Biblia Todo Logo
在线圣经

- 广告 -

ዘካርያስ 5 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም


ነቢዩ ዘካርያስ በራእይ ያየው ጥቅል የብራና መጽሐፍ

1 እንደገናም ስመለከት አንድ የተጠቀለለ መጽሐፍ በአየር ላይ ሲበር አየሁ፤

2 መልአኩም “ምን ታያለህ?” ብሎ ጠየቀኝ፤ እኔም “ርዝመቱ ዐሥር ሜትር፤ ስፋቱም አምስት ሜትር የሆነ፥ አንድ የተጠቀለለ የብራና መጽሐፍ በአየር ላይ ሲበር አያለሁ” አልኩት።

3 እርሱም እንዲህ አለኝ፦ “የተጠቀለለው መጽሐፍ በውስጡ በምድሪቱ ሁሉ ላይ የሚመጣው ርግማን ተጽፎበታል፤ የተጠቀለለው መጽሐፍ በአንድ በኩል ‘ሌባ ሁሉ ከምድር ይወገዳል’ የሚል ሲሆን፥ በሌላ በኩል ‘በመሐላ ሐሰት የሚናገር ሁሉ ይጠፋል’ ይላል።

4 የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር ‘ይህን ርግማን እልካለሁ፤ ወደ እያንዳንዱ ሌባና በስሜ ምሎ በሐሰት ወደሚናገር ሰው ቤት ይገባል፤ በገባበትም ጊዜ በዚያ ቈይቶ ቤታቸውን ሁሉ ያፈራርሰዋል’ ይላል።”


ነቢዩ ዘካርያስ በቅርጫት ውስጥ ስላለች ሴት ያየው ራእይ

5 መልአኩም እንደገና ወደ እኔ መጥቶ “የሚመጣው ነገር ምን እንደ ሆነ ተመልከት!” አለኝ።

6 እኔም “ይህ ነገር ምንድን ነው?” አልኩት። እርሱም “በምድሪቱ ሁሉ ላይ የሚሠራውን ኃጢአት የሚያመለክት ቅርጫት ነው” አለኝ።

7 ቅርጫቱ ከእርሳስ የተሠራ መክደኛ ነበረው፤ እኔም እያየሁት መክደኛው ተከፈተ፤ እነሆም በቅርጫቱ ውስጥ አንዲት ሴት ተቀምጣ ነበር።

8 መልአኩም “እነሆ ይህች ሴት የዐመፅ ምሳሌ ነች” ከአለኝ በኋላ ወደ ታች ገፍቶ ወደ ቅርጫቱ ውስጥ አስገባት፤ ክዳኑንም መልሶ ገጠመው።

9 ቀና ብዬ ስመለከት እነሆ ሁለት ሴቶች እየበረሩ ወደ እኔ መጡ፤ ክንፎቻቸውም እንደ ሽመላ ክንፎች ብርቱዎች ነበሩ። እነርሱም ያንን ቅርጫት ከመሬት አንሥተው ወደ ሰማይ ይዘውት በረሩ።

10 እኔም ከእኔ ጋር ይነጋገር የነበረውን መልአክ “ቅርጫቱን ወዴት ነው የሚወስዱት?” ብዬ ጠየቅሁት።

11 እርሱም “ወደ ሰናዖር ወስደው ቤት ሊሠሩለት ነው፤ ቤቱ ተሠርቶ ካለቀ በኋላ ቅርጫቱን በዚያ ያኖሩታል” አለኝ።

© The Bible Society of Ethiopia, 2005

© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997

Bible Society of Ethiopia
跟着我们:



广告