Biblia Todo Logo
在线圣经

- 广告 -

1 ዜና መዋዕል 13 - አዲሱ መደበኛ ትርጒም


የታቦቱ መመለስ
13፥1-14 ተጓ ምብ – 2ሳሙ 6፥1-11

1 ዳዊትም ሻለቆችና መቶ አለቆች ከሆኑት የጦር ሹማምቱ ሁሉ ጋራ ተማከረ።

2 ከዚያም ለመላው የእስራኤል ማኅበር እንዲህ አለ፤ “እንግዲህ ነገሩ መልካም መስሎ ከታያችሁና የአምላካችን የእግዚአብሔር ፈቃድ ከሆነ፣ በእስራኤል ግዛት ሁሉ ለሚኖሩ በሩቅም ሆነ በቅርብ ላሉት ለቀሩት ወንድሞቻችን እንዲሁም በየራሳቸው ከተሞችና መሰማሪያዎች የሚኖሩ ካህናትና ሌዋውያን መጥተው ከእኛ ጋራ እንዲሰባሰቡ እንላክባቸው።

3 በሳኦል ዘመነ መንግሥት ሳንፈልገው የነበረውን የአምላካችንን ታቦት መልሰን ወደ እኛ እናምጣ”።

4 ነገሩም በሕዝቡ ሁሉ ዘንድ ተቀባይነት ስላገኘ መላው ማኅበር ይህንኑ ለማድረግ ተስማማ።

5 ስለዚህ ዳዊት የእግዚአብሔርን ታቦት ከቂርያትይዓይሪም ለማምጣት ከግብጽ ወንዝ ከሺሖር ጀምሮ እስከ ለቦ ሐማት ድረስ የሰፈሩትን እስራኤላውያን ሁሉ ሰበሰበ።

6 ዳዊትና እስራኤላውያን ሁሉ በኪሩብና በኪሩብ መካከል የተቀመጠውን ስሙም በርሱ የተጠራውን፣ የእግዚአብሔር አምላክን ታቦት ከዚያ ለማምጣት በይሁዳ ወዳለችው ቂርያትይዓይሪም ወደተባለችው ወደ በኣላ ሄዱ።

7 የእግዚአብሔርንም ታቦት ከአሚናዳብ ቤት በአዲስ ሠረገላ ላይ አድርገው አመጡት፤ ሠረገላውን ይነዱ የነበሩትም ዖዛና አሒዮ ነበሩ።

8 ዳዊትና እስራኤላውያን ሁሉ በእግዚአብሔር ፊት ሆነው በቅኔና በበገና፣ በመሰንቆና በከበሮ፣ በጸናጽልና በመለከት በሙሉ ኀይላቸው በዓሉን በደስታ ያከብሩ ነበር።

9 ወደ ኪዶን ዐውድማ በደረሱ ጊዜ በሬዎቹ አደናቅፏቸው ስለ ነበር፣ ዖዛ ታቦቱን ለመደገፍ እጁን ዘረጋ።

10 ታቦቱን በእጁ ስለ ነካ፣ የእግዚአብሔር ቍጣ በዖዛ ላይ ነደደ፤ ስለዚህም በዚያው በእግዚአብሔር ፊት ሞተ።

11 የእግዚአብሔር ቍጣ ዖዛን በድንገት ስለ ቀሠፈው ዳዊት ዐዘነ፤ ያም ቦታ እስከ ዛሬ ድረስ የፔሬዝ ዖዛ ስብራት ተብሎ ይጠራል።

12 ዳዊት በዚያ ዕለት እግዚአብሔርን ስለ ፈራ፣ “ታዲያ የእግዚአብሔርን ታቦት ወደ እኔ እንዴት ማምጣት እችላለሁ?” አለ።

13 ስለዚህ ታቦቱን ወደ ዳዊት ከተማ በመውሰድ ፈንታ የጋት ሰው ወደ ሆነው ወደ አቢዳራ ቤት ወሰደው።

14 የእግዚአብሔርንም ታቦት በአቢዳራ ቤት ከቤተ ሰቡ ጋራ ሦስት ወር ተቀመጠ፤ እግዚአብሔርም ቤተ ሰቡንና ያለውንም ሁሉ ባረከ።

መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™

የቅጂ መብት © 2001, 2024 በBiblica, Inc.

በፈቃድ የሚወሰድ። በዓለም ዐቀፍ ባለቤትነቱ።

The Holy Bible, New Amharic Standard Version™

Copyright © 2001, 2024 by Biblica, Inc.

Used with permission. All rights reserved worldwide. 

Biblica, Inc.
跟着我们:



广告