ዘካርያስ 6 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉምነቢዩ ዘካርያስ ስለ አራቱ ሠረገሎች ያየው ራእይ 1 በሌላም ራእይ አራት ሠረገሎች ከሁለት የነሐስ ተራራዎች መካከል ሲወጡ አየሁ። 2 የመጀመሪያው ሠረገላ የሚሳበው በቀያይ ፈረሶች ሲሆን፥ ሁለተኛው ደግሞ በጥቋቊር ፈረሶች ነበር፤ 3 ሦስተኛው የሚሳበው በነጫጭ ፈረሶች ሲሆን አራተኛው ቡራቡሬ በሆኑ ፈረሶች ነበር፤ ሁሉም ኀይለኞች ነበሩ። 4 ከእኔ ጋር ይነጋገር የነበረውንም መልአክ “ጌታዬ እነዚህ ሠረገሎች የምን ምሳሌ ናቸው?” ብዬ ጠየቅሁት። 5 እርሱም “እነዚህ አራቱ ነፋሳት ናቸው፤ ቆመው ከሚያገለግሉበት ከምድር ሁሉ ጌታ ፊት አሁን ገና መውጣታቸው ነው” አለኝ። 6 በጥቋቊር ፈረሶች ይሳብ የነበረው ሠረገላ ወደ ሰሜን፥ በነጫጭ ፈረሶች ይሳብ የነበረው ወደ ምዕራብ፥ በቡራቡሬ ፈረሶች ይሳብ የነበረው ወደ ደቡብ አገሮች ይሄዱ ነበር። 7 ኀይለኞቹ ፈረሶች በወጡ ጊዜ ምድርን ለመቃኘት ተጣድፈው ነበር፤ መልአኩም “ሂዱ፤ ምድርን ቃኙ!” አላቸው፤ እነርሱም ምድርን ቃኙ። 8 ከዚህ በኋላ መልአኩ “ወደ ሰሜን አገሮች የሄዱት ፈረሶች የእግዚአብሔርን ቊጣ እንዲበርድ አደረጉ” ሲል ወደ እኔ ጮኸ። ኢያሱን ቀብቶ ለማንገሥ የተሰጠ ትእዛዝ 9 እግዚአብሔር እንዲህ አለኝ፦ 10 “ሔልዳይ፥ ጦቢያና ይዳዕያ የተባሉት ስደተኞች የሰጡትን ብርና ወርቅ ይዘህ ሳትዘገይ አሁኑኑ ወደ ሶፎንያስ ልጅ ወደ ኢዮስያስ ቤት ሂድ፤ እነዚህ ሁሉ ሰዎች ከባቢሎን የተመለሱ ምርኮኞች ናቸው፤ 11 እነርሱ ከሰጡት ብርና ወርቅ ዘውድ ሠርተህ በሊቀ ካህናቱ በኢዮሴዴቅ ልጅ በኢያሱ ራስ ላይ ድፋለት። 12 የሠራዊት አምላክ እንዲህ ይላል ብለህ ንገረው፦ ‘ቅርንጫፉ በቦታው ስለሚስፋፋ ቅርንጫፍ የሚባል ስም ያለው ይህ ሰው ነው። ባለበት ስፍራ በቅሎ ገናና ይሆናል፤ የእግዚአብሔርንም ቤተ መቅደስ እንደገና ይሠራል፤ 13 የእግዚአብሔርን ቤተ መቅደስ የሚመራ እርሱ ነው፤ የንጉሥነትን ክብር በመቀዳጀት በዙፋኑ ላይ ተቀምጦ ይገዛል፤ አንድ ካህን በዙፋኑ አጠገብ ይቆማል፤ ሁለቱም አብረው በስምምነትና በሰላም ይሠራሉ።’ 14 ዘውዱም በእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ሔሌም ለተባለ ለሔልዳይ፥ ለጦቢያ፥ ለይዳዕያና ለሰፎንያስ ልጅ ሔን ለኢዮስያስ ክብር መታሰቢያ ሆኖ ይቀመጣል።” 15 በዚያን ጊዜ በሩቅ የሚኖሩ ሰዎች የእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ሲታደስ ለመርዳት ይመጣሉ። ቤተ መቅደሱ በታደሰ ጊዜ እኔን ወደ እናንተ የላከኝ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር መሆኑን ታውቃላችሁ። ይህም ሁሉ የሚፈጸመው ለእግዚአብሔር ለአምላካችሁ ቃል ፍጹም ታዛዦች የሆናችሁ እንደ ሆነ ነው። |