Biblia Todo Logo
在线圣经

- 广告 -

1 ዜና መዋዕል 19 - አዲሱ መደበኛ ትርጒም


ከአሞናውያን ጋራ የተደረገ ጦርነት
19፥1-19 ተጓ ምብ – 2ሳሙ 10፥1-19

1 ከዚህ በኋላ የአሞናውያን ንጉሥ ናዖስ ሞተ፤ ልጁም በእግሩ ተተክቶ ነገሠ።

2 ዳዊትም፣ “አባቱ ለእኔ በጎ ነገር እንዳደረገልኝ እስኪ እኔም ለናዖስ ልጅ ለሐኖን በጎ ነገር ላድርግለት” ብሎ ዐሰበ። ስለዚህ ዳዊት ስለ አባቱ ሞት ሐዘኑን ለመግለጽ ወደ ሐኖን መልክተኞችን ላከ። የዳዊት ሰዎች ሐዘናቸውን ለመግለጽ ሐኖን ወደሚኖርበት ወደ አሞናውያን ምድር በመጡ ጊዜ፣

3 የአሞናውያን መኳንንት ለሐኖን፣ “ዳዊት ሐዘኑን ለመግለጽ ሰዎችን ወደ አንተ የላከው አባትህን አክብሮ ይመስልሃልን? ሰዎቹ ወደ አንተ የመጡት አገሪቱን ለመመርመር፣ ለመሰለልና ለመያዝ አይደለምን?” አሉት።

4 ስለዚህ ሐኖን የዳዊትን ሰዎች ይዞ ላጫቸው፤ ልብሳቸውንም እስከ መቀመጫቸው ድረስ መኻል ለመኻል ቀዶ ሰደዳቸው።

5 በሰዎቹ ላይ የደረሰባቸውን ዳዊት በሰማ ጊዜ እጅግ ዐፍረው ስለ ነበር፣ ወደ እነርሱ መልክተኞችን ላከ፤ ንጉሡም፣ “ጢማችሁ እስኪያድግ ድረስ በኢያሪኮ ቈዩና ከዚያ በኋላ ትመጣለችሁ” አለ።

6 አሞናውያን በዳዊት ዘንድ እንደ ተጠሉ ባወቁ ጊዜ፣ ሐኖንና አሞናውያን ከመስጴጦምያ፣ ከአራም መዓካና ከሱባ ሠረገሎችንና ፈረሰኞችን ለመከራየት አንድ ሺሕ መክሊት ብር ላኩ።

7 ከዚያም ሠላሳ ሁለት ሺሕ ሠረገሎችንና ፈረሰኞችን እንዲሁም የመዓካን ንጉሥና ወታደሮች በገንዘብ ቀጠሩ፤ እነርሱም መጥተው በሜድባ አጠገብ ሲሰፍሩ፣ አሞናውያን ደግሞ ከየከተሞቻቸው ተሰብስበው ለጦርነት ወጡ።

8 ዳዊት ይህን ሲሰማ ኢዮአብንና መላውን ተዋጊ ሰራዊት ላከ።

9 አሞናውያንም መጥተው ወደ ከተማቸው በሚያስገባው በር ላይ ለጦርነት ተሰለፉ፤ የመጡት ነገሥታት ደግሞ ብቻቸውን በሜዳው ላይ ነበሩ።

10 ኢዮአብም ከፊቱና ከኋላው ጦር መኖሩን አየ፤ ስለዚህ በእስራኤል የታወቁትን ጀግኖች መርጦ ሶርያውያንን እንዲገጥሙ አሰለፋቸው።

11 የቀሩትም ሰዎች በወንድሙ በአቢሳ ሥር ሆነው አሞናውያንን እንዲገጥሙ አሰለፋቸው።

12 ኢዮአብም እንዲህ አለ፤ “ሶርያውያን ከበረቱብኝ አንተ ትረዳኛለህ፤ አሞናውያን ከበረቱብህ ደግሞ እኔ እረዳሃለሁ።

13 እንግዲህ በርቱ፤ ለሕዝባችንና ለአምላካችን ከተሞች በጀግንነት እንዋጋ፤ እግዚአብሔርም በፊቱ ደስ ያሠኘውን ያድርግ።”

14 ከዚያም ኢዮአብና ዐብረውት ያሉት ወታደሮች ሶርያውያንን ለመውጋት ወደ ፊት ገሠገሡ፤ ሶርያውያንም ከፊታቸው ሸሹ።

15 አሞናውያንም ሶርያውያን መሸሻቸውን ሲያዩ፣ እነርሱም ከወንድሙ ከአቢሳ ፊት ሸሽተው ወደ ከተማዪቱ ገቡ፤ ስለዚህ ኢዮአብ ወደ ኢየሩሳሌም ተመለሰ።

16 ሶርያውያን በእስራኤላውያን እንደ ተሸነፉ ባዩ ጊዜ፣ መልእክተኞችን ልከው ከኤፍራጥስ ወንዝ ማዶ ያሉትን ሶርያውያን አስመጡ፤ እነዚህንም የሚመራቸው የአድርአዛር ሰራዊት አዛዥ ሾፋክ ነበረ።

17 ዳዊት ይህን በሰማ ጊዜ፣ እስራኤልን ሁሉ ሰብስቦ ዮርዳኖስን ተሻገረ፤ ወደ ፊት በመገሥገሥም ከፊት ለፊታቸው የውጊያ መሥመሩን ያዘ። ዳዊትም ሶርያውያንን ጦርነት ለመግጠም ወታደሮቹን አሰለፈ፤ እነርሱም ተዋጉት።

18 ይሁን እንጂ ከእስራኤል ፊት ሸሹ። ዳዊትም ሰባት ሺሕ ሠረገለኞችና አርባ ሺሕ እግረኛ ወታደሮች ገደለ። የሰራዊታቸው አዛዥ ሾፋክም በጦርነቱ ላይ ሞተ።

19 የአድርአዛርም ሹማምት በእስራኤል መሸነፋቸውን ሲያዩ፣ ከዳዊት ጋራ ታረቁ፤ ገባሮቹም ሆኑ። ስለዚህ ሶርያውያን ከዚህ ጊዜ ጀምሮ አሞናውያንን ለመርዳት ፈቃደኞች አልሆኑም።

መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™

የቅጂ መብት © 2001, 2024 በBiblica, Inc.

በፈቃድ የሚወሰድ። በዓለም ዐቀፍ ባለቤትነቱ።

The Holy Bible, New Amharic Standard Version™

Copyright © 2001, 2024 by Biblica, Inc.

Used with permission. All rights reserved worldwide. 

Biblica, Inc.
跟着我们:



广告