሙል፣ 18 ሃያ ሦስተኛው ለድላያ፣ ሃያ አራተኛ ለመዓዝያ ወጣ። 19 የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር ባዘዘውና ከቀድሞ አባታቸው ከአሮን በተሰጣቸው መመሪያ መሠረት ወደ እግዚአብሔር ቤተ መቅደስ በሚገቡበት ጊዜ፣ የተወሰነላቸው ሥርዐት ይህ ነበር። የተቀሩት ሌዋውያን 20 ከቀሩት የሌዊ ዘሮች ደግሞ፦ ከእንበረም ወንዶች ልጆች፣ ሱባኤል፤ ከሱባኤል ወንዶች ልጆች፣ ዬሕድያ። 21 ከረዓብያ ወንዶች ልጆች፤ አለቃው ይሺያ። 22 ከይስዓራውያን ወገን፣ ሰሎሚት፤ ከሰሎሚት ወንዶች ልጆች፣ ያሐት። 23 የኬብሮን ወንዶች ልጆች፣ የመጀመሪያው ይሪያ፣ ሁለተኛው አማርያ፣ ሦስተኛው የሕዚኤል፣ አራተኛው ይቅምዓም። 24 የዑዝኤል ልጅ፣ ሚካ ከሚካ ወንዶች ልጆች ሻሚር። 25 የሚካ ወንድም ይሺያ፤ ከይሺያ ወንዶች ልጆች ዘካርያስ። 26 የሜራሪ ወንዶች ልጆች፤ ሞሖሊ፣ ሙሲ። የያዝያ ወንድ ልጅ በኖ። 27 የሜራሪ ወንዶች ልጆች፤ ከያዝያ በኖ፣ ሾሃም፣ ዛኩር፣ ዔብሪ። 28 ከሞሖሊ፤ አልዓዛር፤ ይህ ሰው ወንዶች ልጆች አልነበሩትም። 29 ከቂስ፤ የቂስ ወንድ ልጅ፤ ይረሕምኤል። 30 የሙሲ ወንዶች ልጆች፤ ሞሖሊ፣ ዔደር፣ ለኢያሪሙት። እነዚህ እንግዲህ እንደየቤተ ሰባቸው የተቈጠሩ ሌዋውያን ነበሩ። 31 ወንድሞቻቸው የአሮን ዘሮች እንዳደረጉት ሁሉ፣ እነዚህም በንጉሥ ዳዊት፣ በሳዶቅ፣ በአቢሜሌክ እንዲሁም የካህናቱና የሌዋውያኑ ቤተ ሰብ አለቆች ባሉበት ዕጣ ተጣጣሉ፤ የበኵሩም ቤተ ሰቦች እንደ ትንሹ ወንድም ቤተ ሰብ እኩል ዕጣ ተጣለላቸው። |
መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™
የቅጂ መብት © 2001, 2024 በBiblica, Inc.
በፈቃድ የሚወሰድ። በዓለም ዐቀፍ ባለቤትነቱ።
The Holy Bible, New Amharic Standard Version™
Copyright © 2001, 2024 by Biblica, Inc.
Used with permission. All rights reserved worldwide.
Biblica, Inc.