1 ዜና መዋዕል 21 - አዲሱ መደበኛ ትርጒምዳዊት ተዋጊ ሰራዊቱን ቈጠረ 21፥1-26 ተጓ ምብ – 2ሳሙ 24፥1-25 1 ሰይጣን በእስራኤል ላይ ተነሥቶ ዳዊት የእስራኤልን ሕዝብ እንዲቈጥር አነሣሣው። 2 ዳዊትም ኢዮአብንና የሰራዊቱን አዛዦች፣ “ሄዳችሁ ከቤርሳቤህ እስከ ዳን ያሉትን እስራኤላውያን ቍጠሩ፤ ከዚያም ምን ያህል እንደ ሆኑ ዐውቅ ዘንድ ንገሩኝ” አላቸው። 3 ኢዮአብ ግን፣ “እግዚአብሔር የእስራኤልን ሰራዊት አሁን ካለው በላይ በመቶ ዕጥፍ ያብዛው፤ ጌታዬ ንጉሥ ሆይ፤ ሁሉስ ቢሆኑ የጌታዬ ተገዦች አይደሉምን? ታዲያ ንጉሡ ጌታዬ ይህን ማድረግ ለምን አስፈለገው? ለምንስ በእስራኤል ላይ በደል ያመጣል?” አለ። 4 ይሁን እንጂ የንጉሡ ቃል ኢዮአብን አሸነፈው፤ ስለዚህ ኢዮአብ ወጣ፤ በመላው እስራኤል ከተዘዋወረ በኋላ፣ ወደ ኢየሩሳሌም ተመለሰ። 5 ኢዮአብም የተዋጊዎቹን ሰዎች ቍጥር ለዳዊት አቀረበ፤ እነዚህም በመላው እስራኤል አንድ ሚሊዮን አንድ መቶ ሺሕ፣ በይሁዳ ደግሞ አራት መቶ ሰባ ሺሕ ሲሆኑ፣ ሁሉም ሰይፍ መምዘዝ የሚችሉ ነበሩ። 6 ኢዮአብ ግን የንጉሡ ትእዛዝ አስጸያፊ ነበረና፣ የሌዊንና የብንያምን ነገድ ጨምሮ አልቈጠረም። 7 ይህ ትእዛዝ በእግዚአብሔር ዘንድ የተጠላ ነበር፤ ስለዚህ እግዚአብሔር እስራኤልን ቀጣ። 8 ከዚያም ዳዊት እግዚአብሔርን፣ “ባደረግሁት ነገር ታላቅ ኀጢአት ሠርቻለሁ፤ የፈጸምሁትም ታላቅ የስንፍና ሥራ ስለ ሆነ፣ የባሪያህን በደል እንድታስወግድ እለምንሃለሁ” አለ። 9 እግዚአብሔርም የዳዊት ባለራእይ የሆነውን ጋድን እንዲህ አለው፤ 10 “ሂድና ዳዊትን እንዲህ ብለው ንገረው፤ ‘እግዚአብሔር የሚለው ይህን ነው፤ እነሆ፣ ሦስት ምርጫ ሰጥቼሃለሁ፤ በአንተ ላይ አደርግብህ ዘንድ አንዱን ምረጥ።’ ” 11 ስለዚህ ጋድ ወደ ዳዊት ሄዶ እንዲህ አለው፤ “እግዚአብሔር የሚለው ይህን ነው፤ ‘በል እንግዲህ አንዱን ምረጥ፤ 12 የሦስት ዓመት ራብ ወይስ የጠላቶችህ ሰይፍ ለሦስት ወር አይሎብህ መጥፋት ወይስ ሦስት ቀን የእግዚአብሔር ሰይፍ መቅሠፍት በምድሪቱ ላይ ወርዶ የእግዚአብሔር መልአክ እስራኤልን ሁሉ ያጥፋ?’ ለላከኝ ምን እንደምመልስ ወስን።” 13 ዳዊትም ጋድን፣ “እጅግ ተጨንቄአለሁ፤ ምሕረቱ ታላቅ ስለ ሆነ፣ በእግዚአብሔር እጅ መውደቅ ይሻለኛል፤ በሰው እጅስ አልውደቅ” አለ። 14 ስለዚህ እግዚአብሔር በእስራኤል ላይ መቅሠፍት ላከ፤ ከእስራኤልም ሰባ ሺሕ ሰው ዐለቀ። 15 እንዲሁም እግዚአብሔር ኢየሩሳሌምን እንዲያጠፋ መልአክ ላከ፤ መልአኩ ሊያጠፋትም ሲል እግዚአብሔር አይቶ ስለሚደርሰው ጥፋት ዐዘነ፤ ሕዝቡን የሚያጠፋውንም መልአክ፣ “በቃ! እጅህን መልስ” አለው። የእግዚአብሔርም መልአክ በኢያቡሳዊው በኦርና ዐውድማ አጠገብ ቆሞ ነበር። 16 ዳዊት ቀና ብሎ ሲመለከት፣ የእግዚአብሔር መልአክ በሰማይና በምድር መካከል ቆሞ አየ፤ መልአኩም በኢየሩሳሌም ላይ የተመዘዘ ሰይፍ በእጁ ይዞ ነበር፤ ከዚያም ዳዊትና ሽማግሌዎቹ ማቅ እንደ ለበሱ በግምባራቸው ተደፉ። 17 ዳዊት እግዚአብሔርን፣ “ተዋጊዎቹ እንዲቈጠሩ ያዘዝሁ እኔ አይደለሁምን? ኀጢአት የሠራሁትም ሆነ የተሳሳትሁም እኔ ነኝ፤ እነዚህ እኮ በጎች ናቸው፤ ታዲያ እነርሱ ምን አደረጉ? እግዚአብሔር አምላኬ ሆይ፤ እጅህ በእኔና በአባቴ ቤት ላይ ትሁን እንጂ፣ መቅሠፍቱ በሕዝብህ ላይ አይውረድ” አለ። 18 ከዚያም የእግዚአብሔር መልአክ ዳዊት ወጥቶ በኢያቡሳዊው በኦርና ዐውድማ ላይ ለእግዚአብሔር መሠዊያ ይሠራ ዘንድ እንዲነግረው ጋድን አዘዘው። 19 ስለዚህ ዳዊትም ጋድ በእግዚአብሔር ስም በነገረው ቃል ታዝዞ ለመፈጸም ወጣ። 20 ኦርና ስንዴ በመውቃት ላይ ሳለ ዘወር ሲል መልአኩን አየ፤ ዐብረውት የነበሩት አራት ወንዶች ልጆቹም ተሸሸጉ። 21 ዳዊት ወደ እርሱ እየቀረበ መጣ፤ ኦርናም ቀና ብሎ ሲመለከት፣ ዳዊትን አየው፤ ከዐውድማውም ወጥቶ መሬት ላይ ለጥ ብሎ በመደፋት ለዳዊት እጅ ነሣ። 22 ዳዊትም ኦርናን፣ “በሕዝቡ ላይ የወረደው መቅሠፍት እንዲወገድ ለእግዚአብሔር መሠዊያ እሠራ ዘንድ ዐውድማህን ልውሰደው፤ ሙሉውን ዋጋ እከፍልሃለሁ” አለው። 23 ኦርናም ዳዊትን፣ “እንዲሁ ውሰደው፤ ጌታዬ ንጉሥ ደስ ያለውን ያድርግ። እነሆ፤ ለሚቃጠል መሥዋዕት በሬዎቹን፣ ለሚነድደውም ዕንጨት መውቂያ በትሮቹን፣ ስንዴውን ደግሞ ለእህል ቍርባን እንዲሆን እሰጣለሁ፤ ሁሉንም እኔ እሰጣለሁ” አለ። 24 ንጉሥ ዳዊት ግን ኦርናን “እንዲህ አይደረግም፤ ሙሉውን ዋጋ እኔ እከፍላለሁ፤ የአንተ የሆነውን ለእግዚአብሔር ለማቅረብ አልፈልግም፤ ዋጋ ያልከፈልሁበትንም የሚቃጠል መሥዋዕት አድርጌ አላቀርብም” ሲል መለሰለት። 25 ስለዚህም ዳዊት ለኦርና የቦታውን ዋጋ ስድስት መቶ ሰቅል ወርቅ ከፈለ። 26 ዳዊትም በዚያ ለእግዚአብሔር መሠዊያ ሠራ፤ የሚቃጠል መሥዋዕትና የኅብረት መሥዋዕት አቀረበ። እግዚአብሔርንም ጠራ፤ እግዚአብሔርም የሚቃጠል መሥዋዕት በሚቀርብበት መሠዊያ ላይ ከሰማይ በእሳት መለሰለት። 27 ከዚያም እግዚአብሔር ለመልአኩ ተናገረ፤ መልአኩም ሰይፉን ወደ አፎቱ መለሰ። 28 በዚያ ጊዜ ዳዊት፣ እግዚአብሔር በኢያቡሳዊው በኦርና ዐውድማ ላይ እንደ መለሰለት ሲያይ፣ በዚያው ቦታ መሥዋዕት ማቅረብ ጀመረ። 29 ሙሴ በምድረ በዳ የሠራው የእግዚአብሔር ማደሪያ ድንኳንና የሚቃጠል መሥዋዕት የሚቀርብበት መሠዊያ በዚያ ጊዜ በገባዖን ኰረብታ ላይ ነበረ። 30 ዳዊት የእግዚአብሔርን መልአክ ሰይፍ ስለ ፈራ ወደዚያ ሄዶ እግዚአብሔርን ለመጠየቅ አልቻለም። |
መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™
የቅጂ መብት © 2001, 2024 በBiblica, Inc.
በፈቃድ የሚወሰድ። በዓለም ዐቀፍ ባለቤትነቱ።
The Holy Bible, New Amharic Standard Version™
Copyright © 2001, 2024 by Biblica, Inc.
Used with permission. All rights reserved worldwide.
Biblica, Inc.