Biblia Todo Logo
在线圣经

- 广告 -

1 ዜና መዋዕል 18 - አዲሱ መደበኛ ትርጒም


ዳዊት የተቀዳጃቸው ድሎች
18፥1-13 ተጓ ምብ – 2ሳሙ 8፥1-14

1 ከዚህ በኋላ ዳዊት ፍልስጥኤማውያንን ድል መትቶ ተገዥ አደረጋቸው፤ ጋትንና በዙሪያዋም የሚገኙትን መንደሮች ከፍልስጥኤማውያን እጅ ወሰደ።

2 እንዲሁም ዳዊት ሞዓባውያንን ድል አደረጋቸው፤ እነርሱም ገባሮቹ ሆኑ፤ ግብርም አመጡለት።

3 ከዚህም በላይ ዳዊት በኤፍራጥስ ወንዝ አጠገብ የነበረውን ግዛት ለመቈጣጠር በሄደ ጊዜ፣ የሱባን ንጉሥ አድርአዛርን እስከ ሐማት ድረስ ዘልቆ ወጋው።

4 ዳዊትም አንድ ሺሕ ሠረገላ፣ ሰባት ሺሕ ፈረሰኛና ሃያ ሺሕ እግረኛ ወታደር ማረከ፤ አንድ መቶ የሠረገላ ፈረሶች ብቻ አስቀርቶ የቀሩትን ቋንጃቸውን ቈረጠ።

5 ሶርያውያንም የሱባን ንጉሥ አድርአዛርን ለመርዳት ከደማስቆ በመጡ ጊዜ፣ ዳዊት ሃያ ሁለት ሺሕ ሰው ገደለ።

6 ከዚያም በሶርያ ግዛት ውስጥ ባለችው በደማስቆ የጦር ሰፈር አቋቋመ፤ ሶርያውያንም ገባሮቹ ሆኑ፤ ግብርም አመጡለት። እግዚአብሔርም ዳዊትን በሄደበት ሁሉ ድልን ሰጠው።

7 ዳዊትም የአድርአዛር ጦር አለቆች ያነገቧቸውን የወርቅ ጋሻዎች ወሰደ፤ ወደ ኢየሩሳሌምም አመጣቸው።

8 ዳዊት ከአድርአዛር ከተሞች ከጢብሐትና ከኩን እጅግ ብዙ ናስ ወሰደ፤ ሰሎሞን የናሱን ባሕር፣ ዐምዶቹንና ልዩ ልዩ የናስ ዕቃዎቹን የሠራው በዚሁ ነበር።

9 የሐማት ንጉሥ ቶዑ፣ ዳዊት የሱባን ንጉሥ የአድርአዛርን ሰራዊት ሁሉ ድል እንደ መታ ሲሰማ፣

10 እጅ እንዲነሣውና ደስታውንም እንዲገልጥለት ልጁን አዶራምን ወደ ንጉሥ ዳዊት ላከው፤ ቶዑ ከአድርአዛር ጋራ ብዙ ጊዜ ጦርነት ገጥሞ ነበር። አዶራምም ከወርቅ፣ ከብርና ከናስ የተሠሩ ልዩ ልዩ ዕቃዎች አመጣለት።

11 ንጉሥ ዳዊት ከኤዶምና ሞዓብ፣ ከአሞናውያን፣ ከፍልስጥኤማውያንና ከአማሌቃውያን፣ ከእነዚህ ሁሉ መንግሥታት የማረከውን ወርቅና ብር ከዚህ ቀደም እንዳደረገው ሁሉ፣ እነዚህንም ዕቃዎች ለእግዚአብሔር ቀደሰ።

12 የጽሩያ ልጅ አቢሳ በጨው ሸለቆ ዐሥራ ስምንት ሺሕ ኤዶማውያን ገደለ።

13 እርሱም በኤዶም የጦር ሰፈሮችን አቋቋመ፤ ኤዶማውያንም ሁሉ ለንጉሥ ዳዊት ገባሮች ሆኑ። እግዚአብሔርም ዳዊትን በሄደበት ሁሉ ድልን ሰጠው።


የዳዊት ሹማምት
18፥14-17 ተጓ ምብ – 2ሳሙ 8፥15-18

14 ዳዊት በመላው እስራኤል ላይ ነገሠ፤ ለሕዝቡም ሁሉ ፍትሕንና ጽድቅን አሰፈነላቸው።

15 የጽሩያ ልጅ ኢዮአብ የሰራዊቱ አዛዥ ነበረ፤ የአሒሉድ ልጅ ኢዮሣፍጥ ደግሞ የቤተ መዛግብቱ ኀላፊ ነበረ።

16 የአኪጦብ ልጅ ሳዶቅና የአብያታር ልጅ አቢሜሌክ ካህናት ነበሩ፤ ሱሳ ደግሞ ጸሓፊ ነበረ።

17 የዮዳሄ ልጅ በናያስ የከሊታውያንና የፈሊታውያን አዛዥ ነበር፤ የዳዊት ወንዶች ልጆቹ ደግሞ ከንጉሡ ቀጥሎ የበላይ ሹማምት ነበሩ።

መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™

የቅጂ መብት © 2001, 2024 በBiblica, Inc.

በፈቃድ የሚወሰድ። በዓለም ዐቀፍ ባለቤትነቱ።

The Holy Bible, New Amharic Standard Version™

Copyright © 2001, 2024 by Biblica, Inc.

Used with permission. All rights reserved worldwide. 

Biblica, Inc.
跟着我们:



广告