1 ዜና መዋዕል 14 - አዲሱ መደበኛ ትርጒምየዳዊት ቤትና ቤተ ሰቡ 14፥1-7 ተጓ ምብ – 2ሳሙ 5፥11-16 ፤ 1ዜና 3፥5-8 1 በዚህ ጊዜ የጢሮስ ንጉሥ ኪራም ለዳዊት ቤተ መንግሥት እንዲሠሩ መልክተኞችን፣ ድንጋይ ጠራቢዎችንና የእጅ ጥበብ ባለሙያዎችን ከዝግባ ዕንጨት ጋራ ላከ። 2 ዳዊትም እግዚአብሔር በእስራኤል ላይ ንጉሥነቱን እንዳጸናለት፣ ስለ ሕዝቡ ስለ እስራኤልም ሲል መንግሥቱን እጅግ ከፍ ከፍ እንዳደረገለት ተገነዘበ። 3 ዳዊት በኢየሩሳሌም ተጨማሪ ሚስቶች አገባ፤ ሌሎች ወንዶችና ሴቶች ልጆችም ወለደ። 4 በኢየሩሳሌም የተወለዱለትም ልጆች ስም ይህ ነው፤ ሳሙስ፣ ሶባብ፣ ናታን፣ ሰሎሞን፣ 5 ኢያቤሐር፣ ኤሊሱዔ፣ ኤሊፋላት፣ 6 ኖጋ፣ ናፌቅ፣ ያፍያ፣ 7 ኤሊሳማ፣ ኤሊዳሄ፣ ኤሊፋላት። ዳዊት ፍልስጥኤማውያንን ድል አደረገ 14፥8-17 ተጓ ምብ – 2ሳሙ 5፥17-25 8 ዳዊት በእስራኤል ሁሉ ላይ ንጉሥ ሆኖ መቀባቱን ፍልስጥኤማውያን በሰሙ ጊዜ፣ እርሱን ፍለጋ በሙሉ ኀይላቸው ወጡ፤ ዳዊትም ይህን ሰምቶ ስለ ነበር ሊገጥማቸው ወጣ። 9 በዚህ ጊዜ ፍልስጥኤማውያን መጥተው የራፋይምን ሸለቆ ወረሩ። 10 ስለዚህም ዳዊት፣ “በፍልስጥኤማውያን ላይ ወጥቼ ልምታቸውን? በእጄስ አሳልፈህ ትሰጣቸዋለህን?” ሲል እግዚአብሔርን ጠየቀ። እግዚአብሔርም፣ “አዎን ውጣ! በእጅህ አሳልፌ እሰጣቸዋለሁ” ብሎ መለሰለት። 11 ስለዚህ ዳዊትና ሰዎቹ ወደ በኣልፐራሲም ወጡ፤ በዚያም ድል አደረጋቸው። ዳዊትም፣ “የጐርፍ ውሃ ጥሶ በመውጣት እንደሚያፈራርስ ሁሉ እግዚአብሔርም ጠላቶቼን በእጄ አፈራረሳቸው” አለ፤ ከዚህ የተነሣም የዚያ ቦታ ስም “በኣልፐራሲም” ተባለ። 12 ፍልስጥኤማውያን አማልክታቸውን በዚያው ጥለዋቸው ስለ ነበር፣ ዳዊት በእሳት እንዲያቃጥሏቸው አዘዘ። 13 ፍልስጥኤማውያን ሸለቆውን እንደ ገና ወረሩ፤ 14 ዳዊትም እንደ ገና እግዚአብሔርን ጠየቀ። እግዚአብሔርም እንዲህ ሲል መለሰለት “ዙሪያውን ከብበህ በሾላው ዛፍ ፊት ለፊት አደጋ ጣልባቸው እንጂ ከኋላቸው በቀጥታ ወደ ላይ አትውጣ፤ 15 በሾላው ዐናት ላይ የሰልፍ ድምፅ ስትሰማ ወዲያውኑ ለጦርነት ውጣ፤ ይህም የፍልስጥኤማውያንን ሰራዊት ለመምታት እግዚአብሔር በፊትህ ወጥቷል ማለት ነውና።” 16 ስለዚህም ዳዊት እግዚአብሔር እንዳዘዘው አደረገ፤ ከገባዖን ጀምሮ እስከ ጌዝር ድረስ ፍልስጥኤማውያንን መቷቸው። 17 ከዚህም የተነሣ የዳዊት ዝና በየአገሩ ሁሉ ተሰማ፤ እግዚአብሔርም መንግሥታት ሁሉ እንዲፈሩት አደረገ። |
መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™
የቅጂ መብት © 2001, 2024 በBiblica, Inc.
በፈቃድ የሚወሰድ። በዓለም ዐቀፍ ባለቤትነቱ።
The Holy Bible, New Amharic Standard Version™
Copyright © 2001, 2024 by Biblica, Inc.
Used with permission. All rights reserved worldwide.
Biblica, Inc.