Biblia Todo Logo
在线圣经

- 广告 -

1 ዜና መዋዕል 11 - አዲሱ መደበኛ ትርጒም


ዳዊት በእስራኤል ላይ ነገሠ
11፥1-3 ተጓ ምብ – 2ሳሙ 5፥1-3

1 እስራኤል ሁሉ በኬብሮን ወደ ዳዊት ተሰብስበው እንዲህ አሉ፤ “እነሆ፤ እኛ የዐጥንትህ ፍላጭ፣ የሥጋህ ቍራጭ ነን፤

2 በቀደመው ዘመን ሳኦል ንጉሥ ሆኖ ሳለም እንኳ እስራኤልን በጦርነት የምትመራ አንተ ነበርህ፤ እግዚአብሔርም፣ ‘ሕዝቤን እስራኤልን ትጠብቃለህ፤ መሪያቸውም ትሆናለህ’ ብሎህ ነበር።”

3 ስለዚህ የእስራኤል ሽማግሌዎች በሙሉ ንጉሥ ዳዊት ወዳለበት ወደ ኬብሮን መጡ፤ ዳዊትም በኬብሮን በእግዚአብሔር ፊት ከእነርሱ ጋራ ቃል ኪዳን ገባ። እግዚአብሔር በሳሙኤል አማካይነት በተናገረው መሠረት ዳዊትን ቀብተው በእስራኤል ላይ አነገሡት።


ዳዊት ኢየሩሳሌምን ድል አደረገ
11፥4-9 ተጓ ምብ – 2ሳሙ 5፥6-10

4 ዳዊትና እስራኤላውያን ሁሉ ኢያቡስ ወደምትባለው ወደ ኢየሩሳሌም ሄዱ። በዚያም የሚኖሩ ኢያቡሳውያን

5 ዳዊትን፣ “ወደዚህ ፈጽሞ አትገባም” አሉት፤ ዳዊት ግን የጽዮንን ምሽግ ያዘ፤ እርሷም የዳዊት ከተማ ናት።

6 ዳዊትም፣ “ኢያቡሳውያንን ቀድሞ የሚወጋ ሰው የሰራዊቱ አዛዥ ይሆናል” አለ፤ ስለዚህ የጽሩያ ልጅ ኢዮአብ በመጀመሪያ ወጣ፤ እርሱም አዛዥ ለመሆን በቃ።

7 ከዚያም ዳዊት መኖሪያውን በዐምባዪቱ ውስጥ አደረገ፤ ከዚህም የተነሣ የዳዊት ከተማ ተባለች።

8 ዳዊትም ከሚሎ ጀምሮ የከተማዪቱን ዙሪያ ቅጥር ሠራ፤ ኢዮአብ ደግሞ የቀረውን የከተማዪቱን ክፍል መልሶ ሠራ።

9 የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር ከርሱ ጋራ ስለ ነበር፣ ዳዊት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየበረታ ሄደ።


የዳዊት ኀያላን ሰዎች
11፥10-41 ተጓ ምብ – 2ሳሙ 23፥8-39

10 የዳዊት ኀያላን ሰዎች አለቆች እነዚህ ናቸው፤ እነርሱም እግዚአብሔር በሰጠው ተስፋ መሠረት መንግሥቱ በምድሪቱ ሁሉ ትሰፋ ዘንድ ከሌሎቹ እስራኤላውያን ጋራ ሆነው ለመንግሥቱ ብርቱ ድጋፍ ሰጡ።

11 የዳዊት ኀያላን ሰዎች ስም ይህ ነው፤ ሐክሞናዊው ያሾብዓም የጦር መኰንኖቹ አለቃ ነበረ፤ እርሱም ጦሩን አንሥቶ በአንድ ጊዜ ሦስት መቶ ሰው ገደለ።

12 ከርሱም ቀጥሎ ከሦስቱ ኀያላን አንዱ የሆነው የአሆሃዊው የዱዲ ልጅ ኤልዔዘር ነው፤

13 እርሱም ፍልስጥኤማውያን ለጦርነት በተሰበሰቡ ጊዜ በፈስደሚም ከዳዊት ጋራ ዐብሮ ነበረ፤ ገብስ በሞላበት የዕርሻ ቦታ ወታደሮቹ ከፍልስጥኤማውያን ፊት ሸሹ፤

14 ይሁን እንጂ በዕርሻው መካከል ቦታ ይዘው ስለ ነበረ ፍልስጥኤማውያንን ገደሉ፤ እግዚአብሔርም ታላቅ ድል ሰጣቸው።

15 ከፍልስጥኤማውያን ሰራዊት ጥቂቱ በራፋይም ሸለቆ ሰፍሮ ሳለ፣ ከሠላሳዎቹ አለቆች ሦስቱ ዳዊትን ለመገናኘት በዓዶላም ዋሻ አጠገብ ወደሚገኘው ወደ ዐለቱ ወረዱ።

16 በዚያ ጊዜ ዳዊት በምሽግ ውስጥ ነበረ፤ የፍልስጥኤማውያንም ሰራዊት በቤተ ልሔም ነበረ፤

17 ዳዊትም ውሃ ፈልጎ ነበርና፣ “ከቤተ ልሔም በር አቅራቢያ ከሚገኘው ጕድጓድ የምጠጣው ውሃ ማን ባመጣልኝ!” አለ።

18 በዚህ ጊዜ ሦስቱ የፍልስጥኤማውያንን ሰራዊት መካከል ሰንጥቀው በማለፍ በቤተ ልሔም በር አጠገብ ከሚገኘው ጕድጓድ ውሃ ቀድተው ለዳዊት አመጡለት፤ እርሱ ግን ሊጠጣው ስላልፈለገ በእግዚአብሔር ፊት አፈሰሰው።

19 ከዚያም፣ “ይህን ከማድረግ እግዚአብሔር ይጠብቀኝ፤ ይህ በሕይወታቸው ቈርጠው የሄዱትን የእነዚህን ሰዎች ደም እንደ መጠጣት አይደለምን?” አለ። ይህን ለማምጣት በሕይወታቸው ቈርጠው ስለ ነበር፣ ዳዊት ሊጠጣው አልፈለገም። ሦስቱ ኀያላን ሰዎች ያደረጉት ጀብዱ እንዲህ ነበር።

20 የኢዮአብ ወንድም አቢሳ የሦስቱ አለቃ ነበረ። እርሱም ጦሩን አንሥቶ ሦስት መቶ ሰዎች ገደለ፤ ከዚህም የተነሣ እንደ ሦስቱ ሁሉ ዝነኛ ሆነ።

21 ከሦስቱ አንዱ ሆኖ ባይቈጠርም እንኳ፣ ዕጥፍ ክብር አገኘ፤ አዛዣቸውም ሆነ።

22 ከቀብጽኤል የመጣውና ታላቅ ጀብዱ የሠራው የዮዳሄ ልጅ በናያስ ብርቱ ተዋጊ ነበረ። እርሱም እጅግ የታወቁ ሁለት የሞዓብ ሰዎችን ገደለ። እንዲያውም አንድ ጊዜ በረዶ ምድርን በሸፈነበት ቀን ወደ አንድ ጕድጓድ ወርዶ አንበሳ ገደለ።

23 ደግሞም ቁመቱ ዐምስት ክንድ የሆነ አንድ ግብጻዊ ገደለ፤ ግብጻዊው የሸማኔ መጠቅለያ የመሰለ ጦር በእጁ ቢይዝም፣ በናያስ ግን ቈመጥ ይዞ ገጠመው፤ ከግብጻዊው እጅ ጦሩን ነጥቆ በገዛ ጦሩ ገደለው።

24 የዮዳሄ ልጅ በናያስ የፈጸመው ጀብዱ ይህ ነበር፤ እርሱም እንደ ሦስቱ ኀያላን ዝነኛ ሆነ።

25 ከሠላሳዎቹም ይልቅ የበለጠ ክብር ተጐናጸፈ፤ ይሁን እንጂ ከሦስቱ አንዱ አልነበረም፤ ዳዊትም የክብር ዘቡ አዣዥ አደረገው።

26 ኀያላኑም እነዚህ ነበሩ፤ የኢዮአብ ወንድም አሣሄል፣ የቤተ ልሔሙ የዱዲ ልጅ ኤልያናን፣

27 ሃሮራዊው ሳሞት፣ ፍሎናዊው ሴሌስ፣

28 የቴቁሔ ሰው የሆነው የዒስካ ልጅ፣ ዒራስ፣ የዓናቶቱ ሰው አቢዔዜር፣

29 ኩሳታዊው ሴቦካይ፣ አሆሃዊው ዔላይ፣

30 ነጦፋዊው ማህራይ፣ የነጦፋዊው የበዓና ልጅ ሔሌድ፣

31 ከብንያም ወገን የጊብዓ ሰው የሆነው የሪባይ ልጅ ኤታይ፣ ጲርዓቶናዊው በናያስ፣

32 የገዓስ ሸለቆዎች ሰው የሆነው ኡሪ፣ ዐረባዊው አቢኤል፣

33 ባሕሩማዊው ዓዝሞት፣ ሰዓልቦናዊው ኤሊያሕባ፣

34 የጊዞናዊው የአሳን ልጆች፣ የሃራራዊው የሻጌ ልጅ ዮናታን፣

35 የሃራራዊው የሳኮር ልጅ አሒአም፣ የኡር ልጅ ኤሊፋል፣

36 ምኬራታዊው ኦፌር፣ ፍሎናዊው አኪያ፣

37 ቀርሜሎሳዊው ሐጽሮ፣ የኤዝባይ ልጅ ነዕራይ፤

38 የናታን ወንድም ኢዮኤል፣ የሃግሪ ልጅ ሚብሐር፣

39 አሞናዊው ጼሌቅ፣ የጽሩያ ልጅ የኢዮአብ ጋሻ ጃግሬ ብኤሮታዊው ነሃራይ፣

40 ይትራዊው ዒራስ፣ ይትራዊው ጋሬብ፣

41 ኬጢያዊው ኦርዮ፣ የአሕላይ ልጅ ዛባድ፣

42 የሮቤላዊው የሺዛ ልጅ ዓዲና፤ እርሱም የሮቤላውያንና ዐብረውት ለነበሩት የሠላሳ ሰዎች አለቃ ነበረ።

43 የማዕካ ልጅ ሐናን፣ ሚትናዊው ኢዮሣፍጥ፣

44 አስታሮታዊው ዖዝያ፣ የአሮዔራዊው የኮታም ልጆች ሻማና ይዒኤል፣

45 የሺምሪ ልጅ ይዲኤል፣ ወንድሙም ቴዳዊው ዮሐ፣

46 መሐዋዊው ኤሊኤል፣ የኤልነዓም ልጆች ይሪባይና ዮሻውያ፣ ሞዓባዊው ይትማ፣

47 ኤሊኤል፣ ዖቤድና ምጾባዊው የዕሢኤል።

መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™

የቅጂ መብት © 2001, 2024 በBiblica, Inc.

በፈቃድ የሚወሰድ። በዓለም ዐቀፍ ባለቤትነቱ።

The Holy Bible, New Amharic Standard Version™

Copyright © 2001, 2024 by Biblica, Inc.

Used with permission. All rights reserved worldwide. 

Biblica, Inc.
跟着我们:



广告