1 ዜና መዋዕል 12 - አዲሱ መደበኛ ትርጒምከዳዊት ጋራ የተቀላቀሉ ተዋጊዎች 1 ዳዊት ከቂስ ልጅ ከሳኦል ፊት ሸሽቶ በጺቅላግ ሳለ ወደ እርሱ የመጡት ሰዎች እነዚህ ናቸው፤ እነርሱም በጦርነቱ ላይ ከረዱት ተዋጊዎች መካከል ነበሩ። 2 ሰዎቹ ቀስተኞች ሲሆኑ፣ በቀኝም ሆነ በግራ እጃቸው ፍላጻ መወርወርና ድንጋይ መወንጨፍ የሚችሉ ነበሩ፤ እነርሱም ከብንያም ነገድ የሆነው የሳኦል ሥጋ ዘመዶች ነበሩ፤ 3 አለቃቸው አሒዔዝር ነበረ፤ ከርሱም በኋላ ኢዮአስ ነበረ፤ ሁለቱም የጊብዓዊው የሸማዓ ልጆች ነበሩ፤ የዓዝሞት ልጆች ይዝኤልና ፋሌጥ፣ በራኪያ፣ ዓናቶታዊው ኢዩ፤ 4 ገባዖናዊው ሰማያስ ከሠላሳዎቹ መካከል ኀያልና የሠላሳዎቹም መሪ ነበረ፤ ኤርምያስ፣ የሕዚኤል፣ ዮሐናን፣ ገድሮታዊው ዮዛባት፣ 5 ኤሉዛይ፣ ለኢያሪሙት፣ በዓልያ፣ ሰማራያ፣ ሐሩፋዊው ሰፋጥያስ፣ 6 ቆሬያውያኑ ሕልቃና፣ ይሺያ፣ ዓዘርኤል፣ ዮዛር፣ ያሾብዓም፤ 7 የጌዶር ሰው ከሆነው ደግሞ የይሮሐም ልጆች ዮዔላና ዝባድያ። 8 ዳዊት በምድረ በዳ በሚገኘው ምሽጉ ውስጥ ሳለ፣ ከጋድ ነገድ የሆኑ ሰዎች መጥተው የርሱን ሰራዊት ተቀላቀሉ፤ እነርሱም ለውጊያ የተዘጋጁ ጋሻና ጦር ለመያዝ የሚችሉ ብርቱ ተዋጊዎች ነበሩ፤ ፊታቸው እንደ አንበሳ ፊት የሚያስፈራና በየተራራውም ላይ እንደሚዘልል ሚዳቋ ፈጣኖች ነበሩ። 9 የእነዚህም አለቃ ዔጼር ነበረ፤ ሁለተኛው አዛዥ አብድዩ፣ ሦስተኛው ኤልያብ፣ 10 አራተኛው መስመና፣ ዐምስተኛው ኤርምያስ፣ 11 ስድስተኛው ዓታይ፣ ሰባተኛው ኤሊኤል፣ 12 ስምንተኛው ዮሐናን፣ ዘጠነኛው ኤልዛባድ፣ 13 ዐሥረኛው ኤርምያስ፣ ዐሥራ አንደኛው መክበናይ። 14 እነዚህ ጋዳውያን የጦር አዛዦች ነበሩ፣ ከእነርሱ ታናሽ የሆነው እንደ መቶ፣ ታላቅ የሆነው ደግሞ እንደ ሺሕ አለቃ ይቈጠር ነበር። 15 በመጀመሪያው ወር የዮርዳኖስ ወንዝ ከአፍ እስከ ገደፍ ሞልቶ ሳለ፣ ወንዙን ተሻግረው በስተ ምሥራቅና በስተ ምዕራብ ሸለቆዎች ይኖሩ የነበሩትን ሁሉ ከዚያ ያባረሩት እነዚህ ሰዎች ነበሩ። 16 ሌሎች ከብንያምና ከይሁዳም ወገን የሆኑ ሰዎች ዳዊት ወደሚገኝበት ምሽግ መጡ። 17 ዳዊትም እነዚህን ሰዎች ሊቀበል ወጥቶ እንዲህ አላቸው፤ “የመጣችሁት ልትረዱኝና በሰላም ከሆነ፣ ከእኔ ጋራ እንድትሰለፉ ልቀበላችሁ ዝግጁ ነኝ፤ ነገር ግን እጄ ከበደል ንጹሕ ሆኖ ሳለ፣ ለጠላቶቼ አሳልፋችሁ ልትሰጡኝ ከሆነ፣ የአባቶቻችን አምላክ ይመልከተው፤ ይፍረደውም።” 18 ከዚያም መንፈስ በሠላሳዎቹ አለቃ በዓማሣይ ላይ ወረደ፤ እርሱም እንዲህ አለ፤ “ዳዊት ሆይ፤ እኛ የአንተ ነን፤ የእሴይ ልጅ ሆይ፤ እኛ ከአንተ ጋራ ነን፤ ሰላም ፍጹም ሰላም ለአንተ ይሁን፤ አንተን ለሚረዱም ሁሉ ሰላም ይሁን፤ አምላክህ ይረዳሃልና።” ስለዚህ ዳዊት ተቀበላቸው፤ የሰራዊቱም አለቃ አደረጋቸው። 19 ዳዊት ከፍልስጥኤማውያን ጋራ ተባብሮ ሳኦልን ለመውጋት በሄደ ጊዜ፣ ከምናሴ ነገድ የሆኑ ጥቂት ሰዎች ከድተው ከዳዊት ሰራዊት ጋራ ተቀላቀሉ። እርሱ ግን ርዳታ አላደረገላቸውም፤ ምክንያቱም የፍልስጥኤማውያን ገዦች ምክር ካደረጉ በኋላ እንዲህ ሲሉ ልከውት ነበር፤ “ከድቶ ወደ ጌታው ወደ ሳኦል ቢሄድ እኛን ያስጨርሰናል።” 20 ዳዊት ወደ ጺቅላግ በሄደ ጊዜ ከድተው ወደ እርሱ የተቀላቀሉ የምናሴ ነገድ ሰዎች እነዚህ ነበሩ፤ ዓድና፣ ዮዛባት፣ ይዲኤል፣ ሚካኤል፣ ዮዛባት፣ ኤሊሁ፣ ጺልታይ፤ እነዚህ በምናሴ ግዛት ሳሉ ሻለቆች ነበሩ። 21 ሁሉም ብርቱ ተዋጊዎችና በዳዊትም ሰራዊት ውስጥ አዛዦች ስለ ነበሩ፣ አደጋ ጣዮችን በመውጋት ረዱት። 22 ሰራዊቱም እንደ እግዚአብሔር ሰራዊት እስኪሆን ድረስ፣ ዳዊትን ለመርዳት በየዕለቱ ብዙ ሰዎች ይጐርፉ ነበር። ሌሎችም በኬብሮን የዳዊትን ሰራዊት ተቀላቀሉ 23 እግዚአብሔር ለዳዊት በገባለት ቃል ኪዳን መሠረት፣ የሳኦልን መንግሥት አንሥተው ለርሱ ለመስጠት ዳዊት ወደሚገኝበት ወደ ኬብሮን የመጡት ሰዎች ቍጥር ይህ ነው፤ 24 ጋሻና ጦር አንግበው ለጦርነት የተዘጋጁት የይሁዳ ሰዎች ስድስት ሺሕ ስምንት መቶ፤ 25 ከስምዖን ነገድ ለጦርነት ዝግጁ የሆኑ ሰባት ሺሕ አንድ መቶ። 26 ከሌዊ ነገድ አራት ሺሕ ስድስት መቶ፤ 27 የአሮን ቤተ ሰብ መሪ የሆነውን ዮዳሄን ጨምሮ ሦስት ሺሕ ሰባት መቶ ሰዎች፤ 28 ወጣቱ ብርቱ ተዋጊ ሳዶቅና ከቤተ ሰቡ ሃያ ሁለት የጦር አለቆች፤ 29 የሳኦል ሥጋ ዘመድ የሆኑ የብንያም ሰዎች ሦስት ሺሕ፤ ከእነዚህም አብዛኞቹ እስከዚያች ጊዜ ድረስ ለሳኦል ቤት ታማኝ ነበሩ፤ 30 ከኤፍሬም ሰዎች በጐሣዎቻቸው ዘንድ ታዋቂ የሆኑ ብርቱ ተዋጊዎች ሃያ ሺሕ ስምንት መቶ፤ 31 ከምናሴ ነገድ እኩሌታ ዐሥራ ስምንት ሺሕ ሰዎች፤ እነርሱም ዳዊትን ለማንገሥ በየስማቸው ተጽፈው የመጡ ነበሩ። 32 ዘመኑን የተረዱና እስራኤላውያንም ምን ማድረግ እንደሚገባቸው የተገነዘቡ የይሳኮር ሰዎች ሁለት መቶ አለቆች፤ በእነርሱም ሥር ሆነው የሚታዘዙ ዘመዶቻቸው። 33 ልምድ ያላቸው፣ በሁሉም ዐይነት መሣሪያ ለመዋጋት የተዘጋጁና ዳዊትን ለመርዳት የመጡት መንታ ልብ የሌላቸው የዛብሎን ሰዎች ኀምሳ ሺሕ፤ 34 ከንፍታሌም ሰዎች አንድ ሺሕ የጦር አለቆች፤ ከእነርሱም ጋራ ጋሻና ጦር የያዙ ሠላሳ ሰባት ሺሕ ሰዎች፤ 35 ከዳን ሰዎች ለጦርነት የተዘጋጁ ሃያ ስምንት ሺሕ ስድስት መቶ፤ 36 ከአሴር ሰዎች ልምድ ያላቸውና ለጦርነት የተዘጋጁ ወታደሮች አርባ ሺሕ፤ 37 ከምሥራቅ ዮርዳኖስ ከሮቤል፣ ከጋድና ከምናሴ ነገድ እኩሌታ ልዩ ልዩ ዐይነት መሣሪያ የታጠቁ አንድ መቶ ሃያ ሺሕ ሰዎች። 38 እነዚህ ሁሉ በሰራዊቱ ውስጥ ለማገልገል ፈቃደኞች የሆኑ ተዋጊዎች ናቸው። ወደ ኬብሮን የመጡትም ዳዊትን በእስራኤል ሁሉ ላይ ለማንገሥ ወስነው ስለ ነበር ነው። የቀሩትም እስራኤላውያን ሁሉ ዳዊትን ለማንገሥ በአንድ ሐሳብ ጸኑ። 39 የሚያስፈልጋቸውንም ቤተ ሰቦቻቸው አዘጋጅተውላቸው ስለ ነበር፣ ሰዎቹ እየበሉና እየጠጡ ከዳዊት ጋራ ሦስት ቀን ቈዩ። 40 እንዲሁም ሩቅ ከሆነው ከይሳኮር፣ ከዛብሎንና ከንፍታሌም አገር ሳይቀር ጎረቤቶቻቸው በአህያ፣ በግመል፣ በበቅሎና በበሬ ጭነው ምግብ አመጡላቸው፤ በእስራኤል ታላቅ ደስታ ስለ ሆነ ዱቄት፣ የበለስና የዘቢብ ጥፍጥፍ፣ የወይን ጠጅ፣ የወይራ ዘይት፣ የቀንድ ከብትና በጎች በገፍ ቀርበው ነበር። |
መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™
የቅጂ መብት © 2001, 2024 በBiblica, Inc.
በፈቃድ የሚወሰድ። በዓለም ዐቀፍ ባለቤትነቱ።
The Holy Bible, New Amharic Standard Version™
Copyright © 2001, 2024 by Biblica, Inc.
Used with permission. All rights reserved worldwide.
Biblica, Inc.