Biblia Todo Logo
在线圣经

- 广告 -

1 ዜና መዋዕል 22 - አዲሱ መደበኛ ትርጒም

1 ከዚያም ዳዊት፣ “ከእንግዲህ የእግዚአብሔር አምላክ ቤት በዚህ ይሆናል፤ እንዲሁም ስለ እስራኤል የሚቃጠል መሥዋዕት የሚቀርብበት መሠዊያ በዚሁ ይቆማል” አለ።


ቤተ መቅደሱን ለመሥራት የተደረገ ዝግጅት

2 ስለዚህ ዳዊት በእስራኤል የሚኖሩ መጻተኞች እንዲሰበሰቡ አዘዘ፤ ከመካከላቸውም የእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ የሚሠራበትን ጥርብ ድንጋይ እንዲያዘጋጁ ጠራቢዎችን መደበ።

3 ለቅጥር በሮቹ ምስማርና ማጠፊያ የሚሆን ብዙ ብረትና ከብዛቱ የተነሣ ሊመዘን የማይቻል ናስ አዘጋጀ።

4 እንዲሁም ሲዶናውያንና ጢሮሳውያን በብዛት ለዳዊት አምጥተውለት ስለ ነበር፣ ስፍር ቍጥር የሌለው የዝግባ ዕንጨት አሰናዳ።

5 ዳዊትም፣ “ልጄ ሰሎሞን ወጣት ነው፤ ልምዱም የለውም፤ ለእግዚአብሔር የሚሠራው ቤተ መቅደስ ደግሞ እጅግ የሚያምር፣ በአሕዛብም ሁሉ ዘንድ ዝናው የተሰማና እጅግ የተዋበ መሆን አለበት፤ ስለዚህ ሁሉንም እኔ አዘጋጃለሁ” አለ። እንዳለውም ዳዊት ከመሞቱ በፊት በብዛት አዘጋጀ።

6 ከዚያም ልጁን ሰሎሞንን ጠርቶ ለእስራኤል አምላክ ለእግዚአብሔር ቤት እንዲሠራ አዘዘው።

7 ዳዊትም ሰሎሞንን እንዲህ አለው፤ “ልጄ ሆይ፤ ለአምላኬ ለእግዚአብሔር ስም ቤት ለመሥራት በልቤ ዐስብ ነበር፤

8 ነገር ግን ከእግዚአብሔር እንዲህ የሚል ቃል መጣልኝ፤ ‘አንተ ብዙ ደም አፍስሰሃል፤ ብዙ ጦርነትም አድርገሃል፤ በፊቴ በምድር ላይ ብዙ ደም ያፈሰስህ ስለ ሆነ፣ አንተ ለስሜ ቤት አትሠራልኝም፤

9 ነገር ግን የሰላምና የዕረፍት ሰው የሆነ ልጅ ትወልዳለህ፤ በየአቅጣጫው ካሉ ጠላቶቹ አሳርፈዋለሁ፤ ስሙም ሰሎሞን ይባላል። በዘመኑም ለእስራኤል ሰላምንና ጸጥታን እሰጣለሁ።

10 ለስሜ ቤት የሚሠራልኝ እርሱ ነው። እርሱ ልጅ ይሆነኛል፤ እኔም አባት እሆነዋለሁ። ዙፋኑንም በእስራኤል ላይ ለዘላለም አጸናለሁ።’

11 “አሁንም ልጄ ሆይ፤ እግዚአብሔር ከአንተ ጋራ ይሁን፤ እንድትፈጽመው በተናገረውም መሠረት፣ ተሳክቶልህ የአምላክህን የእግዚአብሔርን ቤት ለመሥራት ያብቃህ።

12 በእስራኤል ላይ አለቃ ባደረገህ ጊዜ፣ የአምላክህን የእግዚአብሔርን ትእዛዝ ትፈጽም ዘንድ እግዚአብሔር ጥበብንና ማስተዋልን ይስጥህ።

13 እግዚአብሔር በሙሴ አማካይነት ለእስራኤል የሰጠውን ሕጉንና ሥርዐቱን ተጠንቅቀህ ብትጠብቅ ይሳካልሃል፤ አይዞህ ጠንክር፤ በርታ፤ ተስፋም አትቍረጥ።

14 “ለእግዚአብሔር ቤት እንዲሆንም አንድ ሺሕ መክሊት ወርቅ፣ አንድ ሚሊዮን መክሊት ብር፣ ከብዛቱ የተነሣ ሊመዘን የማይቻል ናስና ብረት ለማዘጋጀት በተቻለኝ ሁሉ ጥሬአለሁ፤ በተረፈ አንተ ጨምርበት።

15 ድንጋይ ጠራቢዎች፣ ግንበኞች፣ የእጅ ጥበብ ባለሙያዎች የሆኑ ብዙ ሠራተኞች፣ እንዲሁም በልዩ ልዩ ሙያ የተጠበቡ ሰዎች አሉህ፤

16 እነዚህም ቍጥራቸው እጅግ የበዛ የወርቅ፣ የብር፣ የናስና የብረት ሠራተኞች ናቸው። በል ሥራህን ጀምር፤ እግዚአብሔርም ከአንተ ጋራ ይሁን።”

17 ከዚያም ዳዊት የእስራኤል መሪዎች ሁሉ ልጁን ሰሎሞንን እንዲረዱት አዘዘ፤

18 እንዲህም አለ፤ “እግዚአብሔር አምላካችሁ እስካሁን ከእናንተ ጋራ አይደለምን? በየአቅጣጫውስ ዕረፍትን ሰጥቷችሁ የለምን? የምድሪቱን ነዋሪዎች በእጄ አሳልፎ ሰጥቶኛል፤ ምድሪቱም ለእግዚአብሔርና ለሕዝቡ ተገዝታለች።

19 አሁንም እግዚአብሔር አምላካችሁን ለመፈለግ ልባችሁንና ነፍሳችሁን ሰብስቡ። የእግዚአብሔርን የኪዳኑን ታቦትና ንዋያተ ቅድሳቱን ለእግዚአብሔር ስም ወደሚሠራው ቤተ መቅደስ እንድታመጡ የእግዚአብሔር አምላክን መቅደስ ሥሩ።”

መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™

የቅጂ መብት © 2001, 2024 በBiblica, Inc.

በፈቃድ የሚወሰድ። በዓለም ዐቀፍ ባለቤትነቱ።

The Holy Bible, New Amharic Standard Version™

Copyright © 2001, 2024 by Biblica, Inc.

Used with permission. All rights reserved worldwide. 

Biblica, Inc.
跟着我们:



广告