1 ዜና መዋዕል 17 - አዲሱ መደበኛ ትርጒምእግዚአብሔር ለዳዊት የሰጠው ተስፋ 17፥1-15 ተጓ ምብ – 2ሳሙ 7፥1-17 1 ዳዊት በቤተ መንግሥቱ ተደላድሎ በተቀመጠበት ጊዜ፣ ነቢዩ ናታንን “እነሆ፤ እኔ ከዝግባ በተሠራ ቤተ መንግሥት ውስጥ እኖራለሁ፤ የእግዚአብሔር የኪዳኑ ታቦት ግን በድንኳን ውስጥ ይኖራል” አለው። 2 ናታንም ለዳዊት፣ “እግዚአብሔር ከአንተ ጋራ ስለ ሆነ፣ ያሰብኸውን ሁሉ አድርግ” ሲል መለሰለት። 3 በዚያች ሌሊት የእግዚአብሔር ቃል ወደ ናታን እንዲህ ሲል መጣ፤ 4 “ሂድና ባሪያዬን ዳዊትን እንዲህ ብለህ ንገረው፤ እግዚአብሔር የሚለው ይህን ነው፤ ‘እኔ የምኖርበትን ቤት የምትሠራልኝ አንተ አይደለህም። 5 እስራኤልን ከግብጽ ምድር ካወጣሁበት ቀን ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ፣ ከአንዱ ድንኳን ወደ ሌላው ድንኳን፣ ከአንዱ ማደሪያ ወደ ሌላው ማደሪያ እሄድ ነበር እንጂ፣ በቤት ውስጥ አልተቀመጥሁም። 6 በእስራኤላውያን ሁሉ መካከል ባለፍሁባቸው ቦታዎች ሁሉ፣ ሕዝቤን እንዲጠብቁ ካዘዝኋቸው መሪዎቻቸው “ለምን ከዝግባ ዕንጨት ቤት አልሠራችሁልኝም” ያልሁት አለን?’ 7 “አሁንም ባሪያዬ ዳዊትን እንዲህ በለው፤ የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ ‘በሕዝቤ በእስራኤል ላይ ገዥ እንድትሆን ከሜዳ አነሣሁህ፤ ከበግ ጥበቃም ወሰድሁህ። 8 በሄድህበት ሁሉ ከአንተ አልተለየሁም፤ ጠላቶችህንም ሁሉ ከፊትህ አጠፋሁልህ፤ አሁንም ስምህን እንደ ምድር ታላላቅ ሰዎች ስም ገናና አደርገዋለሁ። 9 የራሳቸውም መኖሪያ ስፍራ እንዲኖራቸው፣ ከእንግዲህ በኋላም እንዳይናወጡ ለሕዝቤ ለእስራኤል መኖሪያ ስፍራ እሰጣቸዋለሁ። ከዚህ ቀደም እንዳደረጉት ክፉዎች ከእንግዲህ አይጨቍኗቸውም፤ 10 ከዚህ ቀደም በሕዝቤ በእስራኤል ላይ መሪዎች በሾምሁ ጊዜ ጨቋኞቹ ያደረጉትን ዛሬ አያደርጉትም፤ ጠላቶቻችሁን ሁሉ አዋርዳቸዋለሁ። “ ‘እግዚአብሔር ቤት እንደሚሠራልህ በግልጽ እነግርሃለሁ፤ 11 ዘመንህን ጨርሰህ ወደ አባቶችህ በምትሄድበት ጊዜ፣ ከአብራክህ ከተከፈሉት ልጆችህ አንዱ በእግርህ እንዲተካ አደርጋለሁ፤ መንግሥቱንም አጸናለሁ፤ 12 ቤት የሚሠራልኝም እርሱ ነው፤ እኔም ዙፋኑን ለዘላለም አጸናለሁ። 13 አባት እሆነዋለሁ፤ እርሱም ልጄ ይሆናል፤ ጽኑ ፍቅሬን ከአንተ በፊት ከነበረው ላይ እንዳራቅሁ ሁሉ፣ ከርሱ ላይ ከቶ አልወስድም። 14 በቤቴና በመንግሥቴ ላይ ለዘላለም አኖረዋለሁ፤ ዙፋኑም ለዘላለም ይጸናል።’ ” 15 ናታንም የዚህን ራእይ ቃል በሙሉ ለዳዊት ነገረው። የዳዊት ጸሎት 17፥16-27 ተጓ ምብ – 2ሳሙ 7፥18-29 16 ከዚያም ንጉሥ ዳዊት ገባ፤ በእግዚአብሔር ፊት ተቀምጦም እንዲህ አለ፤ “እግዚአብሔር አምላክ ሆይ፤ ለመሆኑ እስከዚህ ያደረስኸኝ እኔ ማን ነኝ? ቤቴስ ምንድን ነው? 17 አምላክ ሆይ፤ ይህ በፊትህ በቂ እንዳልሆነ ቈጥረህ ስለ ወደ ፊቱ የባሪያህ ቤት ተናገርህ። እግዚአብሔር አምላክ ሆይ፤ እኔንም ከሰዎች ሁሉ እጅግ የከበረ ሰው አድርገህ ተመለከትኸኝ። 18 “ባሪያህን ስላከበርኸው፣ ዳዊት ከዚህ በላይ ምን ሊልህ ይችላል? ባሪያህን አንተ ታውቀዋለህ፤ 19 እግዚአብሔር ሆይ፤ ስለ ባሪያህ ብለህና እንደ ፈቃድህም መሠረት ይህን ታላቅ ነገር አድርገሃል፤ እነዚህም ታላላቅ ተስፋዎች ሁሉ እንዲታወቁ አደረግህ። 20 “አቤቱ፤ እግዚአብሔር እንደ አንተ ያለ ማንም የለም፤ በጆሯችን እንደ ሰማነው ሁሉ ከአንተ በቀር አምላክ የለም። 21 ከግብጽ ተቤዥተህ እንዳወጣኸው እንደ ሕዝብህ እንደ እስራኤል ያለ ማን አለ? እነርሱ እግዚአብሔር ለራሱ ሊቤዣቸው ከምድር ሕዝቦች መካከል የመረጣቸው ናቸው፤ በሕዝብህም ፊት ታላላቅና አስፈሪ ነገሮችን በማድረግ መንግሥታትን በፊታቸው አሳደድህ። 22 ሕዝብህንም እስራኤልን ለዘላለም የራስህ ሕዝብ አደረግኸው፤ እግዚአብሔር ሆይ፤ አንተም አምላክ ሆንህለት። 23 “እግዚአብሔር ሆይ፤ አሁንም ለባሪያህና ለቤቱ የሰጠኸውን ተስፋ ለዘላለም የጸና ይሁን፤ እንደተናገርኸውም ፈጽም፤ 24 ይህም ስምህ ጸንቶ እንዲኖርና ለዘላለምም ታላቅ እንዲሆን ነው። ከዚያም ሰዎች ‘የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር የእስራኤል አምላክ ነው!’ ይላሉ፤ የባሪያህ የዳዊትም ቤት በፊትህ የጸና ይሆናል። 25 “አምላኬ ሆይ፤ ቤት እንደምትሠራለት ለባሪያህ ገልጸህለታል፤ ስለዚህ ባሪያህ ወደ አንተ ለመጸለይ ድፍረት አገኘ። 26 አሁንም እግዚአብሔር ሆይ፤ አንተ አምላክ ነህ፤ ይህንም መልካም ነገር ለማድረግ ለባሪያህ ተስፋ ሰጥተኸዋል። 27 በፊትህ ለዘላለም እንዲኖር አሁንም የባሪያህን ቤት ልትባርክ ወድደሃል፤ እግዚአብሔር ሆይ፤ የባረክኸው አንተ ስለ ሆንህ፣ ለዘላለም የተባረከ ይሆናል።” |
መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™
የቅጂ መብት © 2001, 2024 በBiblica, Inc.
በፈቃድ የሚወሰድ። በዓለም ዐቀፍ ባለቤትነቱ።
The Holy Bible, New Amharic Standard Version™
Copyright © 2001, 2024 by Biblica, Inc.
Used with permission. All rights reserved worldwide.
Biblica, Inc.