ዘካርያስ 13 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም1 የሠራዊት አምላክ እንዲህ ይላል፦ “በዚያን ጊዜ ለዳዊት ልጆችና የኢየሩሳሌም ነዋሪዎች ከኃጢአታቸውና ከርኲሰታቸው የሚያነጻ ምንጭ ይከፈታል። 2 በዚያን ጊዜ የጣዖቶችን ስሞች ከምድሪቱ ላይ አስወግዳለሁ፤ ዳግመኛም የሚያስታውሳቸው አይኖርም፤ የጣዖት ነቢያትንና ርኩሳን መናፍስትን አስወግዳለሁ። 3 ማንም ነቢይ ነኝ ብሎ ቢነሣ የወለዱት አባቱና እናቱ በእግዚአብሔር ስም ሐሰትን ስለ ተናገርክ መሞት አለብህ ይሉታል፤ ትንቢትም ሲናገር ወላጆቹ ወግተው ይገድሉታል። 4 በዚያን ጊዜ ማንኛውም ነቢይ ነኝ ባይ በሚያየው ትንቢታዊ ራእይ ያፍርበታል፤ ሰዎችንም ለማታለል ጠጒር ያለበትን ልብስ ለብሶ አይታይም። 5 እኔ ገበሬ ነኝ እንጂ ነቢይ አይደለሁም፤ ከወጣትነቴ ጀምሮ የእርሻ መሬት ባለቤት ነኝ ይላል። 6 አንድ ሰው ‘ታዲያ ይህ በሰውነትህ ላይ ያሉት ቊስሎች ምንድን ናቸው?’ ብሎ ቢጠይቀው ‘በወዳጄ ቤት የቈሰልኩት ነው’ ብሎ ይመልስለታል።” የእግዚአብሔር እረኛ 7 የሠራዊት አምላክ እንዲህ ይላል፦ “ሰይፍ ሆይ! ተባባሪዬ በሆነው በእረኛዬ ላይ ንቃ! በጎቹ ይበተኑ ዘንድ እረኛውን ምታ! እኔም በታናናሾቹ ላይ እጄን አነሣለሁ። 8 በአገሪቱ ላይ ካሉት ሕዝቦች ከሦስቱ ሁለቱ እጅ ተመተው ይሞታሉ፤ ሆኖም ከሦስቱ አንዱ እጅ ይቀራል። 9 እነርሱንም ወደ እሳት እጨምራቸዋለሁ፤ ብርም በእሳት እንደሚጠራ አጠራቸዋለሁ፤ ወርቅም እንደሚፈተን እፈትናቸዋለሁ፤ ከዚያን በኋላ ወደ እኔ ይጸልያሉ፤ እኔም እመልስላቸዋለሁ። እኔ ‘ሕዝቤ’ ብዬ እጠራቸዋለሁ፤ እነርሱም ‘እግዚአብሔር አምላካችን’ ብለው ይጠሩኛል።” |