1 ዜና መዋዕል 10 - አዲሱ መደበኛ ትርጒምሳኦል ራሱን ገደለ 10፥1-12 ተጓ ምብ – 1ሳሙ 31፥1-13 ፤ 2ሳሙ 1፥4-12 1 በዚህ ጊዜ ፍልስጥኤማውያን እስራኤልን ወጉ፤ እስራኤላውያንም ከፊታቸው ሸሹ፤ ብዙዎቹም በጊልቦዓ ተራራ ላይ ተወግተው ወደቁ። 2 ፍልስጥኤማውያን ሳኦልንና ልጆቹን አጥብቀው አሳደዷቸው፤ የሳኦልንም ልጆች ዮናታንን፣ አሚናዳብንና ሜልኪሳን ገደሉ፤ 3 ውጊያው በሳኦል ላይ በረታበት፤ ቀስተኞችም ደርሰው ክፉኛ አቈሰሉት። 4 ሳኦልም ጋሻ ጃግሬውን፣ “እነዚህ ሸለፈታሞች መጥተው መሣለቂያ እንዳያደርጉኝ ሰይፍህን መዝዘህ ውጋኝ” አለው። ጋሻ ጃግሬው ግን እጅግ ፈርቶ ስለ ነበር ፈቃደኛ አልሆነም፤ ስለዚህ ሳኦል በገዛ ሰይፉ ላይ ወድቆ ሞተ። 5 ጋሻ ጃግሬውም ሳኦል መሞቱን ሲያይ፣ እርሱም በራሱ ሰይፍ ላይ ወድቆ ሞተ። 6 ስለዚህ ሳኦልና ሦስት ልጆቹ ሞቱ፤ ቤተ ሰዎቹም ሁሉ በአንድ ላይ ሞቱ። 7 በሸለቆው ውስጥ የነበሩት እስራኤላውያን ሁሉ ሰራዊቱ መሸሹን፣ ሳኦልና ልጆቹም መሞታቸውን ሲያዩ፣ ከተሞቻቸውን ለቅቀው ሸሹ፤ ፍልስጥኤማውያንም መጥተው ከተሞቹን ያዙ። 8 በማግስቱ ፍልስጥኤማውያን የሞቱትን ለመግፈፍ ሲመጡ፣ ሳኦልና ልጆቹ በጊልቦዓ ተራራ ላይ ወድቀው አገኟቸው። 9 ሳኦልን ከገፈፉ፣ ራሱን ከቈረጡና መሣሪያውንም ከወሰዱ በኋላ፣ ለጣዖቶቻቸውና ለሕዝቡ የምሥራቹን እንዲናገሩ ወደ መላው የፍልስጥኤም ምድር መልክተኞችን ላኩ። 10 የጦር መሣሪያውን በአማልክታቸው ቤተ ጣዖት አስቀመጡት፤ ራሱንም በዳጎን ቤተ ጣዖት ውስጥ አንጠለጠሉት። 11 የኢያቢስ ገለዓድ ሰዎች ፍልስጥኤማውያን በሳኦል ላይ ያደረጉትን በሰሙ ጊዜ፣ 12 ጀግኖቻቸው ሁሉ ተነሥተው የሳኦልንና የልጆቹን ሬሳ ወደ ኢያቢስ አመጡ፤ ዐጽማቸውንም ኢያቢስ ውስጥ በሚገኘው ትልቁ ዛፍ ሥር ቀበሩ፤ ሰባት ቀንም ጾሙ። 13 ሳኦል ለእግዚአብሔር ስላልታመነ ሞተ፤ የእግዚአብሔርን ቃል አልጠበቀም፤ ይልቁንም ከሙታን ጠሪ ምክርን ጠየቀ፤ 14 ይህን ከእግዚአብሔር አልጠየቀም፤ ስለዚህ እግዚአብሔር ገደለው፤ መንግሥቱንም ወደ እሴይ ልጅ ወደ ዳዊት እንዲተላለፍ አደረገ። |
መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™
የቅጂ መብት © 2001, 2024 በBiblica, Inc.
በፈቃድ የሚወሰድ። በዓለም ዐቀፍ ባለቤትነቱ።
The Holy Bible, New Amharic Standard Version™
Copyright © 2001, 2024 by Biblica, Inc.
Used with permission. All rights reserved worldwide.
Biblica, Inc.