1 ዜና መዋዕል 23 - አዲሱ መደበኛ ትርጒምሌዋውያን 1 ዳዊት በሸመገለና ዕድሜው በገፋ ጊዜ፣ ልጁን ሰሎሞንን በእስራኤል ላይ አነገሠው። 2 እንዲሁም መላውን የእስራኤልን መሪዎች፣ ካህናቱንና ሌዋውያኑን ሁሉ በአንድነት ሰበሰበ። 3 ዕድሜያቸው ሠላሳና ከዚያ በላይ የሆኑ ወንዶች ሁሉ ተቈጠሩ፤ ቍጥራቸውም በጠቅላላው ሠላሳ ስምንት ሺሕ ነበረ። 4 ዳዊትም እንዲህ አለ፤ “ከእነዚህ መካከል ሃያ አራቱ ሺሕ የእግዚአብሔርን ቤተ መቅደስ ሥራ ይቈጣጠሩ፤ ስድስቱ ሺሕ ደግሞ ሹሞችና ዳኞች ይሁኑ፤ 5 አራቱ ሺሕ የቅጥሩ በር ጠባቂዎች ይሁኑ፤ አራቱ ሺሕ ደግሞ ለዚሁ ብዬ ባዘጋጀሁት የዜማ መሣሪያ እግዚአብሔርን ያመስግኑ”። 6 ዳዊትም ሌዋውያኑን በሌዊ ልጆች በጌርሶን፣ በቀዓትና በሜራሪ በየጐሣቸው መደባቸው። ጌድሶናውያን 7 ከጌርሶናውያን ወገን፤ ለአዳን፣ ሰሜኢ። 8 የለአዳን ወንዶች ልጆች፤ የመጀመሪያው ይሒኤል፣ ዜቶም፣ ኢዩኤል፤ በአጠቃላይ ሦስት ናቸው። 9 የሰሜኢ ወንዶች ልጆች፤ ሰሎሚት፣ ሐዝኤል፣ ሐራን፤ በአጠቃላይ ሦስት ናቸው። እነዚህ የለአዳን ቤተ ሰብ አለቆች ናቸው። 10 የሰሜኢ ወንዶች ልጆች፤ ኢኢት፣ ዚዛ፣ የዑስ፣ በሪዓ፤ እነዚህ አራቱ የሰሜኢ ልጆች ናቸው። 11 የመጀመሪያው ኢኢት፣ ሁለተኛው ደግሞ ዚዛ ነበረ፤ የዑስና በሪዓ ግን ብዙ ወንዶች ልጆች አልነበሯቸውም፤ ስለዚህ የተቈጠሩት በሥራ መደብ እንደ አንድ ቤተ ሰብ ሆነው ነው። ቀዓታውያን 12 የቀዓት ወንዶች ልጆች፤ እንበረም፣ ይስዓር፣ ኬብሮን፣ ዑዝኤል፤ በአጠቃላይ አራት ናቸው። 13 የእንበረም ወንዶች ልጆች፤ አሮን፣ ሙሴ። አሮን የተቀደሰ እንዲሆን ተለየ፤ እርሱና ዘሮቹ ለዘላለም ቅዱስ የሆኑትን ነገሮች እንዲቀድሱ፣ በእግዚአብሔር ፊት መሥዋዕት እንዲያቀርቡ፣ በፊቱ እንዲያገለግሉና በስሙም ለዘላለም እንዲባርኩ ተለዩ። 14 የእግዚአብሔር ሰው የሙሴ ወንዶች ልጆችም እንደ ሌዊ ነገድ ሆነው ተቈጠሩ። 15 የሙሴ ወንዶች ልጆች፤ ጌርሳም፣ አልዓዛር። 16 የጌርሳም ዘሮች፤ ሱባኤል። 17 የአልዓዛር ዘሮች፤ የመጀመሪያው ረዓብያ ነበረ። አልዓዛር ሌሎች ወንዶች ልጆች አልነበሩትም፤ የረዓብያ ወንዶች ልጆች ግን እጅግ ብዙ ነበሩ። 18 የይስዓር ወንዶች ልጆች፤ የመጀመሪያው ሰሎሚት ነበረ። 19 የኬብሮን ወንዶች ልጆች፤ የመጀመሪያው ይሪያ፣ ሁለተኛው አማርያ፣ ሦስተኛው የሕዚኤል፣ አራተኛው ይቅምዓም ነበሩ። 20 የዑዝኤል ወንዶች ልጆች፤ የመጀመሪያው ሚካ፣ ሁለተኛው ይሺያ ነበሩ። ሜራሪያውያን 21 የሜራሪ ወንዶች ልጆች፤ ሞሖሊ፣ ሙሲ። የሞሖሊ ወንዶች ልጆች፤ አልዓዛርና ቂስ ነበሩ። 22 አልዓዛር ወንድ ልጅ ሳይወልድ ሞተ፤ ልጆቹ ሴቶች ብቻ ነበሩ፤ እነርሱንም የአጎታቸው የቂስ ልጆች አገቧቸው። 23 የሙሲ ወንዶች ልጆች፤ ሞሖሊ፣ ዔደር፣ ለኢያሪሙት በአጠቃላይ ሦስት ናቸው። 24 እንግዲህ እነዚህ የቤተ ሰቡ አለቆች ሆነው እያንዳንዳቸው በየስማቸው ተመዝግበው የተቈጠሩት የሌዊ ዘሮች ናቸው፤ ዕድሜያቸውም ሃያና ከዚያ በላይ የሆናቸው በእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ውስጥ የሚያገለግሉ ነበሩ። 25 ዳዊት እንዲህ ብሎ ነበርና፣ “የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር ለሕዝቡ ዕረፍት ሰጥቷል፤ በኢየሩሳሌምም ለዘላለም ለመኖር መጥቷል፤ 26 ሌዋውያን ከእንግዲህ ወዲህ ድንኳኑን ወይም የመገልገያ ዕቃውን ሁሉ መሸከም የለባቸውም።” 27 ዳዊት በሰጠው የመጨረሻ መመሪያ መሠረት የተቈጠሩት ሌዋውያን ዕድሜያቸው ሃያና ከዚያ በላይ ነበረ። 28 የሌዋውያኑ ተግባር በእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ አገልግሎት የአሮንን ዘሮች መርዳት፣ የቤተ መቅደሱን ቅጥር ግቢና ክፍሎች መከባከብ፣ የተቀደሱ ዕቃዎችን ሁሉ ማንጻትና በእግዚአብሔር ቤት ያሉትን ሌሎች ተግባሮች ማከናወን ነበር። 29 እንዲሁም መባ ሆኖ የሚቀርበውን ገጸ ኅብስት፣ የእህል ቍርባኑን ዱቄት፣ ቂጣ የሚጋግሩ፣ የሚያቦኩና የሚሰፈረውንም ሆነ የሚለካውን ሁሉ በኀላፊነት የሚቈጣጠሩ እነርሱ ነበሩ። 30 በየዕለቱም እግዚአብሔርን ለማመስገንና ለመወደስ ጧት ጧት ይቆሙ ነበር፤ ይህንም ማታ ማታ 31 እንዲሁም በየሰንበቱ፣ በወር መባቻ በዓልና በተደነገጉት በዓላት ሁሉ፣ የሚቃጠል መሥዋዕት ለእግዚአብሔር በሚቀርብበት ጊዜ ይፈጽሙ ነበር፤ በተወሰነላቸው ቍጥርና በተሰጠውም መመሪያ መሠረት፣ ዘወትር በእግዚአብሔር ፊት ያገለግሉ ነበር። 32 ስለዚህ ሌዋውያኑ ለመገናኛው ድንኳንና ለመቅደሱ እንዲሁም በወንድሞቻቸው በአሮን ዘሮች ሥር ሆነው ለእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ያለባቸውን ኀላፊነት ያከናውኑ ነበር። |
መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™
የቅጂ መብት © 2001, 2024 በBiblica, Inc.
በፈቃድ የሚወሰድ። በዓለም ዐቀፍ ባለቤትነቱ።
The Holy Bible, New Amharic Standard Version™
Copyright © 2001, 2024 by Biblica, Inc.
Used with permission. All rights reserved worldwide.
Biblica, Inc.