ዘካርያስ 14 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉምኢየሩሳሌምና የአሕዛብ መንግሥታት 1 የእግዚአብሔር ፍርድ ቀን ደርሶአል፤ በዚያን ጊዜ ዐይናችሁ እያየ በዝባዦች ከእናንተ የወሰዱትን ይካፈሉታል። 2 ኢየሩሳሌምን እንዲወጉ እግዚአብሔር ሕዝቦችን ሰብስቦ ይመጣል፤ ከተማይቱ ትያዛለች፤ ቤቶች ይበዘበዛሉ፤ ሴቶች ይደፈራሉ፤ ከሕዝቡም እኩሌታው ተማርኮ ይሄዳል፤ የቀሩት ግን ከከተማይቱ አይወጡም። 3 ከዚያን በኋላ እግዚአብሔር በጦርነት ጊዜ እንደሚዋጋ ሕዝቦችን ለመውጋት ይነሣል። 4 በዚያን ቀን እግዚአብሔር ከኢየሩሳሌም በስተ ምሥራቅ ባለው በደብረ ዘይት ተራራ ላይ ይቆማል፤ የደብረ ዘይት ተራራም ከምሥራቅ እስከ ምዕራብ በሰፊ ሸለቆ በሁለት ይከፈላል፤ ስለዚህም የተራራው እኩሌታ ወደ ሰሜን እኩሌታውም ወደ ደቡብ ፈቀቅ ይላል። 5 እናንተም ተራራውን በሁለት ከፍሎ እስከ አጻል በደረሰው በዚህ ሸለቆ ውስጥ አልፋችሁ ታመልጣላችሁ፤ በይሁዳ ንጉሥ በዖዝያ ዘመን ምድር በተናወጠች ጊዜ የቀድሞ አባቶቻችሁ በሸሹት ዐይነት ትሸሻላችሁ፤ እግዚአብሔር አምላኬም ቅዱሳኑን አስከትሎ ይመጣል። 6 በዚያን ዘመን ውርጭና ዐመዳይ ጨለማም ከቶ አይኖርም፤ 7 በእግዚአብሔር ዘንድ የታወቀ አንድ ተከታታይ ቀን ይመጣል፤ በምሽት ጊዜ ብርሃን ስለሚሆን ቀንም ሌሊትም የለም። 8 በዚያን ቀን ከኢየሩሳሌም የሕይወት ውሃ ይፈልቃል፤ ከእርሱም እኩሌታው በምሥራቅ በኩል ወደ ሙት ባሕር፥ እኩሌታው በምዕራብ በኩል ወደ ሜዲቴራኒያን ባሕር ይፈስሳል፤ በበጋም ሆነ በክረምት ዓመቱን ሙሉ ሲፈስ ይኖራል። 9 በዚያን ጊዜ እግዚአብሔር በዓለም ሁሉ ይነግሣል፤ ሰዎችም አምላክ እርሱ ብቻ መሆኑን ያምናሉ፤ የእርሱንም ስም ብቻ ይጠራሉ። 10 በሰሜን ከጌባዕ አንሥቶ ኢየሩሳሌምን በደቡብ በኩል አልፎ እስከ ሪሞን ድረስ ያለው አውራጃ ደልዳላ ይሆናል፤ ኢየሩሳሌም በዙሪያዋ ካለው ምድር በላይ ከፍ ትላለች፤ ከተማይቱም ከብንያም በር አንሥቶ በቀድሞው በር አቅጣጫ እስከ ማእዘን በር እንዲሁም ከሐናንኤል ግንብ አንሥቶ እስከ ቤተ መንግሥቱ ወይን መጭመቂያው ድረስ ከፍ በማለት ጸንታ ትኖራለች። 11 ኢየሩሳሌም የሕዝብ መኖሪያ ትሆናለች፤ ከእንግዲህ ወዲህ ጥፋት አይደርስባትም፤ ሕዝብዋም ያለ ስጋት በሰላም ይኖራል። 12 ኢየሩሳሌምን ለመውጋት በሚነሣሡ ሕዝቦች ላይ እግዚአብሔር ቀሣፊ በሽታ ያመጣባቸዋል፤ በሕይወት እያሉ ሥጋቸው ይበሰብሳል፤ ዐይናቸው በዐይነስባቸው ውስጥ፥ ምላሳቸውም በአፋቸው ውስጥ ይበሰብሳል። 13 በዚያን ጊዜ እግዚአብሔር ሁከትና ፍርሀት ስለሚለቅባቸው እያንዳንዱ ሰው በአጠገቡ ያለውን ሌላ ሰው ይዞ አደጋ ይጥልበታል። 14 የይሁዳ ሰዎች ኢየሩሳሌምን ለመከላከል ይዋጋሉ፤ በዙሪያዋም ያሉትን መንግሥታት ሀብት ሁሉ ማርከው ይወስዳሉ፤ ከሚወስዱትም ምርኮ ወርቅ፥ ብርና የልብስ ዐይነት እጅግ ብዙ ይሆናል። 15 ያንን የሚመስል ቀሣፊ በሽታ በጠላት ሰፈር ባሉ እንስሶች በፈረሶች፥ በበቅሎዎች፥ በግመሎችና በአህዮች ሁሉ ላይ ይመጣል። 16 ከዚያም በኋላ ኢየሩሳሌምን ከወጉአት መንግሥታት መካከል ከጥፋት የተረፉት ለንጉሡ ለሠራዊት አምላክ ሊሰግዱለትና የዳስ በዓልንም ለማክበር በየዓመቱ ወደ ኢየሩሳሌም ይወጣሉ። 17 ለንጉሡ ለሠራዊት አምላክ የማይሰግዱለት ሕዝቦች ቢኖሩ በምድራቸው ዝናብ አይዘንብላቸውም። 18 ግብጻውያንም በዓሉን ለማክበር ወደ ኢየሩሳሌም ወጥተው በእግዚአብሔር ፊት መቅረብ ባይፈልጉ፥ “ወደ ኢየሩሳሌም ወጥተን የዳስ በዓል አናከብርም” በሚሉ መንግሥታት ላይ የሚደርሰው ቀሣፊ በሽታ ይመጣባቸዋል። 19 ግብጻውያንም ሆኑ ሌሎች መንግሥታት “የዳስ በዓል አናከብርም” ቢሉ የሚደርስባቸው ቅጣት ይህ ነው። 20 በዚያን ጊዜ በፈረሶች አንገት ላይ በሚንጠለጠል ቃጭል ሁሉ ላይ “ለእግዚአብሔር የተለየ” የሚል የጽሕፈት ምልክት ይቀረጽበታል፤ በቤተ መቅደሱ ውስጥ ያለው የማብሰያ ማሰሮ በመሠዊያው ላይ እንደሚገኘው ሳሕን የተቀደሰ ይሆናል። 21 በኢየሩሳሌምና በይሁዳ ምድር የሚገኘው ማሰሮ ሁሉ ለሠራዊት አምላክ የተለየ ይሆናል፤ መሥዋዕት የሚያቀርቡ ሰዎች ሁሉ በማሰሮዎቹ ጥቂቱን የመሥዋዕቱን ሥጋ ያበስሉባቸዋል፤ በዚያን ጊዜ በሠራዊት ጌታ በእግዚአብሔር መቅደስ ውስጥ የሚነግድ ማንም ሰው አይኖርም። |